PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

ድርድር ብሎ ነገር እንደማይታሰብ አረጋገጡ

ኢዛ (ማክሰኞ ኅዳር ፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 10, 2020)፦ ስግብግቡንና አረመኔውን የመቀሌ ጁንታ ለፍትሕ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት ሳያገኝ ለአፍታም ቢኾን አናርፍም ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ። ከጁንታው ጋር ምንም ዐይነት ድርድር እንደማይታሰብ አሳውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ ይህንን የገለጹት ማምሻውን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት ነው።

“ስግብግቡና አረመኔው የመቀሌ ጁንታ በሰሜን ኮማንድ አባላት ላይ ያደረሰውን ኢ-ሰብአዊ ግድያ፣ ግፍ እና በደል መቸውንም አንረሳውም” ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ የሕግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራው ሳይጠናቀቅ ከጁንታው ጋር ድርድር የማይታሰብ መኾኑን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከሰሞኑ በተደጋጋሚ እንደገለጹት፤ አሁን የተገባበት ጦርነት ሕግ የማስከበር ተግባር መኾኑ ሲገልጹ እንደነበር ይታወሳል። ድርድር በሚል እየቀረቡ ያሉ አንዳንድ ጥያቄዎች በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል አሁን ጊዜው ያለፈበትና የማይታሰብ መኾኑ አቋም የተወሰደበት ቢኾንም፤ መቀሌ የመሸገው ቡድን የድርድር ጥያቄ ይዞ ብቅ ማለቱ ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕግ የማስከበር እርምጃው ስግብግቡን የመቀሌ ጁንታ ለሕግ ተገዥ የማድረግና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ማስጠበቅ ስለመኾኑም በሰሞኑ መልእክቶቻቸው አስፍረዋል። እርምጃው ከማንም በላይ ሰፊውን የትግራይ ሕዝብ ተጠቃሚ የሚያደርግ ስለመኾኑም ገልጸው፤ መንግሥት የወሰደውን እርምጃ ተከትሎ ወንድምና እኅት ትግራዋያን ማንነታቸውን ያማከለ ለምንም ዐይነት ሕገወጥ ድርጊት ሰለባ እንዳይኾኑ የማድረግ ኃላፊነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ መኾን እንዳለበት ከአደራ ጭምር ማሳሰባቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ባስተላለፉት ተጨማሪ መረጃ ደግሞ፤ “የጁንታው ፀሐይ እየጠለቀች ነው። ይኼንን መርዶ ጁንታው በቁሙ ተረድቶታል። አሁን የሚይዘውን የሚጨብጠውን የሚያጣበት ጊዜ ነው። በጣዕር መንፈስ በየቦታው የመጨረሻውን የጥፋት ድግስ ይደግስ ይኾናል። ስለዚህም ሕዝቡ በንቃትና በተደራጀ መንገድ አካባቢውን እንዲጠብቅ አደራ እላለሁ።

“ከዚሁ ጋር በተያያዘ የትግራይ ተወላጅ የኾኑ ወገኖቻችን በየአካባቢያችን ምንም ዐይነት አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይደርስባቸው ሁላችንም የወንድሞቻችን ጠባቂ እንሁን። የኢትዮጵያ ጠላት ስግብግቡ ጁንታ ነው። የትግራይ ሕዝብ እንደሌላው ሕዝብ በጁንታው መከራ ያየ ሕዝብ ነው። ጁንታው ለፍርድ እንዲቀርብ የትግራይም ሕዝብ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር አብሮ እየተዋጋ ነው። አካባቢዬን እጠብቃለሁ፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ የመከራ ቀንበር እሰብራለሁ። ጁንታውን ለፍርድ አቀርባለሁ - ይህ ነው ቃል ኪዳናችን” ብለዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ