PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሙ አዋጁን የሚያስፈጽም ሲሆን፤ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ይኾናል

ኢዛ (ረቡዕ ጥቅምት ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 4, 2020)፦ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ረቡዕ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. ባካሔደው ልዩ ስብሰባ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ።

በትግራይ ክልል የታወጀው አዋጅ ለስድስት ወራት የሚቆይና አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም በጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሙ የሚመራ ኾኖ፤ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚኾን ታውቋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በመላው የትግራይ ክልል ተፈጻሚ የሚኾን ነው። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን በተመለከተ የወጣው ሙሉ መግለጫ የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

የኢፌድሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት በትግራይ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አወጀ

የኢፌድሪ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ጥቅምት 25/2013 ባደረገው 21ኛ አስቸኳይ ልዩ ስብሰባ መንግሥት የአገርን ሰላምና ሕልውና፣ የሕዝብንና የዜጎችን ደኅንነት የማረጋገጥ እና አገሪቷን ወደ ኹከትና ብጥብጥ የሚወስዱ ማናቸውንም ድርጊቶችን የመከላከል ሕገ መንግሥታዊ ኃላፊነት ያለበት መኾኑን በመገንዘብ፤ እንዲሁም በትግራይ ብሔራዊ ክልል ውስጥ ሕገ መንግሥቱንና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን እንዲሁም የሕዝብን ሰላምና ጽጥታ አደጋ ላይ የሚጥሉ በተለይም የአገርን ሉዓላዊነት የሚገዳደሩ፣ የፌደራል መንግሥት በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን ሥልጣንና ኃላፊነት በክልሉ እንዳይወጣ እና አገሪቷን የጦር አውድማ የሚያደርጉ፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎችን ጭምር በመጣስ በርካታ ሕገ ወጥ ተግባራት እየተፈጸሙ በመኾኑ፤ ይህን ሁኔታ በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የማይቻልበት ደረጃ ላይ መደረሱን በመረዳት፤ በሕገ መንግሥቱ በተደነገገው መሠረት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመጠበቅ ልዩ እርምጃዎችን መውሰድ የሚያስችል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመደንገግ እና ተግባራዊ በማድረግ ሁኔታውን በመቆጣጠር በአገሪቱ ሰላምና ሕልውና ላይ የተጋረጠውን አደጋ መከላከል አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ፤ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 93/1/ሀ መሠረት የሚከተለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ታውጆዋል።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ለስድስት ወራት ተፈጻሚ የሚኾን ሲሆን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን የሚያስፈጽም በኢፌድሪ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሰብሳቢነት የሚመራና አግባብነት ካላቸው አካላት የተወጣጡ አባላት ያሉት ግብረኃይል በዚህ አዋጅ ተቋቁሟል። ግብረኃይሉ ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲሆን፤ “የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ግብረኃይል” ተብሎ ይጠራል።አዋጁ በመላው የትግራይ ብሔራዊ ክልላዊ መስተዳድር ተፈጻሚ የሚደረግ ሲሆን፤ እንደያስፈላጊነቱ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ተፈጻሚ ወይም ቀሪ የሚኾንባቸውን ተጨማሪ አካባቢዎችነ ግብረኃይሉ በሚያወጣው በመመሪያ ይወስናል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን አስመልክቶ ዝርዝር መርጃዎች በየጊዜው ለሕብረተሰቡ የሚሰጡ ይኾናል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ