PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

“ጁንታው ሕፃናትና ወጣቶችን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል” ዶ/ር ዐቢይ

ኢዛ (ረቡዕ ሐምሌ ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 14, 2021)፦ “ጁንታው የኢትዮጵያ ሕልውና ቀንደኛ ጠላት መኾኑን ደግሞ እያስመሰከረ ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ በሰጡት መግለጫ አስታወቁ። ጁንታው ሕፃናትና ወጣቶችን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል ሲሉም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 7 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፤ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ፕሮፓጋንዳቸውን አቀዳጅተው እየሠሩ መኾኑን አመልክተው፤ ሕዝቡ የመከላከያ ሠራዊቱን በመደገፍ የውጭውን ጫና እና የውስጡን ትንኮሳ እንዲቀለብስ ጥሪ አቅርበዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የዛሬው መልእክታቸው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)

ጠቅላይ ሚኒስር ዐቢይ አሕመድ ሕዝቡ የመከላከያ ሠራዊቱን በመደገፍ የውጪውን ጫና እና የውስጡን ትንኮሳ እንዲመክት ይቀረቡት ጥሪ

ለትግራይ ሕዝብ ያለንን ሐሳብ፤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለንን ቦታ ለመጨረሻ ጊዜ አሳይተናል። ግጭት ላለማባባስ፣ ለሕዝቡ የእርሻ ወቅት ፋታ ለመስጠት እንዲሁም የእርዳታ አቅርቦቱ ያለ ሰበብ እንዲከናወን ስንል በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም አድርገናል። ሰላም የተወሰነ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ብናውቅም ይህ ግን የመጨረሻ ሰላማዊ እድል ነው።

“ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ” እንደሚባለው፤ ጁንታው የሰላም መንገድ ሊዋጥለት አልቻለም። አሁን ባለው ቁመናው ያለ ግጭት ውሎ ማደር አይችልም። ሕፃናትና ወጣቶችን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል። የመከላከያ ሠራዊቱ እነዚህን ሕፃናት ወታደሮች የመታደግ ሞራላዊ ግዴታ ወድቆበታል።

ለሕዝባችን ስንል የከፈልነው ዋጋ ባልገባቸው ደካሞች ምክንያት ውጤት አላመጣም። ጁንታው የኢትዮጵያ ሕልውና ቀንደኛ ጠላት መኾኑን ደግሞ እያስመሰከረ ነው። ይሄንንም መላ ሕዝባችንን አስተባብረን እንቀለብሰዋለን። በአንድ በኩል ሰብአዊ እርዳታ እንዲቀላጠፍ እየሠራን፤ በሌላ በኩል የውጭና የውስጥ ጠላቶች ተናበው የከፈቱብንን ጥቃት መክተን እንቀለብሰዋለን።

ጁንታው ዋሻ ውስጥ ገብቶ ሕዝቡ በረሃብ ሊያልቅ ነው እያለ ሲያላዝን ነበር። ለሕዝቡ ሲባል ሰብአዊ የተኩስ አቁም ሲደረግ ደግሞ የረሃቡን አጀንዳ ትቶ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም ጀመረ።

ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለ እርዳታና ስለ ረሃብ ሲናገር መቆየቱን ዘንግቶ፤ ጁንታው ሕፃናትን ሲያሰልፍ እንኳን ዝምታን መርጧል። የእርዳታ መግቢያ ኮሪደሮችን የግጭት ቦታዎች ሲያደርጋቸው የእርዳታ ድርጅቶች አሁንም መንግሥትን ለመውቀስ ይቃጣቸዋል። እነዚህን ሁሉ ከግምት በማስገባት፤ መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ነገር በተገቢው መንገድ ያደርጋል።

ሕዝባችን ከሐሰተኛ መረጃዎች እና ከጠላት ፕሮፓጋንዳ ራሱን እንዲጠብቅ አሁንም ለማሳሰብ እንወዳለን። ጁንታውና አጋሮቹ ያላቸው ዐቅም ውሸትን መፈብረክ ብቻ ነውና። የውስጥና የውጭ ኃይሎች ፕሮፓጋንዳቸውን አቀናጅተው ሕዝብን ለመከፋፈል እየሠሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ሕዝባችን እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ እንደ አንድ ሠራዊት ኾኖ ለአገሩ ሕልውና በመቆም፣ የመከላከያ ሠራዊቱን በሁሉም ነገር በመደገፍ፣ የውጪውን ጫና እና የውስጡን ትንኮሳ እንዲመክትና እንዲቀለብስ ጥሪ እናቀርባለን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራና ተከብራ ለዘላለም ትኑር!!
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ሐምሌ 7 ቀን 2013 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ