የምክትል ኤታማዦር ሹሙ ማስጠንቀቂያ

ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ
በኃይል ፍላጎቴን አሳካለሁ በሚል ማናቸውም አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ እንገደዳለን አሉ
ኢዛ (ሐሙስ መስከረም ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 24, 2020)፦ ሕገ መንግሥቱን በጣሰ መልኩ በኃይል ፍላጎቴን አሳካለሁ በሚል የትኛውም አካል ላይ እርምጃ ለመውሰድ የሚገደዱ መኾናቸውን ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ አስታወቁ።
ምክትል ኤታማዦር ሹሙ እንዲህ ያለውን መልእክታቸውን ያስተላለፉት ዛሬ ሐሙስ መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ ነው።
በሕገ መንግሥቱ መሠረት ሥልጣን የሚያዘው በምርጫና በምርጫ ብቻ መኾኑን በመጠቆም፤ የሽግግርና ባለአደራ በሚል ትርምስ አለመኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ አንጻር ከመስከረም 30 በኋላ መንግሥት የለምና እንደፈለግኹ እኾናለሁ የሚል አካሔድ ሕገወጥ በመኾኑ፤ ሕገ መንግሥቱን በጣሰ መልኩ “በኃይል ፍላጎቴን” አሳካለሁ በሚል የትኛውም አካል ላይ ሠራዊቱ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚገደድም ገልጸዋል።
ፍላጎቴን በኃይል እጭናለሁ ማለት ፈጽሞ ሕገ መንግሥታዊ አለመኾኑን በመጥቀስም፤ ሠራዊቱንም አትፈታተኑ በማለት አስጠንቅቀዋል። ከዚህ በኋላ በሕገወጥ መንገድ የሚሔደው ላይ እርምጃ ይወሰዳልም ብለዋል። (ኢዛ)