The Ethiopian Human Rights Commission (EHRC)

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)

የማይካድራው ጭፍጨፋ የግፍና የጭካኔ ወንጀል መኾኑን ኢሰመኮ ይፋ አደረገ
ጨፍጫፊዎቹ ለይተው ያጠቁት “አማራ” እና “ወልቃይቴዎች” ያሉዋቸውን ነው

ኢዛ (ማክሰኞ ኅዳር ፲፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 24, 2020)፦ በትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን በምትገኘው የማይካድራ ከተማ በሲቪል ሰዎች ላይ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ሕይወታቸውን ያጡት ዜጎች ከ600 በላይ መኾናቸውንና ድርጊቱ የግፍና ጭካኔ ወንጀል መኾኑን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ማክሰኞ ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም. ባወጣው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት አስታወቀ።

ኮሚሽኑ በማይካድራ ከተማ ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም. የተፈጸመው ጭፍጨፋ በወቅቱ በሥልጣን ላይ በነበረው የአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና ሳምሪ በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን የተፈጸመ ነው።

ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ሊኾን እንደሚችልም አስታውቋል። ጭፍጨፋውን የፈጸሙት አካላት “አማሮች” እና “ወልቃይቴዎች” ያሉዋቸውን የጥቃቱ ሰለባዎች ያደረጓቸው መኾኑንም ሪፖርቱ ጠቅሷል። ጨፍጫፊዎቹ አማራ እና ወልቃይት የኾኑትን የአካባቢውን ነዋሪዎች ከቤት ቤት እየዞሩና በየጐዳናው ላይ በገመድ በማነቅ፣ በስለት፣ በመጥረቢያ፣ በዱላ በመደብደብ መግደላቸውን፤ የአካል ጉዳት ማድረሳቸውን፤ እንዲሁም ንብረት ማውደማቸውን ኢሰመኮ በዛሬው የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ገልጿል፡፡

ኮሚሽኑ ከኅዳር 5 ቀን እስከ ኅዳር 9 ቀን 2013 ዓ.ም. በቦታው ተገኝቶ መኾኑንና ሪፖርቱን ያሰባሰበ በማይካድራ፣ በአብርሀጅራ፣ በሳንጃ፣ በዳንሻ፣ በሑመራ እና በጐንደር ከተማ ተዘዋውሮ ያደረገውን ምርመራና የደረሰበትን ውጤት በተመለከተ ኮሚሽኑ ያዘጋጀውን የመጀመሪያ ደረጃ (ቀዳሚ) ሪፖርት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ