PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባንኮችን አስጠንቅቀዋል

ኢዛ (ሰኞ መስከረም ፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 14, 2020)፦ የኢትዮጵያ መንግሥት ዛሬ (ሰኞ መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም.) ለቀየራቸው የብር ኖቶች ከ3.7 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደወጣ አስታወቀ።

የገንዘብ ለውጡን አስመልክቶ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሰጠው መግለጫ 2.9 ቢሊዮን ለሚኾነው የብር ኖት በአጠቃላይ ለሕትመቱ የወጣው ወጪ 3.7 ቢሊዮን ብር ነው። በቁጥር ሁለት ነጥብ ዘጠን ቢሊዮን (2.9 ቢሊዮን) የሚኾኑት ኖቶች ጠቅላላ የገንዘብ መጠን 262 ቢሊዮን ብር እንደኾነ ታውቋል።

በተለያዩ አገሮች ባሉ ኩባንያዎች የታተሙት አዲሶቹ የገንዘብ ኖቶችን፤ አብዛኛውን በአንድ ወር ለውጦ ለማጠናቀቅ የታቀደ ሲሆን፤ አጠቃላይ የብር ኖቶቹ ለውጥ በምንም ሁኔታ ከሦስት ወር እንደማይዘል ተገልጿል።

ገንዘብ የሚለውጡ ሰዎች ከ10 ሺህ ብር በላይ ይዘው ወደባንክ ከሔዱ፤ አካውንት መክፈት ይኖርባቸዋል። በዚህ የገንዘብ ለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ ከ1.5 ሚሊዮን ብር በላይ ይዞ የተገኘ የሚወረስበት ስለመኾኑም የገንዘብ ለውጡን በተመለከተ ከተሰጠው ማብራሪያ ለማወቅ ተችሏል።

ከገንዘብ ለውጡ ጋር ተያይዞ ማንኛውም ባንክ የገንዘብ ለውጡን የተመለከቱ አሠራሮችን ተላልፎ ምንም ዐይነት ጥፋት ቢገኝበት፤ ባንኩን እስከመዝጋት እርምጃ እንደሚወሰድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጥብቅ አሳስበዋል።

አንዳንድ ባንኮች ፎርጅድ (ሕገወጥ) ገንዘብ እየተቀበሉ ስለመኾኑ በተደረገ ክትትል የተደረሰባቸው ጭምር መኾኑን በመጠቆም፤ በዚህ የገንዘብ ለውጥ ውስጥ አንድም ፎርጅድ የብር ኖት የተገኘበት ባንክ ላይ ከፍተኛ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።

ይህ ብቻ ሳይሆን የባንክ ፕሬዝዳንቶችና ቦርዶችም ይህንን የገንዘብ ለውጥ በአግባቡ ተከታትለው ካልሠሩም ብርቱ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

ግድፈቱ የተገኘበት የባንክ ኃላፊም በየትኛውም ባንክ እንዳይሠራ እንደሚደረግ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገልጸዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ