ጆ ባይደን

ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንና የአሜሪካ የእስካሁኑ የምርጫ ውጤት

በኢትዮጵያውያን ጥርስ የተነከሰባቸው ትራምፕ በትውልደ ኢትዮጵያውያን ጭምር ተቀጥተዋል

ኢዛ (ቅዳሜ ጥቅምት ፳፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 7, 2020)፦ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያውያንን በብርቱ ባስቆጣ ንግግራቸው የምናስታውሳቸውና ከጃንዋሪ በኋላ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የሚባሉት ዶናልድ ትራም በዴሞክራቱ እጩ ጆ ባይደን መሸነፋቸው እውን ኾነ።

ዛሬ ቅዳሜ ጥቅምት 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ከደቂቃዎች በፊት እንደ ሲኤንኤን ያሉ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ይፋ ባደረጉት መረጃ፤ ጆ ባይደን 46ኛው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ለመኾን የሚያስችላቸውን ድምፅ አግኝተዋል።

ጆ ባይደን ፕሬዝዳንት ለመኾን የሚያስችላቸውን 270 የኤሌክቶራል ድምፅ በማለፈ፤ ይህ ዜና በተጠናከረበት በአሁንዋ ደቂቃ 290 ኤሌክቶራል ድምፅ አግኝተዋል። ትራምፕ እስካሁን ያገኙት ድምፅ 214 ላይ እንደቆመ ነው።

ብዙ ውዝግቦችን እያስተናገደ ያለው የዘንድሮው የአሜሪካ ምርጫ፤ በፕሬዝዳንት ትራምፕ “ተጭበርብሯል” ብለው እስከማለት የደረሱበት፣ የድምፅ ቆጠራውን ለቀናት ያቆየ፤ አሁንም ያላለቀ መኾኑ ከዚህ ቀደሞቹ የአሜሪካ ምርጫዎች በተለየ እንዲታይ አድርጎታል።

የአሜሪካ የዘንድሮ ምርጫ በኢትዮጵያውያን ዘንድም ከሌላው ጊዜ በተለየ ትኩረት የተሰጠው ኾኗል። ለዚህም ዋናው ምክንያት ተሰናባቹ ፕሬዝዳንት ትራምፕ የታላቁ ህዳሴ ግድብን አስመልክቶ ፍጹም ለግብጽ ያደላ ንግግራቸው እንደነበር ይታወቃል። በተለይም ግብጽ የሕልውናዋ ጉዳይ በመኾኑ ግድቡን ታፈነዳዋለች በማለታቸው፤ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ጥርስ እንዲነከስባቸው አድርጓል። በዚህም “ምርጫው አይቅናዎ” ተብለዋል።

ይህም በተግባር ይፈጸም ዘንድ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ጆ ባይደንን በመምረጥ በጋራና በግል ሲንቀሳቀሱ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ አሁን ጥረታቸው መስመሩን ያረጋገጡበት ኾኗል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ