በብር ኖት ለውጡ ምክንያት ንብረት በጥሬ ገንዘብ መገበያየት ተከለከለ
እየተቀየረ ያለው አሮጌው የኢትዮጵያ ብር
በስጦታ የሚተላለፉ ውሎች አገልግሎት ቆሟል
ኢዛ (ሐሙስ መስከረም ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 17, 2020)፦ ማንኛውም ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረት በጥሬ ገንዘብ መግዛት የሚከለክለውን አሠራር ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ መጀመሩን የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ኤጀንሲ አስታወቀ።
የገንዘብ ለውጡን ተከትሎ ኤጀንሲው ይፋ ባደረገው መረጃ ከዛሬ ጀምሮ የሚንቀሳቀስም ኾነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ሽያጭ ውል አረጋግጦ ለመመዝገብ በጥሬ ገንዘብ የሚደረጉ ሽያጮችን የማያስተናግድ መኾኑን ነው።
ከንብረት ሽያጭ ባሻገር የብድር ውሎችን ሰነድ አረጋግጦ የምዝገባ አገልግሎት ለማግኘት፤ የሽያጭ ዋጋው ከገዥው የባንክ ሒሳብ ተቀናሽ ኾኖ ወደ ሻጭ የባንክ ሒሳብ የተላለፈ ወይም ገቢ የተደረገበት ሰነድ ሲቀርብ ብቻ ነው።
በተመሳሳይም የብድር ውሎችም የሚመዘገቡት፤ ከአበዳሪው ባንክ ወደ ተበዳሪው የባንክ ሒሳብ ገንዘቡ የተላለፈ መኾኑን የሚያረጋግጥ መረጃ ሲቀርብ ብቻ መኾኑንም አሳውቋል።
ይህም ማንኛውም የንብረት ግብይት ማረጋገጫ የሚሰጠው በባንክ በኩል በተላለፈ አሠራር ብቻ ሲሆን፤ የጥሬ ገንዘብ ግብይቶች የማይስተናገዱ መኾኑን ለማወቅ ተችሏል።
የዚህን የአሠራር ማሻሻያ አስመልክቶ ዛሬ ሐሙስ መስከረም 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በተሰጠው ማብራሪያ፤ የስጦታ ውሎች አገልግሎትም ላልተወሰነ ጊዜ ተቋርጧል።
እንዲህ ያለውን ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገው የብር ኖት ለውጥን ተከትሎ ሕገወጥ የንብረት ሽያጭና ግዥን ለመቆጣጠር ሲሆን፤ ተገልጋዮች በባንክ በኩል እንዲጠቀሙ ለማስቻል ጭምር ነው።
ሕገወጦች በሕገወጥ መንገድ ያከማቹትን ገንዘብ ወደ ንብረት ለመለወጥ የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ለመገደብ ጭምር ታስቦ ተግባራዊ የሚኾነው አሠራር፤ ከብር ኖት ለውጡ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር ይችላል የተባለውን ሥጋት ይደፍናል ተብሎ ታምኖበታል።
ከማይንቀሳቀሱ ንብረቶች ቤት እና ሕንፃዎች በዋናነት የሚጠቀሱ ሲሆን፤ ከተንቀሳቃሽ ንብረቶች ውስጥ አንዱ ተሽከርካሪ ነው። (ኢዛ)



