ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሱዳንና ከእስራኤል መሪዎች ጋር ውይይቱን በደረገጉበት ወቅት

ኢትዮጵያውያን በተጠንቀቅ እንዲቆሙ የሚያመላክት መግለጫ መንግሥት አውጥቷል
ኢትዮጵያውያን አቋማቸውን በተለያየ መንገድ እየገለጹ ነው

ኢዛ (ቅዳሜ ጥቅምት ፲፬ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. October 24, 2020)፦ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ግብጽ የታላቋ የህዳሴ ግድብን ያፈነዱታል በሚል ያስተላለፉት መልእክት ውዝግብ እየፈጠረ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ መንግሥትና ኢትዮጵያውያን ንግግሩን በመቃወም አቋማቸውን በተለያዩ መንገዶች እየገለጹ ነው።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ትራምፕ በግልጽ ለግብጽ ወገንተኝነታቸውን ያንጸባረቁበትንና ቁጣ የቀሰቀሰው የፕሬዝዳንት ትራምፕ ንግግር፤ ኢትዮጵያ ያካሔደችውን የውኃ ሙሌት ጭምር በመቃወም፤ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያላቸውን አመለካከት ጭምር ያንጸባረቁበት ሲሆን፤ ግብጽ ሕልውናዋ በመኾኑ ግድቡን ታፈነዳዋለች እስከማለት ደርሰዋል።

ትናንት በእስራኤልና በሱዳን መካከል የተደረገውን ስምምነት አስከትሎ ትራምፕ ካስተላለፉት መልእክት ውስጥ የታላቁን ህዳሴ ግድብ እንዲህ ባለው መልኩ መግለጻቸው፤ የኢትዮጵያ መንግሥትን በማስቆጣት የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የኢትዮጵያን አቋም የሚያንጸባርቅ መግለጫ ለማውጣት አስገድዶታል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና ሌሎች ታዋቂ ሰዎችም የትራምፕን ንግግር በማውገዝ መግለጫዎችን አከታትለው እያወጡ ሲሆን፤ በአገር ውስጥም ኾነ በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን የትራምፕን ንግግር በመቃወም ድምፃቸውን እያሰሙ ነው።

በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ዛሬ ረፋዱ ላይ ባወጣው መግለጫ፤ ኢትዮጵያ በፈጣሪዋ ታምና፣ በሕዝቧ አንድነትና ጽናት የቆመች አገር መኾንዋን አስታውቆ፤ ጥቂት ሰጥተው ብዙ ሊያዟት በሚሞክሩ ተማምና እንደማታውቅ በመግለጽ፤ ኢትዮጵያውያን በያሉበት 24 ሰዓት ለኢትዮጵያ እንዲቆሙ ጠይቋል። “ሕይወታቸውን ሰጥተው ሊታዘዟት በተዘጋጁ ልጆቿ እንጂ፤ ኢትዮጵያን የፈጠራት አምላኳ ነው። የገነቧት ደግሞ ልጆች ናቸው!” ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ፤ እነዚህ ልጆቿ በከፈሉት መሥዋዕትነት ዓለምን ጉድ ያሰኙ ታሪኮችን መሥራቷንና እነዚህን አስደናቂ ታሪኮችን ስትሠራ አብረዋት ታሪክ የሠሩ ወዳጆች ነበሯት። የከዷት ወዳጆችም ነበሩና ይህ ለኢትዮጵያ አዲስ አለመኾኑን አመላክቷል።

“ኢትዮጵያን ነክቶ በሰላም የኖረ የለም” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት መግለጫ፤ ኢትዮጵያን በአንድነት ለአንድ ዓላማ ከቆሙ ድል ማድረጋቸው አይቀርምና የህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ ግድብ መኾኑን አስታውሶ፤ ግድቡን ኢትዮጵያውያን አሰቡት፣ ኢትዮጵያውያን ጀመሩት፣ ኢትዮጵያውያን ገነቡት፤ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን የጀመሩትን የሚጨርሱ መኾኑንም ጠቁሟል።

“የሚያዋጣን ሕብረትና አንድነታችን ነው። ለእኛ ያለነው እኛ መኾናችንን አውቀን፤ ስለ እኛ ጉዳይ እኛው ራሳችን ኢትዮጵያን አለንሽ እንበላት። ኢትዮጵያውያን አንድ ኾነን ለኢትዮጵያ እንቁም። ከባዱ ፈተና ከውጭ የሚመጣው አይደለም። ከባዱ ፈተና ተለያይተን ችግሩን ከተጋፈጥነው ነው።” ያለው መግለጫ፤ በሕብረት ኢትዮጵያውያን እንዲነሱ ጥሪ አስተላልፏል።

በመግለጫው መጨረሻ ላይም ያቀድነውን ከማሳካት የሚያግደን ምድራዊ ኃይል ያለመኖሩንና አንድ ኾነን የምንይዘው ጋሻ ኃያላኑን ሁሉ ሲመክት የኖረ በመኾኑ፤ ዛሬም ያንን ጋሻ በአንድነት በማንሳት ሁላችንም፣ በየቦታችን፣ 24 ሰዓት፣ ለኢትዮጵያ እንቁም በማለት አስታውቋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት ቤት መግለጫ ከወጣ በኋላ፤ በቅርቡ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሕዝባዊ ተሳትፎ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር በመኾን የተሾሙት ዶክተር አረጋዊ በርሄ፤ የፕሬዝዳንቱ አስተያየት አሜሪካ ለግብጽ ያላትን ወገንተኝነት ዳግም በግልጽ ያሳየ መኾኑን በመግለጽ፤ የፕሬዝዳንቱ ንግግር ከአንድ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የሚጠበቅ ያለመኾኑንና ለግብጽ ያላቸውን ወገንተኝነት በግልጽ ያሳየ ነው ብለውታል። ይኼ ደግሞ የኾነው አገራቸው ከእስራኤል እና ከግብጽ ጋር ካላት ግንኙነት ጋር እንደሚያያዝም ተናግረዋል።

“ግድቡ የተጀመረውና እዚህ የደረሰው በሕዝብ ድጋፍ ነው፤ ዳር የሚደርሰውም በሕዝብ ድጋፍ ነው፤ አሁንም ከተባበርን ይኼን አይደለም ሌላ ግድብ መሥራት እንችላለን” በማለት ዶ/ር አረጋዊ፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለግድቡ ያለውን ድጋፍና ተሳትፎ በአግባቡ የተረዱ ያለመኾኑንም አስታውቀዋል።

በትራምፕ ንግግር ላይ አስተያየት የሰጡት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ “ኢትዮጵያውያን ኃላፊነት በጎደለው መግለጫ አንርበደበድም” በማለት የአሜሪካን ፕሬዝዳንትን ንግግር ኮንነዋል። ፕሬዝዳንት ትራምፕ ስለሚያወሩት ነገር መነሻ ግንዛቤ እንደሌላቸውም አቶ ኃይለማርያም በትዊተር ገጻቸው ላይ ጽፈዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤትም ኢትዮጵያ የህዳሴውን ግድብ ከማጠናቀቅ የሚመልሳት ያለመኖሩን አስታውቆ፤ የትራምፕን ንግግር ኮንኗል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃልአቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ኢትዮጵያ ለድርድር፣ ፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት እንደ ከዚህ ቀደሙ ትሠራለች፤ ከዚህ ውጪ በህዳሴ ግድቡ ላይ በማስፈራራሪያና በዛቻ የሚመጣ ለውጥ አይኖርም በማለት የመንግሥታቸውን አቋም አንጸባርቀዋል።

ኢትዮጵያ ሁሉን ተጠቃሚ ያደረገ ዲፕሎማሲያዊ ድርደር እንዲቀጥል አሁንም አቋሟ መኾኑን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ለአፍሪካዊ ጉዳዮች አፍሪካዊ መፍትሔዎች እንዲገኙ እንደሚሠራም ገልጸዋል። ኢትዮጵያ ጉዳዩን በሰላማዊና በዲፕሎማሲያዊ መንገድ በድርድር ለመፍታት፤ ሁሉንም በጋራ ተጠቃሚ ለማድረግ አሁንም መሥራቷን እንደምትቀጥል አስታውቀዋል።

የትራምፕ ንግግር ተቃውሞ እየገጠመው ያለው በኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፤ የኮሎራዶው ሴናተር ክሮው በትዊተር ገፃቸው እንዳስታወቁት የፕሬዝዳንት ትራምፕ “ግብጽ የህዳሴ ግድብን ልታጋይ ትችላለች” በማለት ያደረጉትን ንግግር፤ ከእርሳቸው የማይጠበቅ መኾኑን በመግለጽ፤ ንግግራቸውን ተቃውመዋል።

የፕሬዝዳንቱ ንግግር የግድቡን የወደፊት ዕጣ ፈንታ ከግንዛቤ ያላስገባ መኾኑን የገለጹት ሴናተሩ፤ ኢትዮጵያውያን እየሰጡ ካሉት አስተያየት ጋር ተመሳሳይ የኾነ ምልከታቸውን አስፍረዋል።

ሴናተሩ ኢትዮጵያ የአሜሪካ የረዥም ዘመናት የልብ ወዳጅ መኾኗንና አሜሪካ ስለ ህዳሴው ግድብ አደራዳሪ እንጂ የአድልዎ ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልጋትም ገልጸዋል።

ጉዳዩ በሰላማዊና ዲፕሎማሲያዊ መንገድ እንዲያልቅ መሥራት እንጂ፤ እርዳታን እናቋርጣለን በሚል ማስፈራሪያ መሸበብ እንደሌለበትም እኒሁ ሴናተር ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ ወገን እየላለፈው ያለው መልእክት ኢትዮጵያውያን በአንድነት ግድቡን ማጠናቀቅና በጋራ ዘብ መቆምን የሚያመላክት ነው።

ዶ/ር አረጋዊ በርሄ እንደገለጹትም በውስጥም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን ተባብረን ግድቡን ዳር ለማድረግ መፍትሔው በኢትዮጵያውያን እጅ መኾኑንና አሁን ካለውም በላይ ተባብረን በመሥራት ግድቡን ማስጨረስ ይኖርብናል ብለዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ