አማራ ባንክ

የአማራ ባንክ ምሥረታ በአዲስ አበባ ጎልፍ ክለብ፣ እሁድ የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. (ፎቶ፣ ኢዛ)

በ5.9 ቢሊዮን ብር ካፒታል ወደ ሥራ የሚገባ የመጀመሪያው ባንክ ይኾናል

ከተከፈለው ካፒታል 20 በመቶው የተሸጠው በአማራ ክልል ሲሆን፣ 50% በአዲስ አበባ፤ ቀሪው 30% በተለያዩ ክልሎች ነው

ኢዛ (እሁድ የካቲት ፳፩ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. February 28, 2021)፦ በኢትዮጵያ ከፍተኛውን የተከፈለ ካፒታል እና ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ባለአክሲዮኖች በመያዝ የመጀመሪያው የሚኾነው የአማራ ባንክ ባለአክሲዮኖች ምሥረታ ዛሬ እሁድ የካቲት 21 ቀን 2013 ዓ.ም. እውን ኾኗል።

ይህንን ዜና ባጠናከርንበትና ባሰራጨንበት ሰዓት፤ የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበር ምሥረታ በአዲስ አበባ ጎልፍ ክለብ እየተደረገ ሲሆን፤ ባንኩ እስካሁን 7.9 ቢሊዮን ብር ቃል የተገባ እና 5.9 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ይዞ ወደ ሥራ እንደሚገባ ታውቋል።

የባንኩ የባለአክሲዮኖች ቁጥርም 188 ሺህ ያደረሰው የአማራ ባንክ ምሥረታ ጉባዔውን በውክልና በአሁኑ ወቅት እያደረገ ይገኛል።

የአማራ ባንክ አክሲዮን ማኅበርን በሥራ ላይ ካሉትም ኾነ በምሥረታ ላይ ከሚገኙ ባንኮች ከሚለይባቸው መካከል አንዱ በአምሥት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ወደ ሥራ የሚገባ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የአክሲዮን ኩባንያዎች ታሪክም 188 ሺህ ባለአክሲዮኖችን የያዘ ኩባንያ በመኾኑ ነው።

በቀድሞው የገቢዎች ሚኒስትር አቶ መላኩ ፈንታ ቦርድ ሊቀመንበር እየተመራ ምሥረታ ጉባዔው ላይ የደረሰው የአማራ ባንክ፤ ከዛሬው የምሥረታ ጉባዔው በኋላ በአጭር ጊዜ ወደ ሥራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ባንክ ለመቋቋም የሚጠየቀው 500 ሚሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል መኾኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መመሪያ ያመላክታል። እስካሁን የተመሠረቱትም ኾነ በምሥረታ ላይ ያሉ ባንኮች አማራ ባንክ ይዞት የተነሳውን ያህል ካፒታል ይዞ የተነሳ ባንክ የለም። በቅርቡ ምሥረታ ያደረጉ ባንኮች ከፍተኛ የተከፈለ ካፒታላቸው ከ800 ሚሊዮን ብር ያነሰ ነው። ይህ የአማራ ባንክ የተከፈለ ካፒታል አሁን በሥራ ላይ ካሉ ባንኮች ካላቸው ካፒታል የበለጠ ነው።

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያሉት 16 የግል ባንኮች የባለአክሲዮኖች ድምር ቁጥር ከ150 ሺህ በታች ሲሆን፤ የአማራ ባንክ ግን 188 ሺህ መኾኑ ባንኩን ለየት አድርጎታል። ባንኩ ከሰበሰበው ጠቅላላ ካፒታል (5.9 ቢሊዮን ብር) ውስጥ የክሲዮኑን ሽያጭ የገዙት ባለአክሲዮኖች 50 በመቶ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ናቸው። 20 በመቶ የሚኾኑት በአማራ ክልል የሚኖሩ ሲሆን፤ ቀሪዎቹ 30 በመቶ የሚኾኑት ደግሞ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሚኖሩ መኾናቸው ታውቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ