ኃይሌ ታደሰ

የአሜሪካ ምርጫ የዓለም የመገናኛ ብዙኀን ትልቁ አጀንዳ ሆኗል። የትኛውንም የቴሌቭዥን ጣቢያ ቢከፍቱ፣ የኦባማ ንግግር ወይም በየሀገሩ ካሉ የመራጮች ህዝብ ጭፈራና ሆታው ውጭ ምንም ማግኘት አይቻል። በመላ ዓለም ያሉ ራዲዮኖች፣ ጋዜጦች መጽሔቶች፣ ድረ-ገፆች ሁሉም ስለ ኦባማ መመረጥ ይተነትናሉ።

 

አሜሪካውያን ፕሬዝዳንታቸውን ያለምንም ፍርሃትና ሰቀቀን አደባባይ ላይ ተገኝተው በመረጡ ማግስት የምርጫቸውን ውጤት ሰምተው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት ሲለዋወጡ ማየት ምን ያህል አስደሳች እንደሆነ አብዛኞቻችን አይተናል፣ ሰምተናል።

 

የአሜሪካን ምርጫ ከክርክሩ ጀምሮ እጅግ አስገራሚ ነበር፤ ያለ አንዲት ስንጥር እንጨት መወራወር፣ ያለ አንዳች ሰቀቀን እና ፍርሃት ተቀናቃኛቸውን ለመጣል አለኝ የሚሉትን መረጃ በሙሉ እየተጠቀሙ፤ በንግግር ተቀጣቅጠዋል።

 

አሜሪካኖች እንደውም በቅስቀሳ ታሪካቸው እኛ ሀገር ቢሆን ”ያሰቅል ነበር” ልንላቸው የምንችላቸውን የምርጫ ቅስቀሳዎች ይጠቀሙ ነበር። አብዛኞች እንደሚሉት ባራክ ኦባማ ጨዋነት የተሞላበት የምርጫ ቅስቀሳን የሚወድ በመሆኑ፣ ከዝልልፍ የታቀበ ቅስቀሳ አካሂዷል።

 

እንደዛም ሆኖ ግን ከእጩዎቹ በተጨማሪ፣ ለምርጫው በርካታ አስተዋፆኦ ያበረከቱት ደጋፊዎቹ ነበሩ። በቴሌቭዥን፣ በሬዲዮ፣ በጋዜጦችና በኢንተርኔት ላይ በሚደረጉ ክርክሮች ታሪክ እየተማዘዙ ተዘላልፈዋል።

 

እጩዎቹና ደጋፊዎቻቸው ዘረኝነት ሊያንፀባርቅ ከሚችል ቅስቀሳ ብቻ ነበር የሚጠነቀቁት፤ ከምርጫው በኋላ ማንም ያሸንፍ ማን፣ በቅስቀሳው ወቅት ለሚያደርጓቸው ንግግሮች ቅንጣት ታክል ሥጋት አልገባቸውም።

 

በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻው፣ ዜግነታቸውን የቀየሩ የሌላ ሀገር ዜጎች ሳይቀሩ በጣም በርካታ አሜሪካውያን፣ ራሳቸውን በቡድን እያደራጁ በኢንተርኔትና በሌሎች ማንኛውም ዘዴ ተጠቅመው ቅስቀሳ አድርገዋል። በኦባማና በማኬይን ስም ሬስቶራንቶችና ካፌዎች ተከፍተዋል። እነዚህ ደጋፊዎች ግን ከምርጫው በኋላ የደገፉት እጩ ባይመረጥ፤ ፕሬዝዳንት ሆኖ የተመረጠው እጩ እሱን ከመረጡት ደጋፊዎች እኩል ሊያስተዳድራቸው፣ ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸውን ሊጠብቅላቸው ግዴታ አለበትና ሥጋት አይገባቸውም። ከምርጫው በኋላ ግብር ይጫንብኛል፣ ሆቴሌ ይዘጋል፣ እታሰራለሁ፣ ሰበብ ተፈልጐ እጎዳለሁ የሚሉ ሥጋቶች የሉባቸውም፤ በነፃነት ድጋፋቸውን ይሰጣሉ፣ በነፃነት ይመርጣሉ።

 

በ44ኛው የአሜሪካ ምርጫ 14 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ጥቁር በሆነበት አሜሪካ፤ አፍሪካ አሜሪካውያኑ ባራክ ኦባማ 349 ለ163 በሆነ የኤሌክቶራል ድምፅ አሸንፈው፣ የመጀመሪያው ጥቁር አሜሪካዊ ፕሬዝዳንት ሆነዋል።

 

የቅናቴ መነሻ ከዚህ ነው የሚጀምረው። ከ86 በመቶ በላይ የሚሆነው የአሜሪካ ህዝብ ነጭ በሆነበት አሜሪካ፤ የነጭ ዝርያ ያላቸውን ማኬይንን አሸንፎ ባራክ ኦባማ ተመርጧል። ባራክ ኦባማን ከመጀመሪያ ጀምሮ የነጮች ድጋፍ ባይኖረው ኖሮ ለእጩነትም ባልበቃ ነበር። ነጮቹ አሜሪካውያኖች ለአፍሪካውያንም ሆነ ለሌሎች የዓለም ህዝቦች ትልቅ ትምህርት አስተምረው አልፈዋል። ዘርና ቀለምን ወደ ጎን አድርገው፤ ይዞ የተነሳውን ሃሳብ እና እሱነቱን ብቻ መሠረት አድርገው ለሚደግፉት ድምፅ ሰጥተዋል።

 

ከምርጫው ውጤት በኋላ ለፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ቀድመው የስልክ የደስታ መግለጫ ያስተላለፉት ደግሞ ፕሬዝዳንት ጆርጅ ቡሽ ነበሩ ”… እኔና ባለቤቴ ወደ ቴክሳስ እንመለሳለን፣ እርሶና ባለቤትዎ ከሁለት ቆነጃጅት ሴት ልጆችዎ ጋር ሆነው ወደ ነጩ ቤት ያመራሉ። እንኳን ደስ ያሎት፣ አሁን ወጣ ብለው ራስዎን ያስደሰቱ …” ነበር ያሉዋቸው። እኔ የአሜሪካንን ምርጫ ከእኛዋ ኢትዮጵያ ጋር አላወዳድርም፤ ለማወዳደር የፈለገ ካለ ግን የግንቦት ሰባቱን የ97 ምርጫ ማግስት ማስታወስ ብቻ ነው።

 

ኮሮጆ ተሰረቀ የለ፣ ተጭበረበረ የለ፣ እስር የለ፣ ግድያ የለ፣ ዛቻ የለ፣ ፍርሃት የለ፣ ሁለት ጣቱን የቀሰረ … የለ፣ ሠላማዊ ሰልፍና መሰብሰብ መከልከል የለ፣ …። ምን አለፋችሁ ድምፁ ተቆጥሮ ሳያልቅ በውጤቱ መሸነፋቸውን ያወቁት የ72 ዓመቱ ሴናተር ጆን ማኬይን ለእንኳን ደስ አሎት መልዕክት ወደ መድረክ ብቅ አሉ።

 

”… የአሜሪካን ህዝብ ተናገረ፣ አዎ! የአሜሪካ ህዝብ በግልፅ ተናገረ፤ እንኳን ደስ አለህ፤ ቀጣዩ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ …” ማኬይንን ደጋፊዎቻቸው አልተቆጧቸውም፣ እሳቸውም ደጋፊዎቻቸውን አልፈሩም፣ ኦባማን ካልገደልን አላሉም፣ በጭብጨባ ድጋፍ ሰጧቸው።

 

ማኬይን በንግግራቸው ምርጫውን ታሪካዊ ነው አሉት ”ሴናተር ባራክ ኦባማ ለሱና ለሀገሩ ትልቅ ነገር አሳክቷል” ሲሉ አሞካሹት። መቼም የተፈጥሮ ጉዳይ ነውና በውጤቱ ዕለት ማታ ትንሽ መጥፎ ስሜት እንደተሰማቸው ገልፀው ”ግን ነገ ጥሩ እሆናለሁ፣ እኔና ደጋፊዎቻችን ከባራክ ኦባማ ጋር በጋራ ሆነን ለሀገራችን በሚገባ እንሠራለን” ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ከእንግዲህ ድጋፋቸውን ለኦባማ እንዲሰጡ መከሩ። ውጤቱን በፀጋ ተቀብለውም መድረኩን ለባራክ ኦባማ አስረክበው ወደ መጡበት ተመለሱ።

 

አሁንም እኔ ኃያሏን ሀገር ከሀገሬ ምርጫ ጋር አላወዳድርም፤ ”ሀገሬ ኃያል ባትሆንም ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አደርጋለሁ ስትል ከአሜሪካ እኩል አውጃለችና እኔ አወዳደራለሁ” ላለኝ ግን ለመረጃ ይረዳው ዘንድ የማውቀውን ምርጫ 97 ላስታውሰው እችላለሁ።

 

ከምርጫው ማግስት ጀምሮ ተጭበረበሩ የተባሉ 299 ድምፆች፣ ለሊቱን ሙሉ ተሰልፎ ድምፁን የሰጠው ህዝብ በማግስቱ ውጤቱን ሲጠብቅ፣ የተገኘውም ቢሆን ”ድንገት ንፋስ አምጥቶ የሰጣቸው ነው መባሉ”፣ ምርጫ ቦርድ የምርጫውን ውጤት ”አልደረሰም” እያለ ልብ አንጠልጣይ ፊልም ማድረጉ … በል እንግዲህ እያስታወስክ አወዳድረው። እኔ እነዚህ ሁሉ ነገሮች እየታወሱኝ ነው በሰው ሀገር ምርጫ መቅናቴ።

 

ባራክ ኦባማ አሸናፊ መሆኑን ካወቀ በኋላ፣ ከባለቤቱና ከሁለት ልጆቹ ጋር ድምፃቸውን በሰጡበትና ካሸነፍኩ ንግግር አደርግበታለሁ ብለው ቃል በገቡበት ቺካጎ፣ ወደ መድረክ ብቅ አሉ።

 

አሜሪካውያን ነፋሳቸው ዲሞክራሲ መሆኑን በህዝቡ ምላሽ መታየቱን ገለፁ። እናም ብዙም ንግግር ሳያበዙ በቀጥታ ስለተፎካካሪያቸው ማኬይን መናገር ጀመሩ ”ሴናተር ጆን ማኬይን ለሀገራቸው እስከ ደም ጠብታ አገልግለዋል። ሀገራቸውንም ወዳድ ናቸው” ሲሉ አሞኳሻቸው። ለምርጫው ቅስቀሳ የወረዱበትን ቂም ሳይዝ ”ለሀገራቸው ሲሉ ነው” ሲል ተረጎመላቸው ”እንኳን ደስ አለህም!” አላቸው።

 

ከቤተሰቦቹ ጀምሮ ለምርጫው ድጋፍ ያደረጉለትን በሙሉ አመሠገነ፤ የመረጠውንም ህዝብ አልረሳም ”ድምፃችሁን ባትሰጡኝ ዛሬ ማታ አሸናፊ አልሆንም ነበር” ሲል ምስጋናን ለገሰ። ከዚህ በኋላም ለአሜሪካ የጋራ ጥቅም፣ የህዝቡን ዕርዳታ እንደሚፈልግ ገለፀ ”ዕርዳታችሁን እፈልጋለሁ፤ እናም መሪያችሁ እሆናለሁ” (I need your help. And I will be your President, too) ብሎ ህዝቡን የሥልጣኑ ባለቤት አደረገው።

 

ተኩስ የለ፣ ግድያ የለ፣ ሞት የለ፣ ጩኸት የለ፣ እስር የለ፣ ፍርሃት የለ፣ ከሀገር መውጣት የለ … ምንም ክፉ ነገር የለም! ደስታ በአሜሪካ ምድር ሆነ! ዓለም በአሜሪካ ምርጫ ተደነቀ።

 

በሀገራቸው ይህን ዕድል ያላገኙ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ፣ አፍሪካ አሜሪካውያን የደስታው ተካፋይ ሆኑ፤ ይህን ዕድል ለሀገሩ ያልተመኘ ኢትዮጵያዊ ሊኖር እንደማይችል ብገምትም፤ የዕድሜዬን እኩሌታ ያገባደድኩት እኔ ግን መቼ እንደማገኘው ላላወኩት የአሜሪካ ዓይነት ምርጫ በቅናት ተቃጠልኩ።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ