የኮሮና ወረርሽኝ በኢትዮጵያ አደገኛ እየኾነ ነው

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ የሁኔታ መግለጫ (ሐሙስ መጋቢት 9 ቀን 2013 ዓ.ም.፤ በጤና ሚኒስቴር እና በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት የተዘጋጀ)
እስካሁን ባልታየ ሁኔታ በአንድ ቀን 2,057 ሰዎች በቫይረሱ ተያዙ
ከመቶ ተመርማሪዎች 26 ሰዎች ተይዘዋል
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 18, 2021)፦ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) በኢትዮጵያ መገኘቱ ከተገለጸ ወዲህ ከፍተኛ የተባለው እና በ24 ሰዓት 2,057 ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸውን የሚያመለክት ሪፖርት ይፋ ኾነ።
የጤና ሚኒስቴር ማምሻውን ይፋ ባደረገው መረጃ በሃያ አራት ሰዓት ውስጥ 8,055 ሰዎች ተመርምረው፤ 2,057 ሰዎች ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።
ይህ በ24 ሰዓታት ውስጥ የተመዘገበው የቫይረሱ ተጠቂዎች ከተመረመሩት አንጻር 25.5 በመቶው ተጠቂዎች ኾነው መገኘታቸውን ያመለክታል።
ከ100 ተመርማሪዎች 26 ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው መኾኑን የሚያሳይ እና የቫይረሱ ሥርጭት አደገኛ የሚባል ደረጃ ላይ መድረሱን አመላካች ኾኗል።
እስካሁን ይህንን ያህል ቁጥር ያለው የቫይረሱ ተጠቂ በአንድ ቀን የተገኘበት ጊዜ ያልነበረ በመኾኑ፤ ሁኔታውን አሳሳቢ አድርጎታል። (ኢዛ)