House of Federation and TPLF

የፌዴሬሽን ምክር ቤት (በግራ)፤ ሕወሓት (በቀኝ)

የፌዴራል መንግሥቱ ከከተማና ከቀበሌ አስተዳደሮችና ሕጋዊ ተቋማት ጋር ብቻ ግንኙነት ያደርጋል

ኢዛ (ማክሰኞ መስከረም ፳፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 6, 2020)፦ የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል ምክር ቤት እና ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ግር ምንም ዐይነት ግንኙነት ማድረግ እንደማይችል የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም. ወሰነ።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ነኀሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሔደው አስቸኳይ ጉባዔ፤ በትግራይ ክልል የሚካሔደው ምርጫ እንዳልተደረገ የሚቆጠር መኾኑን ተከትሎ የተሰጠ ውሳኔ ነው።

በክልሉ የሚደረገው ምርጫ እንዳልተፈጸመ እና እንደማይጸና ጭምር በወቅቱ ውሳኔ ማሳለፉ የሚታወስ ሲሆን፤ የዛሬው ውሳኔም ይህንኑ ውሳኔውን ተከትሎ የተላለፈ መኾኑ ታውቋል።

በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የዛሬ (ማክሰኞ መስከረም 26 ቀን 2013 ዓ.ም.) ውሳኔ መሠረት በትግራይ ክልል መንግሥት ላይ ሦስት ውሳኔዎች ያሳለፈ ሲሆን፤ ቀዳሚው ውሳኔው በኢ-ሕገ መንግሥታዊ ምርጫ ከተመሠረተው የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ከፍተኛ የሕግ አስፈጻሚ አካል ጋር የፌዴራል መንግሥት ምንም ዐይነት ግንኙነት የማያደርገ መኾኑ ነው።

ሁለተኛው የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ደግሞ፤ የትግራይ ሕዝብን የልማትና መሠረታዊ አገልግሎቶች ፍላጎት ማዕከል በማድረግ የከተማና የቀበሌ አስተዳደሮችን ጨምሮ በክልሉ ከሚገኙ ሕጋዊ ተቋማት ጋር ብቻ ግንኙነት ያደርጋል የሚል ነው።

የውሳኔውን አፈጻጸም በፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ እና ጉዳዩ በሚመለከታቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴ ክትትል እንዲደረግበት የሚለው ሦስተኛ ውሳኔ ተደርጎ ተቀምጧል።

በዚሁ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ላይ ማምሻውን ተጨማሪ መግለጫ የተሰጠ ሲሆን፤ ፌዴሬሽኑ የዛሬውን ውሳኔ ያስተላለፈው፤ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነኀሴ 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በተወሰነው መሠረት የትግራይ ክልል ምክር ቤት የሚያካሒደው ምርጫ ሕገወጥ መኾኑን በማሳወቅ ከዚህ እንዲታቀብ የተላለፈው ውሳኔ ሊያከብር ባለመቻሉ ጭምር ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ