ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስመራ ናቸው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ (ግ) እና ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ (ቀ)
የኤርትራ ወታደሮች በትግራይ ፈጽመዋቸዋል በተባሉ ጥቃቶችና በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ስላለው የኤርትራ ሠራዊት ይወያያሉ ተብሎ ተገምቷል
ኢዛ (ሐሙስ መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. March 25, 2021)፦ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ ጋር ለመምከር ወደ አስመራ ማቅናታቸው ተሰማ። በሕወሓት እና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ይህ የመጀመሪያው ኦፊሴላዊ ጉብኝታቸው ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አስመራ ማቅናታቸው የተሰማው ዛሬ ሐሙስ መጋቢት 16 ቀን 2013 ዓ.ም. ሲሆን፤ የሁለት ቀን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት እንደሚያደርጉ ታውቋል። የጉዟቸው ዓላማ ግን እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።
ኾኖም በትግራይ ከሕግ ማስከበር ዘመቻው ጋር ተያይዞ በትግራይ በኤርትራ ወታደሮች ተፈጸሙ የተባሉ ጥቃቶችን፣ ኢትዮጵያ ድንበር ውስጥ ስላለው የኤርትራ ሠራዊት እና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር የተያያዘ ሊኾን እንደሚችል ተገምቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ፤ ከሁለት ቀናት በፊት ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን በፓርላማ ተገኝተው በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከፓርላማ አባላት ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ፤ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ መኖራቸውን አስመልክተው ማብራሪያ ሰጥተው ነበር። በእነዚህ ወታደሮች እና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ የሁለቱ አገሮች ባለሥልጣናት ሲመክሩበት እንደቆዩ፤ በቀጣይም ይኸው ውይይት እንደሚቀጥል አስታውቀው እንደነበር መዘገባችን አይዘነጋም። (ኢዛ)