Lidetu Ayalew (Photo: Addis Fortune)

አቶ ልደቱ አያሌው (ፎቶ፡ ፎርቹን)

አቶ ልደቱ የዋስትና ጥያቄያቸውን በሌላ መዝገብ ማቅረብ ይችላሉ ተባለ

ኢዛ (ሰኞ ነኀሴ ፳፭ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. August 31, 2020)፦ በአቶ ልደቱ አያሌው ላይ ክስ እስኪመሠረት ተጨማሪ የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ እንዲሰጠው የጠየቀው መርማሪ ፖሊስ፤ ጥያቄውን ፍርድ ቤቱ ውድቅ በማድረግ፤ አቶ ልደቱ በሌላ መዝገብ የዋስትና ጥያቄያቸውን እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ተሰጠ።

የቢሾፍቱ ወረዳ ፍርድ ቤት ዛሬ ሰኞ ነኀሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. በዋለው ችሎት የመርማሪ ፖሊሶቹን ጥያቄ ውድቅ ያደረገው ጥያቄው አግባብነት የሌለው ነው በሚል ነው።

ፍርድ ቤቱ በአቶ ልደቱ መዝገብ ላይ ምርመራ መጠናቀቁን በመግለጽ፤ ከወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት አንቀጽ 591 እና 592 መሠረት ፖሊስ ያቀረበው ጥያቄ ተገቢ ያለመኾኑንና ያጠናከረው መዝገብ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የማያሰጥ ነው ብሏል። በመኾኑም የፖሊስ ጥያቄ የሕግ አግባብነት ስለሌለው ውድቅ መደረጉን ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

የዋስትና መብታቸውን መጠየቅ እንደሚችሉ የተገለጸላቸው አቶ ልደቱ፤ ይህ ጥያቄያቸው ግን አሁን በተከሰሱበት መዝገብ የተዘጋ በመኾኑ የዋስትና ጥያቄያቸው በሌላ መዝገብ ማቅረብ እንደሚችሉ ፍርድ ቤቱ አዟል። ፍርድ ቤቱ እስካሁን ያለውን የፖሊስ መዝገብም ዘግቶ ፋይሉን ወደ መዝገብ ቤት ልኮታል።

አቶ ልደቱ የአርቲስ ሐጫሉ ሁንዴሳን ሞት ተከትሎ በቢሾፍቱ (በደብረዘይት) ከተማ ለወጣቶች ገንዘብ በመስጠት ለብጥብጥና ለአመጽ በማነሳሳት በሚል ወንጀል ተጠርጥረው መታሰራቸው ይታወቃል። ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡትም ለአራተኛ ጊዜ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ