የአርቲስት ሐጫሉን ግድያ ተከትሎ በተፈጸሙ ወንጀሎች ምርመራ ተጠናቀቀ

የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ፍቃዱ ጸጋ (በግራ) እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ሁሴን ዑስማን (በቀኝ)
የፌዴራልና የኦሮሚያ ዓቃቤ ሕጎች በ5,728 ግለሰቦች ላይ ክስ መመሥረታቸው ተገለጸ
በኹከቱ የወደመ ንብረት 4.7 ቢሊዮን ብር ነው
በሐረር ሐውልት ያፈረሱ በሽብር ሕጉ ይጠየቃሉ
ኢዛ (ቅዳሜ መስከረም ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 26, 2020)፦ ከአርቲስት ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ በተፈጸሙ ወንጀሎች ዙሪያ በኦሮሚያ ክልል ሲያካሒድ የነበረውን ምርመራ ዓቃቤ ሕግ ማጠናቀቁንና በወቅቱ በተፈጸሙ ጥቃቶች 4.67 ቢሊዮን ብር ግምት ያለው ንብረት መውደሙን ገለጸ።
ከምርመራው በኋላ ብ488 የክስ መዝገቦች 5,728 ግለሰቦች ላይ ክስ መመሥረቱንና የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ፍቃዱ ጸጋ እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ አቶ ሁሴን ዑስማን ዛሬ ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም. አስታውቀዋል።
የምርመራ ሒደቱን መጠናቀቅ አስመልክቶ የፌዴራልና የኦሮሚያ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ክስ ከተመሠረተባቸው 3,377 ተከሳሾች ውስጥ በፌዴራል መንግሥት ሥልጣን ሥር የሚወድቅ ወንጀል በመፈጸማቸው፤ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በኩል ክስ የተመሠረተባቸው ናቸው። በኦሮሚያ ዓቃቤ ሕግ ክስ የተመሠረተባቸው ደግሞ 2,351 መኾናቸውንም አመልክተዋል።
በፌዴራል ደረጃ ተከሳሾች ውስጥ 114 የክስ መዛግብት ክሳቸው መደራጀቱን የሚያመለክተው መረጃ፤ በኦሮሚያ ደግሞ በ374 የክስ መዛግብት ክሳቸው ተደራጅቷል።
ከእነዚህ ተከሳሾች ውስጥ 63 ግለሰቦች በሐረር በፈረሱ ሐውልቶች ምክንያት፤ በሽብር ሕጉ መሠረት ተጠያቂ መኾናቸውንም በዛሬው የዓቃቤ ሕግ መግለጫ ላይ ተጠቅሷል።
የአርቲስት ሐጫሉን ግድያ ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል በተፈጠረው ኹከት የ167 ሰዎች ሕይወት ማለፉንና 369 ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም የኦሮሚያና የፌዴራል ዓቃቤ ሕጎች ባደረጉት ምርመራ ማረጋገጥ መቻላቸውንም አመልክቷል።
በዚህ ኹከት የተፈጠረውን የንብረት ውድመት በተመለከተም በተደረገው ምርመራ፤ የወደመው ንብረት መጠን ከ4.67 ቢሊዮን ብር በላይ እንደኾነም አመልክተዋል። (ኢዛ)