ኤርትራ ሠራዊቷን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት ተስማማች

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ (ግ) እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ (ቀ)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ወዲያውኑ ተክቶ የድንበር አካባቢዎችን ይጠብቃል
ኢዛ (ዓርብ መጋቢት ፲፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 26, 2021)፦ ትናንት ወደ አስመራ ለይፋዊ የሥራ ጉብኝት የተጓዙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፣ ከአቻቸው የኤርትራው ፕሬዝዳንት ጋር ባደረጉት ውይይት፤ ኤርትራ ሠራዊቷን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት መስማማትዋን ዛሬ አስታወቁ።
የሕወሓት ቡድን የመከላከያን የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቅምት 25 ቀን 2013 ዓ.ም. የመከላከያ ሠራዊቱ በተኛበት ከመግደል ጀምሮ አስከፊና አሰቃቂ ጥቃት ከፈጸመበት በኋላ፤ በባሕር ዳር እና በኤርትራ ላይ ሮኬቶችን ሲተኩስ እንደነበር አይዘነጋም።
ይህንን ተከትሎ “የኤርትራን መንግሥት የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ በመግባት ከተጨማሪ ጥቃቶች ራሱን እንዲከላከል እና ብሔራዊ ደኅንነቱን እንዲጠብቅ አነሳስቶታል” ሲሉ የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ትናንት መጋቢት 16 ቀን ወደ አስመራ ተጉዘው፤ ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ባደረጉት ውይይት የኤርትራ መንግሥት ጦሩን ከኢትዮጵያ ድንበር ለማስወጣት መስማማቱን በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል። አክለውም “የኢትዮጵያ ብሔራዊ የመከላከያ ሠራዊት ወዲያውኑ ተክቶ የድንበር አካባቢዎችን ይጠብቃል” ብለዋል።
ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በዚሁ መልእክታቸው ላይ፤ “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በሁለትዮሽ ግንኙነታቸው እና በኢኮኖሚ ትብብር ፍላጎታቸው ላይ አብረው መሥራታቸውን አጠናክረው ይቀጥላሉ። በ2010 ዓ.ም. በተጀመረው መሠረት በሁለቱ አገራት መካከል በመተማመን መንፈስ መልካም የጉርብትና ግንኙነታችንን መገንባታችንን እንቀጥላለን። በተለይም፣ በትግራይ ክልል እና ከድንበር ማዶ ባሉ ኤርትራውያን ወገኖቻችን መካከል በመተማመን ላየ የተመሠረተ ግንኙነትን መመለስ በእጅጉ ያስፈልጋል።” በማለት አስፍረዋል። (ኢዛ)