ተጠባቂው የሁለቱ ምክር ቤቶች ስብሰባ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ይካሔዳል

ሕወሓቶች በስብሰባው ይገኛሉን?
የሕወሓት አባላት ይገኛሉ ወይስ አይገኙም የሚለው በጉጉት እየተጠበቀ ነው
ኢዛ (ሰኞ መስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 5, 2020)፦ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ስብሰባቸውን ዛሬ ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ያካሒዳሉ። የሕወሓት የሁለቱም ምክር ቤቶች አባላት በስብሰባው ላይ ይገኛሉ ወይስ አይገኙም የሚለው በጉጉት እየተጠበቀ ነው።
የምክር ቤቶቹ ስድስተኛ ዓመት የሥራ ጊዜ መክፈቻ ሥነ ሥርዓት ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበትና በሚያደርጉት ንግግር ይከፈታል።
ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በ2013 በጀት ዓመት የፌዴራል መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በይፋ የሚያስታውቁበትን ንግግር ያደርጋሉ።
በዚህ ስብሰባ ከሁለቱም የምክር ቤት አባላት በተጨማሪ ታዋቂ ሰዎች፣ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ አምባሳደሮች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በዚህ ስብሰባ ላይ እንዲገኝ የቀረበለትን ጥያቄ ያልተቀበለ ሲሆን፤ ስብሰባው ሕጋዊ አይደለም በማለት በደብዳቤ አሳውቋል።
ዛሬ ተጠባቂ የሚኾነው ደግሞ፤ በሁለቱ ምክር ቤቶች የሕወሓት ተወካዮች መገኘት አለመገኘታቸው ነው። (ኢዛ)