Gen. Mohammed Tesema and Gen. Berhanu Jula

የኢንዶክትሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄኔራል መሐመድ ተሰማ (ግራ) እና አዲሱ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ (ቀኝ)

“በከሃዲው ሕወሓት እጅ ያሉ ከባድ መሣሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ወድመዋል” ኤታማዦር ሹሙ ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ

ኢዛ (እሁድ ጥቅምት ፳፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 8, 2020)፦ የመከላከያ ሠራዊት የሑመራ ሱዳን መንገድን ጨምሮ ማይዳሊ፣ ደንሻ፣ ባዕከር፣ ልጉዲ፣ የሑመራ አውሮፕላን ማረፊያን መቆጣጠሩንና በምዕራብ ግንባር እያደረገ ያለውን ጥቃት መቀጠሉን የመከላከያ ኢንዶክትሬሽን አስታወቀ።

የኢንዶክትሬሽኑ ዋና ዳይሬክተር ሜ/ጄኔራል መሐመድ ተሰማ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በእነዚህ አካባቢዎች የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥቃቱን ቀጥሏል።

አሁን ማምሻውን ከሰጡት መረጃ ቀደም ብሎ በሰጡት መግለጫም፤ ሠራዊቱ አገርን ከጥፋት የማዳን ተልዕኮውን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚያጠናቅቅ ገልጸዋል።

አሁን የተገባበትን ውጊያ ለመመከት መላው የጸጥታ ኃይል በመዋጋት ወንጀለኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብ ፍልሚያ ላይ ነን ብለዋል።

አዲሱ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ብርሃኑ ጁላ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት መግለጫ ደግሞ፤ “ሠራዊቱ ደንሻንና ባኮርን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ ወደ ሽሬ እየገሰገሰ ነው” ብለዋል።

በከሃዲው ሕወሓት እጅ ያሉ ከባድ መሣሪያዎችን ሙሉ በሙሉ ማውደሙን የገለጹት ጄኔራል ብርሃኑ፤ እንደተምች በየቦታው ሠራዊቱን የከበበውን ኃይል እያራገፈ መኾኑን ገልጸዋል።

ከሃዲ ቡድኑንም በመደምሰስ የሕግ የበላይነትና ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ለማረጋገጥ በብቃት እየተሠራ መኾኑንም ጄኔራሉ አመልክተዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ