ሀንፈሬ አሊሚራህ አረፉ

የአፋር ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ
“እንኳን እኛ ግመሎቻችን የኢትዮጵያን ባንዲራ ይለዩታል” ሀንፈሬ አሊሚራህ
ኢዛ (እሁድ መስከረም ፲ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 20, 2020)፦ የአፋር ሱልጣን ሀንፈሬ አሊሚራህ ባደረባቸው ሕመም የሕክመና ክትትል ሲያደርጉ ቆይተው፤ በ74 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
ከ2004 ዓ.ም. ጀምሮ ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የአፋር ሕዝብ ሱልጣን በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩት ሱልጣን ሀንፈሬ፤ የአፋር ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፕሬዝዳንት በመኾን ክልሉን ሲመሩ እንደነበር አይዘነጋም። ከክልል ፕሬዝዳንትነታቸውን ከለቀቁ በኋላ በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር በመኾን አገልግለዋል።
የሱልጣን ሀንፈሬ ሥርዓተ ቀብር ነገ መስከረም 11 ቀን 2013 ዓ.ም. በአሳይታ ከተማ በሀደሌ ጌራ ይፈጸማል ተብሎ ይጠበቃል። ሱልጣን ሀንፈሬ በተለይ የኢትዮጵያን ባንዲራ “እንኳን እኛ ግመሎቻችንም ይለዩታል” በሚል ኢትዮጵያዊነትን የገለጹበት መንገድ ይታወስላቸዋል። (ኢዛ)