Benishangul Gumuz

ቤንሻንጉል ጉሙዝ

የሰብአዊ መብት ኮሚሽን 15 ሰዎች መገደላቸውን አረጋግጫለሁ አለ

ኢዛ (ዓርብ መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 25, 2020)፦ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን፣ ዳንጉር ወረዳ፣ ማንቡክ ከተማ በንገዝ ወንዝ አካባቢ በሚገኝ መንደር ዛሬ ከንጋቱ 10 ሰዓት አካባቢ ዳግመኛ ጥቃት ተሰንዝሮ ከ15 - 20 የሚኾኑ ንጹኀን ሕይወታቸው መቀጠፉ ተገለጸ።

ዛሬ ዓርብ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ሊነጋጋ ሲል ከሌሊቱ 10 ሰዓት ገደማ ያልታወቁ ታጣቂዎች ናቸው በተባሉ ሰዎች ንጹኀንን መግደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት አረጋግጠዋል።

በአካባቢው ካለፉት ጥቂት ሳምንታት ወዲህ በእነዚህ ያልታወቁ በሚባሉ ታጣቂዎች ተደጋጋሚ ጥቃት ተሰንዝሮ ለሕይወት መጥፋትና በሺህዎች ለሚቆጠሩ ነዋሪዎች መፈናቀል ምክንያት ኾኗል። ጥቃቱን ለማስቆምና በአካባቢው ሰላም ለመፍጠር በዞኑ የኮማንድ ፖስት ለሦስት ወራት መራዘሙ በተገለጸ በቀናት ልዩነት የተፈጠረው አዲስ ጥቃት አካባቢውን የሥጋት ቀጠና አድርጎታል።

የዛሬውን ሌሊት/ንጋት ጥቃት ተከትሎ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ማምሻውን ባወጣው መግለጫ ደግሞ 15 ሰዎች ሕይወት ስለመጥፋቱ አስመልክቶ አሁንም በክልሉ ተጨማሪ ሕይወት እየጠፋ መኾኑን ጠቅሷል።

ኮሚሽኑ አረጋግጫለሁ ባለው መረጃ፤ ከሞቱት ሰዎች መካከል 11 ወንዶች እና አራት ሴቶች ናቸው።

በኮሚሽኑ መግለጫ መሠረት ጥቃቱ የተፈጸመው በሕገወጥ ታጣቂዎች እንደኾነና ኮሚሽኑ በደረሰው መረጃ መሠረትም፤ ታጣቂዎቹ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የተኩስ ልውውጥ ካካሔዱ በኋላ ጥቃቱ የተፈጸመበትን አካባቢ መከላከያ ሠራዊት ከቀኑ 7 ሰዓት አካባቢ ስለመቆጣጠሩም ጠቅሷል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ኢሰመኮ ጋዜጣዊ መግለጫ፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ተጨማሪ ሕይወት መጥፋት

“የዜጎችን ደኅንነት ማረጋገጥ እና ወንጀለኞችን ለፍርድ ማቅረብ ያስፈልጋል!"

(አሶሳ፤ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም.) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በድጋሚ በተፈጸመ ጥቃት ቢያንስ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉ በእጅጉ አሳሳቢነቱን እንደጨመረ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገለጸ፡፡

ዛሬ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ በመተከል ዞን፣ ዳንጉር ወረዳ፣ ማንቡክ ከተማ በንገዝ ወንዝ አካባቢ በሚገኝ መንደር በታጠቁ ሰዎች በተከፈተ ተኩስ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡

እስከ ዛሬ ቀኑ 8 ሰዓት ድረስ በተሰበሰበ መረጃ፤ 15 ያልታጠቁ ሲቪል ሰዎች ሕይወት ማለፉን እና ከሟቾች መካከልም 11 ወንዶች እና 4 ሴቶች መኾናቸውን ከአካባቢው ካሉ የመንግሥት ምንጮች ኮሚሽኑ አረጋግጧል፡፡ የሟቾች ዕድሜ እስካሁን ያልተለየ ሲሆን፤ በተጨማሪም አንድ ሰው ለሕይወት የማያሰጋ መቁሰል እንደደረሰበት ተመሳሳይ ምንጮች ለኮሚሽኑ አስረድተዋል፡፡ የአገር መከላከያ ሠራዊት አሁንም የተጎዱ ሰዎችን ለማፈላለግ አሰሳ እያካሔደ ሲሆን፤ ምናልባት የተጎዱ ሰዎች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል ሥጋት መኖሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

እስካሁን ያሉ መረጃዎች ጥቃቱ የተፈጸመው በሕገወጥ ታጣቂዎች እንደኾነ የሚያመለክቱ ሲሆን፤ ኮሚሽኑ በደረሰው መረጃ መሠረት ታጣቂዎቹ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የተኩስ ልውውጥ ካካሔዱ በኋላ ከቀኑ 7 ሰዓት ላይ የመከላከያ ሠራዊት አካባቢውን እንደተቆጣጠረ ለማረጋገጥ ችሏል፡፡

የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፤ “በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጸጥታን ማስፈን፣ የሕግ በላይነትን ማረጋገጥና በሲቪል ሕዝብ ላይ አሰቃቂ ጥቃት እያደረሱ ያሉትን አጥፊዎች አድኖ ለፍትሕ ማቅረብ እጅግ አፋጣኝ ትኩረት ይሻል” ብለዋል፡፡

ከትላንት መስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ የመተከል ዞን አራት ወረዳዎች የጸጥታ ኃላፊነት እስከ ኅዳር 2013 ድረስ በኮማንድ ፖስት ሥር እንዲኾን በተሰጠ ውሳኔ መሠረት፤ የጸጥታ ማስከበሩን ሥራ የፌደራል መንግሥት ተረክቧል፡፡ በኮማንድ ፖስቱ ሥር የሚቆዩት ትናንት ንጋቱ ላይ ጥቃት ያጋጠመው የዳንጉር ወረዳን ጨምሮ የወምበራ፣ ቡለን እና ጉባ ወረዳዎች ናቸው፡፡

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ