ኢትዮጵያ በታላቁ ህዳሴ አካባቢ የሲቪልም ኾነ ወታደራዊ በረራዎችን ከለከለች
የታላቁ ህዳሴ ግድብ
በዚያ አካባቢ ለመብረር ልዩ ፈቃድ መሰጠት እንዳለበት ተገልጿል
የመንግሥት እርምጃ የህዳሴውን ግድብ ድኅንነት ለመጠበቅ ነው
ኢዛ (ሰኞ መስከረም ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 5, 2020)፦ የታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚገኝበት የአየር ክልል፤ ከተፈቀደላቸው በረራዎች ውጭ ማንኛውም የሲቪልም ኾነ ወታደራዊ በረራዎች ዝግ መደረጉና መከልከሉ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪየሽን ባለሥልጣን ዛሬ ሰኞ መስከረም 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ይፋ እንዳደረገው፤ በታላቁ ህዳሴ ግድብ በሚገኝበት የኢትዮጵያ የአየር ክልል ለመብረር ከተፈለገ፤ ከባለሥልጣኑ ልዩ ፈቃድ ማግኘት ግዴታ ስለመኾኑም አስታውቋል።
የባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ ክብረአብ በዚህ ጉዳይ ላይ በሰጡት ማብራሪያ ከባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ልዩ ፈቃድ ያላገኘ ማንኛውም የሲቪልም ኾነ ወታደራዊ በረራ ማድረግ አይቻልም።
ኢትዮጵያ የወሰደችውን ይህንን የበረራ ክልከላ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚመለከተው አካል ሁሉ እንዲያውቀው መደረጉንም መረጃው አመልክቷል።
በመረጃው መሠረት መንግሥት ከዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው የግድቡን ድኅንነት ለማረጋገጥ ሲባል፤ ይህ ክልከላ ተግባራዊ እንደተደረገና ሌሎች አገሮችም ትላልቅ ፕሮጀክቶች በሚያከናውኑባቸው አካባቢዎች ተመሳሳይ እርምጃ የሚወሰድ መኾኑንም አስታውሷል። (ኢዛ)



