አርቲስት አልማዝ ኃይሌ አረፈች

አርቲስት አልማዝ ኃይሌ
ሥርዓተ ቀብሯ ነገ ይፈጸማል
ኢዛ (ዓርብ መስከረም ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. September 25, 2020)፦ ከ42 ዓመታት በላይ በሞያዋ መልካም ሥም ያተረፈችው ታዋቂዋ አርቲስት አልማዝ ኃይሌ ዛሬ ዓርብ መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት ተለየች። ባለፈው መስከረም 1 ቀን 2013 ዓ.ም. የ75ኛ ዓመት የልደት በዓልዋ ተከብሮላት ነበር።
ከሁለት ሳምንት በፊት ከደም ግፊት ጋር በተገናኘ በስትሮክ ተመትታ በሕመም ከቆየች በኋላ በዛሬው ዕለት ሕይወትዋ ማለፉ የተነገረ ሲሆን፤ ሥርዓተ ቀብሯም ነገ ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ በስድስት ሰዓት በመንበረ ጽባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።
በሁለት ሳምንታት ሕመም ሕይወትዋ ማለፉ የተነገረ ሲሆን፤ ሥርዓተ ቀብሯም ነገ ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀኑ በስድስት ሰዓት በመንበረ ጽባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል።
በቲያትር፣ በተከታታይ የቴሌቭዥንና የሬድዮ ድራማ፤ እንዲሁም በተለያዩ የማስታወቂያ ሥራዎቿ ዝናን ያተረፈችው አርቲስት አልማዝ፤ በተወዛዋዥነትም መሥራትዋ ይታወቃል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ድረገጽ ዝግጅት ክፍል ለመላው ቤተሰቦችዋ፣ ወዳጆችዋ እና አድናቂዎችዋ መጽናናትን ይመኛል። (ኢዛ)