ሌተናል ጄኔራል ሐሰን ኢብራሒም

የመከላከያ ሠራዊት ሕብረት ሥልጠና ዋና መምሪያ ሌተናል ጄኔራል ሐሰን ኢብራሒም (ፎቶ፣ ስክሪንሾት ከኢዜአ)

ሠራዊቱ መቀሌን ለመቆጣጠር ስትራቴጂክ ቦታ ይዟል
በሁሉም ግንባር ሠራዊቱ ድል ማድረጉንና የቀረው መቀሌ ብቻ ነው

ኢዛ (ዓርብ ኅዳር ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. November 27, 2020)፦ የአገር መከላከያ ሠራዊት መቀሌን እና የወንጀለኛውን ጁንታ ቡድን አባላት ለመቆጣጠር የሚያስችሉትን ስትራቴጂክ ቦታዎችን መያዙንና በጥቂት ቀናት ውስጥ የጁንታውን አባላት ለሕግ የሚያቀርቡ መኾኑን ሌተናል ጄኔራል ሐሰን ኢብራሒም አስታወቁ።

የመከላከያ ሠራዊት ሕብረት ሥልጠና ዋና መምሪያ ሌተናል ጄኔራል ሐሰን ኢብራሒም ዛሬ ዓርብ ኅዳር 18 ቀን 2013 ዓ.ም. ማምሻውን በሰጡት መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት አብዛኛውን የትግራይ ክልል የተቆጣጠረ ሲሆን፤ አሁን የቀረው መቀሌ ብቻ መኾኑን ጠቁመው፤ መቀሌንም ለመቆጣጠር ስትራቴጂክ የኾኑ ቦታዎችን ሠራዊቱ መቆጣጠሩን አመልክተዋል።

የአገር መከላከያ ሠራዊት ሐውዜን፣ አልነጃሺ፣ አዲቀየህ፣ ማይመሳኖን እና ውቅሮን ከጁንታው ኃይል መሉ ለሙሉ ነፃ ማድረጉንም አመልክተዋል።

እስካሁን የተካሔደው ሕግ የማስከበሩ ሥራ ውጤታማ መኾኑን የገለጹት ሌተናል ጄኔራል ሐሰን፤ በአድዋ ግንባር የተንቀሳቀሰው ሠራዊት ሐውዜን፣ አብርሃ ወአጽበሃንና ውቅሮን በግማሽ ቀን መቆጣጠሩንም ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት በመቀሌ አቅራቢያ ወደሚገኘው መሶበ ተራራ እየገሰገሰ በመኾኑ፤ መቀሌን በጥቂት ቀናት ውስጥ ለመቆጣጠር የሚያስችል መኾኑን ኃላፊው ከሰጡት ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል።

የጁንታው ታጣቂ ኃይል በየግንባሩ ድል ስለመነሳቱ፤ በተለያየ መንገድ ያስረዱት ሌተናል ጄኔራል ሐሰን፤ የትግራይ ሕዝብ ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ ለመከላከያ ሠራዊቱ ወገንተኝነቱን እያሳየ መኾኑንም አክለው አስረድተዋል።

የጁንታው ቡድን በፕሮፓጋንዳ ጭምር እያፈገፈገ መሔዱ ሽንፈቱን ያረጋገጠ ስለመኾኑም በዛሬው መግለጫ ላይ ተጠቅሷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!