የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ (በግራ) ለዘምዘም ባንክ ሥራ መጀመር የሚችልበትን ፍቃድ በሰጡበት ወቅት

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ (በግራ) ለዘምዘም ባንክ ሥራ መጀመር የሚችልበትን ፍቃድ በሰጡበት ወቅት

ብሔራዊ ባንክ ፍቃዱን አስረከበው
ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ የተፈረመ ካፒታል አሰባስቧል

ኢዛ (ሰኞ ጥቅምት ፪ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 12, 2020)፦ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሙሉ ለሙሉ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ሲንቀሳቀስ የቆየው ዘምዘም ባንክ ሥራ ለማስጀመር የሚያስችለውን ፍቃድ ዛሬ ሰኞ ጥቅምት 2 ቀን 2013 ዓ.ም. ከብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ ተረከበ።

ከ13 ዓመታት በላይ ብዙ ውጣ ውረድን በማለፍ ዛሬ ወደ ሥራ ለመግባት የሚያስችለውን ፍቃድ የተረከቡት የዘምዘም ባንክ አደራጅና ቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ናስር ዲኖ፤ የ13 ዓመታት ውጣ ውረዳቸውን በማሰብ እንባ የተቀላቀለ ደስታቸውን ገልጸዋል።

ዘምዘም ባንክ ከአንድ ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ብር በላይ የተፈረመ ካፒታልና ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የተከፈለ ካፒታል ይዞ ወደ ሥራ የሚገባ መኾኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት ከወለድ ነፃ ባንክና መደበኛውን የባንክ አገልግሎት ለመስጠት ለብሔራዊ ባንክ ፍቃድ ከጠየቁት ወደ 20 ከሚጠጉ ባንኮች ውስጥ የመጀመሪያው ለመኾን በቅቷል። የሥራ ማስጀመሪያ ፍቃዱ በተሰጠበት ወቅት እንደተገለጸውም ከለውጡ ወዲህ ወደ ሥራ ለመግባት ፍቃድ የተሰጠው ቀዳሚ ባንክ ሊኾን ችሏል።

ባንኩ ከ13 ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ለመስጠት እንቅስቃሴ ሲጀመር የወለድ አልባ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ሕግ ባይኖርም፤ ሕጉ እንደሚወጣ ቃል በመገባቱ፤ ዘምዘም ባንክ አክስዮኖችን ሽጦ ወደ ምሥረታ በሚገባበት ወቅት ራሱን የቻለ ወለድ አልባ ባንክ ማቋቋም አትችሉም ተብለው ያሰባሰቡትን አክሲዮን እንዲመልሱ አስገድዷቸዋል።

በወቅቱ በነበረው የመንግሥት አመራር ክልከላ የተደረገበት ከወለድ ነፃ የኾነ ባንክ ምሥረታ ሕግ እንዲወጣለት የተደረገው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደ ኃላፊነት ከመጡ በኋላ ነው።

የዛሬው ፕሮግራም ላይ ዶ/ር ይናገር ደሴ እና ዶ/ር ናስር ዲኖ ደጋግመው የገለጹትም፤ ከወለድ ነፃ ባንክ ራሱን ችሎ እንዲመሠረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኹነኛ ሚና እንደነበራቸው በመጥቀስ አመስግነዋቸዋል።

በእምነታቸው ምክንያት ወደ ባንክ መምጣት ያልቻሉ ዜጎችን ወደ ባንክ እንዲመጡና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ተብሎ የሚታመንበት ይህ እንዲህ ያለው ባንክ በአመዛኙ የእስልምና ተከታይ ዜጎችን ተገልጋይ ቢያደርግም፤ ባንኩ ሃይማኖት ሳይመርጥ የሚሠራ እንደኾነ ተገልጿል።

ዶ/ር ይናገር ደሴም ይህንኑ የጠቀሱ ሲሆን፤ ባንኩ በአዲሱ የብር ኖት አዲስ አገልግሎት ለመስጠት እድል ስለማግኘቱም አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት ባንክ ለመመሥረት ለብሔራዊ ባንክ ፍቃድ የጠየቁና ወደ ሥራ ለመግባት በተለያዩ ምዕራፍ ላይ ይገኛሉ ከተባሉ ባንኮች ውስጥ ወደ ስድስት የሚኾኑት ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት ለመስጠት የሚንቀሳቀሱ ናቸው።

መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ካለፉት አሥር ዓመታት ወዲህ በመስኮት ደረጃ ከወለድ ነፃ ባንክ አገልግሎት ባንኮች ቁጥር ከአሥር በላይ የደረሱ ሲሆን፤ በእነዚህ ባንኮች ከወለድ ነፃ የተቆጠበው የገንዘብ መጠን ከ60 ቢሊዮን ብር በላይ ደርሷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ