በምርጫ ዋዜማ - ከ“ተንቤን” እስከ ”ዓዲሓ”
ጽዮን ግርማ - ከተንቤን
በአገሪቱ ቀደም ሲል የተከናወኑት ሦስት ምርጫዎች፤ የትግራይ ህዝብ ከህወሓት ፓርቲ ሌላ እንዲመርጥ ዕድል ሳይሰጡት አልፈዋል። ህወሓት በትግራይ ብቻውን ይወዳደራል፤ ብቻውን ያሸንፋል። የዘንድሮ ምርጫ ግን ይህን ልማድ ገፎ የጣለው ይመስላል፤ ዐረና መድረክ እና አንድነት መድረክ ዕጩዎቻቸውን ወደ ትግራይ ልከዋል።
በምርጫው ዋዜማ የማለዳው የመቀሌ ከተማ አውቶብስ መናኸሪያ በከባድ ፍተሻ ተቀበለኝ። ... ኢቢአዲ ... ኢቢአዲ ... እያሉ የሚጣሩ ረዳቶችን ተከትዬ ወደጠቆሙኝ አይሱዙ ገባሁ። መጨረሻው ወንበር አካባቢ አንድ ባዶ ቦታ አገኘሁ እና ተቀመጥኩ። በአንደኛው ወንበር ላይ ሻንጣዋን ለምልክት የተወች አንዲት ሴት መጥታ ከጎኔ ቦታዋን ያዘች። ጥቂት ቆይቶ መኪናው የቆላ ተምቤንን መንገድ ተያያዘው። አብዛኛው መንገደኛ ጨዋታውን ገታ አድርጐ በየወንበሩ ላይ ደገፍ እያለ እንቅልፉን መለጠጥ ጀመረ።
እኔም መጽሐፌን አውጥቼ ንባቤን ተያያዝኩት። ጥቂት ቆይቶ በነጭ አቧራ የታጀበው የ”ተንቤን” መንገድ ያነጥረኝ ገባ። እንኳን ለማንበብ፤ ተረጋግቼ ተቀምጬ ለመጓዝ እንኳን ከበደኝ። ዞር ዞር ብዬ መንገደኛውን ቃኘሁ። መንገዱን ተላምዶታል መሰለኝ ግማሹ እንደተኛ ነው። ሌላው ደግሞ የራሱን ጨዋታ ይዟል።
”እዚህ ወንበር ላይ ሽንኩርት በማዳበሪያ አስቀምጬ ነበር አይተሻል? ...” ከጐኔ የተቀመጠችው ሴት ድንገት ጠየቀችኝ። እስካሁን ቆይታ እንዴት ትጠይቀኛለች ስል ግራ ተጋባሁ፤ ተደናገጥኩም። ”ኧረ አላየሁም” አልኳት፤ ጮክ ብላ በትግርኛ የኾነ ነገር ተናገረች።
ከፊት ለፊታችን የተቀመጠው ወጣት ምን እንዳላት ባላውቅም ንግግሩ ቁጣን ያዘለ ነበር። በስተቀኝ ባለው መቀመጫ የተቀመጡትም እንዲሁ። ወደኔ መለስ አለችና ... አንቺ እዚህ ከመቀመጥሽ በፊት አንዲት ሴት ተቀምጠው ነበር፣ ’ገንዘብ የለኝም እወርዳለሁ’ ሲሉ ነበር፤ እሳቸው ይዘውት ወርደው ይሆናል፤ ስለምናቃቸው ቤታቸውን እናሳይሻለን ነው የሚሉኝ ... አለችኝ፤ ትንሽ ተረጋጋሁ።
ጥቂት ቆየችና ”ለምንድነው ወደ አቢአዲ የምትሄጅው?” ስትል ጠየቀችኝ ”ባለቤቴን ልጠይቅ” ዋሸኋት። ”ምርጫ አትመርጪማ?” አለች፤ ሥራዬን እንደቀማችኝ ቢሰማኝም አማራጭ ያለኝ አልመሰለኝም። ... መጀመሪያውኑ የምርጫ ካርድ ስላልወሰድኩ እዚህ ባልመጣም መምረጥ አልችልም ነበር ... አልኳት። ምርጫውን፣ የሚመለከቱ በርካታ ጥያቄዎችን ሰነዘረችልኝ፤ መመለስ ባለብኝ መንገድ መለስኩላት።
ከተጠያቂነት ወደ ጠያቂነት የሚያሸጋግረኝን ርዕስ ፈልጌ ስለትግራይ ምርጫ ጠየኳት። ጥርት ባለ አማርኛ ኢህአዲግ ስላደረገው ሰፊ ቅስቀሳ አወጋችኝ፤ ”... የትግራይ ህዝብ የረጅም ጊዜ ታሪኩ ጦርነት ነው። ህዝቡ ከትግሉ ውጤት በኋላ ልማት ነበር የጠበቀው። የጠበቀውን አላገኘም። የተንቤንን መንገድ እንደምታይው ነው። ከተማው ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ደግሞ ታይዋለሽ። ሌሎች የትግራይ ከተሞችም ቢኾኑ መንገድ የተሠራላቸው ጥቂት ናቸው።
”በትምህርት በኩልም ትግራይ ክልል ሁል ጊዜ ከሌሎች ክልሎች የመጨረሻው ነው። አብዛኛውን ጊዜ መቀሌ ውስጥ ውሃ የለ። ህዝቡ አማራጭ አጥቶ ነው እንጂ ለውጥ ይፈልጋል። ... ትግራይ ... አዲስ አበባ ላይ ተቀምጠው ሲያወሯት ብቻ ነው የምታምረው፤ ለህዝቡ የተረፈው ጥላቻ ብቻ ነው። እንደፈለገው በሌላ ቦታ ሄዶ እንዳይሠራ የሞራል ነፃነት አጥቷል፤ ትግሉ የተደረገው ለነፃነት ነበር፤ ግን እኛ ነፃነት አላገኘንም ...” አለች ተስፋ በቆረጠ ስሜት።
”ህዝቡ ምን ይላል?” አልኳት ”... ዋይ! የትግራይ ህዝብ የውስጡን አይናገርም። ምናልባት በጣም የሚተማመን እና ቤተሰብ ካልኾነ በስተቀር እርስ በርስ እንኳን አይወያይም፤ በዝምታ ተውጧል ...” አለችኝ።
የመቀሌ ልጅ መኾኗን እና አቢያዲ ውስጥ በመምህርነት ሥራ እንደምታገለግል እያወራችኝ አቧራማውን የተንቤን መንገድ ለሦስት ሰዓት ያህል ተጉዘን አቢያዲ ደረስን።
የቆላ ተንቤን ቆይታዬ
ወደ ተንቤን የሄድኩት በትጥቅ ትግሉ ወቅት ትልቅ ታሪክ ስላላቸው የመከላከያ ሚኒስቴር የቀድሞው ሚኒስትር የአቶ ስየ አብርሃን የምርጫ ሁኔታ ለመዘገብ ነበር። ቀደም ሲል በስልክ መረጃ ስለዋወጠው ለነበረው ለዐረና ትግራይ ፀሐፊ አቶ አስራት ስልክ ደወልኩ እና አቶ ስየን የት እንደማገኛቸው ጠየኩት። ከአቢአዲ የ30 ደቂቃ የሚኾን መንገድ ተጉዤ ወርቃአምባ የምትባል ቀበሌ እንድሄድ እና እሳቸው ካሉበት ቦታ ወደዛ እንዲመጡ እንደሚያደርግልኝ ነገረኝ።
ከዚህ የስልክ ልውውጥ በኋላ ወደ መናኸሪያ ተመለስኩ። በመግቢያ ላይ አውቶብስ ውስጥ ያገኘኋትን ሴት ቆማ አየኋት፤ ፈጠን ብላ ... ምነው የምትፈልጊውን አጣሽ አለችኝ? ... ወደ ወርቅአምባ ልሄድ እንደሆነ ነግሬያት ቦርሳዬን አስፈትሼ አውቶብስ ውስጥ ገባሁ። የወርቅአምባ መንገድ ፒስታ እና አቧራማ ቢሆንም ቀጥ ያለና አጭር ነበር። እንደደረስኩ ለአቶ አስራት ስልክ ደወልኩ፤ መምጣቴን ሊነግራቸው ስልክ ሲደውል ወደ አቢያዲ እየሄዱ እንደሆነ እንደነገሩት አስረድቶኝ እሳቸው ጋር እንድደውል ምክር ለገሰኝ።
ወርቅአምባ የድንጋይ ቤቶች የሞሉባት የገጠር ቀበሌ፤ በጣሊያን ጊዜ በተደረገ ውጊያ 10 ሺህ የጣሊያን ወታደር እንደተቀበረባት የሚነገርላት መንደር ናት። ወጣቶች እና ህጻናት ሰብሰብ ብለው ቆመዋል። ፀጉረ ልውጥ መኾኔን ስላወቁ ነው መሰለኝ ለጊዜው ሁሉም የሚመለከቱት እኔን ነበር። ለጥቂት ደቂቃም ቢኾን ከዕይታቸው ለመሰወር ብዬ የመጣሁበትን አውቶብስ ረዳት ለስላሳ የት ላገኝ እንደምችል ጠይቄ ወዳሳየኝ ቤት ጎራ አልኩ።
... ኮካ ይኖራል? ... ብዬ የጠየኩት አስተናጋጅ ... ”ኮካ? ...” በማለት መልሶ እኔኑ ጠየቀኝ። ለስላሳ እንደማላገኝ ስረዳ ወደመጣሁበት አውቶብስ ሹፌር ተጠግቼ ወደ አቢያዲ መሄድ እንደምፈልግ ነገርኩት። እስኪሞላ ጠብቂ አለኝ። ተመልሼ ወደ አውቶብሱ ገባሁ። ጥቂት ሰዎችን እንደጫነ፤ ... 50 ብር ክፈይ እና እንውሰድሽ አለኝ ... ተስማምቼ አቢያዲ ገባሁ።
አቢያዲ እንደደረስኩ በድጋሚ ለአቶ አስራት ደውዬ አቶ ስየን የት ላገኛቸው እንደምችል ጠየኩት፤ ያሉበት ቦታ ከመናኸሪያው ቅርብ በመኾኑ መጥቶ እንደሚወስደኝ በነገረኝ በአምስት ደቂቃ ውስጥ እዛው አገኘሁት። አቶ ስየ ወደሚገኙበት ቤትም አመራሁ። የውስጥ ለውስጥ መንገዱ ድንጋያማ እና ዳገት ነው። የውጭ ቀለሙ ወዳረጀ የዱሮ ቤት ደረስን። በመግቢያው ላይ ... ምህረት አብ የመጠጥ ማከፋፈያ ... ይላል። ወደ ውስጥ ዘለቅን።
አራት በአራት በኾነች ቤት ውስጥ ጥግ ላይ አንድ አልጋ አለ። የቤቱ ዙሪያ በስሚንቶ መደብ ተሰርቶበታል። አንገታቸው ላይ ሽርጥ የጠመጠሙት አቶ ስየ ዙሪያቸውን ከበው የተቀመጡት ወጣቶች የሚነጋገሩትን ይሰማሉ። ወንድማቸው አቶ ፍሰሃ አብርሃ፤ ከያዙት ወረቀት ላይ ስም እየጠሩ ምልክት ያደርጋሉ። ወጣቶቹ የምርጫ ታዛቢዎች እንደሆኑ ገባኝ። ከመታዘብ ራሱን ያገለለ ታዛቢን በሌላ ለመተካት ከተቀሩት ጋር ይወያያሉ።
... ለምን ሳትነግሪኝ መጣሽ? .... የመጀመሪያ ጥያቄያቸው ነበር። ለዐረናው ፀሐፊ ደውዬ መናገሬን እና እሱ ሊነግራቸው ይችላል ብዬ መገመቴን አብራራሁ።
በታዛቢዎች ጉዳይ ምርጫ ቦርድ ሊሄዱ መኾኑን ነግረውኝ ከፈለኩ እንድጠብቃቸው፤ ሌላ ሥራ ካለኝ ደግሞ ስጨርስ እንድደውል ጠቁመውኝ ተነሱ። አመጣጤ ስለ ምርጫ ቅስቀሳው የመጨረሻ ቀናት መረጃ ለማግኘት በመኾኑ ወጣ ብዬ መረጃ ለመሰብሰብ ተከትያቸው ወጣሁ። ከግቢው ወጥቼ መንገዴን ልጀምር ስል፤ አንድ ወፈር ያለ ፖሊስ ከተቀመጠበት ተነስቶ ወደኔ ቀረበ። ... እንደምን አሉ ... አለና ጨበጠኝ ሠላምታ መስጠት የአካባቢው ባህል መስሎኝ ተመሳሳዩን አደረኩ። እንደገና ሠላምታ ሰጠኝ፤ ግራ መጋባት ይነበብበታል። ከፊት ለፊቴ ጀርባውን ሰጥቶ የተቀመጠ እና ከኋላ ሲያዩት ሲቪል የለበሰ የሚመስል ፖሊስ ፍንጥር ብሎ ተነሳና ወደኔ መጥቶ፤ ... እስኪ መታወቂያ አምጪ ... አለና ጠየቀኝ። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የመንግሥት ጉዳዮች ኮሚዩኒኬሽን የሰጠኝን መታወቂያ አውጥቼ አሳየሁት። በትግርኛ ሊያነጋግረኝ ሞከረ እንደማልችል ነግሬው በአማርኛ እንዲያዋራኝ ጠየኩት።
ወደ መኪናቸው ሊገቡ የነበሩት አቶ ስየ፣ ፖሊሶቹን ጨምሮ የከበበኝን ሰው ሲመለከቱ ወደኛ መጥተው ምን እንደተፈጠረ ፖሊሶቹን ጠየቁ። ተንቤን ለመንቀሳቀስ ፍቃድ የላትም አሉ። ተንቤን ኢትዮጵያ በመኾኑ እና እኔ ደግሞ ኢትዮጵያዊ በመኾኔ ልዩ ፍቃድ እንደሚያስፈልገኝ ባላውቅም ... የምን ፈቃድ? .... ስል ጠየኩ፤ ምርጫ ቦርድ የሚሰጠው አሉ። አብረውኝ የነበሩት ለፖሊሱ የሰጠሁት መታወቂያ ምርጫ ቦርድ የሰጠኝ መኾኑን እና ጀርባው ላይ ፈርመው መኅተም ያኖሩት የቦርዱ ሊቀመንበር ፕሮፌሠር መርጋ በቃና መኾናቸውን በመግለጽ ለማስረዳት ሞከሩ። ግን የሚኾን አልነበረም።
... የምንፈልገው እሷን ነው። ይዛችኋት ኑ ነው የተባልነው። በስሟ ምንም የተሰጠ ፍቃድ የለም ... አሉ። የሚሉት ነገር ብዙም ባይገባኝም እየከበበን የመጣው የመንደሩ ሰው ሠላም ነሳኝ። ችግር ቢፈጠር ምክንያት ለመኾን አልፈለኩም። ... ”እንደነገራችሁኝ ጉዳዩ የሚመለከተው እኔን ነው። ስለዚህ እኔን ወደምትፈልጉበት ይዛችሁኝ ሂዱ ...” አልኳቸው። እነሱም የሚፈልጉት እሱን መኾኑን ገልጸው፤ ለሁለት አጅበው ወደ ጣቢያ ወሰዱኝ። ከፀሐዩ፣ ከሙቀቱ እና ከአቧራው ጋር መንገዱ ሲደራረብ ጣቢያው ሩቅ ሆነብኝ። ጣቢያ እንደደረስን ፖሊሶቹ ወደ አለቃቸው ቢሮ አስገቡኝ። ካመጡኝ ፖሊሶች አንዱን ተጨምሮ አራት ኾነው በጠባቧ ክፍል ተቀመጡ።
ከፊት ለፊቴ የተቀመጠው ፖሊስ ምንም ሳይለኝ ወረቀት አውጥቶ መጻፍ ጀመረ፤ ስሜን እስከ አያቴ ጠየቀኝ ... መጀመሪያ ለምን እንደመጣሁ ንገረኝ ... ስል ጠየኩት። ... ተንቤን ውስጥ ለመንቀሳቀስ የሚያስችል ፈቃድ የለሽም፤ ለኛ ምርጫ ቦርድ የላከልን ወረቀት አለ በዚህ ወረቀት መሰረት አንድም ለምርጫው ወደ ተንቤን የሚመጣ ጋዜጠኛ የለም ... አለኝ።
እኔ በምሠራበት ድርጅት አማካኝነት ምርጫውን ለመዘገብ የሚያስችል ፈቃድ ስጠይቅ ደብዳቤ እንዳስገባ ተነግሮኝ ያንን ማድረጌን ከዚያም በሞላሁት ፎርም ላይ፤ ትግራይ፣ ተንቤን፣ አዲግራት፣ ሽሬ እና አድዋ ውስጥ እንደምንቀሳቀስ ማሳወቄን ገልጬላቸው ይህንንም ምርጫ ቦርድ አሊያም ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች በመደወል እንዲጠይቁ ጠቆምኳቸው።
ነገር ግን መርማሪው ፖሊስ የት እንሆነ ባላውቅም በተደጋጋሚ ስልክ እየደወለ የያዝኳቸው ሁለት መታወቂያዎች ላይ ያለውን መረጃ በሙሉ እየደጋገመ ያነባል። በመጨረሻም ... ያንቺ ጉዳይ መጣራት ስላለበት እስኪጣራ እዚህ ትቆያለሽ አለኝ ... እና ውጭ ባለ አግዳሚ ላይ አስቀመጠኝ።
በየጥቂት ደቂቃዎች ልዩነትም እየጠራ መታወቂያዬ ላይ ያለውን መረጃ ምንም ሳያስቀር በስልክ ያነባል። በመጨረሻ አንድ ፖሊስ መጣና ... መታወቂያሽን ላኪ ትባያለሽ ... አለኝ፤ ለሱ ልሰጠው እንደማልችል ነግሬው ተከትዬው ሄድኩ ግን ምንም የተለየ ነገር አልነበረም አሁንም መታወቂያው ላይ ያለው መረጃ በስልክ ለሌላ ሰው አነበበ እና ወደነበርኩበት እንድመለስ አዘዘኝ።
ሙቀቱ እና ረሃቡ ስለተደራረበብኝ ለስላሳ ነገር ወጥቼ ጠጥቼ እንድመጣ ጠየኩ፤ ... ”የለም አንቺማ መውጣት አትችይም ምትፈልጊው ይገዛልሻል ...” ተባልኩ። መታሰሬ እንደሆነ ገባኝና አዲስ አበባ ወደሚገኘው ቢሮዬ ደወልኩ። ለኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ደውለው እንዲያሳውቁልኝ ነገርኳቸው።
ሰላሳ ደቂቃ ያህል ቆይቶ መርማሪ ፖሊሱ ወደኔ መጣ፤ ... ”እንዲጣራ ደውያለሁ በቃ እስኪጣራ ትቆያለሽ ያለበለዚያ ደግሞ ወደ መቀሌ እንመልስሻለን ...” አለኝ። ያንን ማድረግ እንደማይችሉ ጠንከር አድርጌ ነገርኩት፤ አሁንም እንድጠብቅ ነግረውኝ ገቡ። በአጠቃላይ ለአንድ ሰዓት ከአርባ ደቂቃ እንደቆየሁ እንደገና ተጠራሁ እና ገባሁ። መርማሪው አሁንም ስልክ ያወራል። አጠገቡ የተቀመጠው ሲቪል ለባሽ፤ ”ለምን መጣሽ፣ እነ አቶ ስየን የት አገኘሻቸው ...” የሚሉ ጥያቄዎችን ይጠይቀኝ ገባ። አመጣጤን እና እንዴት እንዳገኘኋቸው ነገርኩት።
ስልክ የሚያወራው ፖሊስ ... ”ነይ ይህን ስልክ አናግሪ ...” አለኝ። የማናግረውን ሰው ማንነት ጠየኩት፤ ... ”እሱኑ አናግሪው” አለኝ ...። በስልኩ ውስጥ ድምፁ የሚሰማው ሰው ትግርኛ እንደምችል ጠየቀኝ፣ እንደማልችል ነገርኩት እና በአማርኛ ማውራት ጀመረ። የመዘገብ ፍቃድ ስለሌለኝ እና እሱ እስኪጣራ እንደቆየሁ ነገረኝ። መቼ እንደመጣሁ፣ የት ሆቴል እንዳረፍኩ፣ ተንቤን መቼ እንደገባሁ ከጠየቀኝ በኋላ ማንነቱን ሳይነግረኝ ስልክ ቁጥሬን ትቼ እንድወጣ ነገረኝ። የሱን ማንነት ግን ሊነግረኝ አልቻለም። ስልኩን ከዘጋሁ በኋላ መታወቂያዬ ፎቶ ኮፒ እንዲደረግ መታዘዙን ነግረው ኮፒ አድርገው መለሱልኝ፤ አሁን መሄድ ትችያለሽ ተባልኩ።
የፖሊስ ጣቢያውን ግቢ ለቅቄ ስወጣ ነፃነት ሊሰማኝ አልቻለም። አነስተኛዋ የተንቤን ከተማ በአቧራ ተሞልታለች። ፀሐዩ የሚሞከር አይደለም በመንገዱ ላይ ሰው አይታይም። ወዴት እንደምሄድ ግራ ተጋባሁ። ፖሊስ ጣቢያው አቅራቢያ ያለ አንድ አነስተኛ ሱቅ ገባሁ፤ ከሱቁ ስወጣ ጣቢያ ውስጥ ያያሁት ልጅ እግር ፖሊስ ከእነ ፖሊስ ልብሱ እየተከተለኝ እንደኾነ ተረዳሁ። በጣም እርግጠኛ ለመኾን የማር ገበያው የት እንደሚገኝ ባለሱቁን ጠየኩ እና በነገረኝ አቅጣጫ ቁልቁል ወረድኩ ... ማሪ ... የምትለዋን ቃል እየጠራሁ ገበያውን መዞር ጀመርኩ። ያልታከተው ፖሲስ አብሮኝ ይዞር ገባ። እውነቱን ለመናገር በጣም ፍርሃት አደረበኝ። የት እንዳለሁ ግራ ተጋባሁ። ከተማውን ጥዬ ወደ መቀሌ መመለስ ፈለኩ። ለማንኛውም ራሴን ማረጋጋት እንዳለብኝ ተረዳሁ እና ፊት ለፊቴ ”ለንደን ምግብ ቤት” የሚል አየሁ እና ወደ ውስጥ ዘለቅኩ። ምግብ ቤቱ ልክ እንደ መኖሪያ ቤት በጥሩ መስተንግዶ ተቀበለኝ፤ ትንሽ ተረጋጋሁ።
ከዚህ በኋላ ከተማ ውስጥ እያጠያየቅሁ መዞር ሞኝነት መስሎ ተሰማኝ። መቀሌ ለሚገኙት የህወሓት ቃል አቀባይ አቶ ወልደገብርኤል ደውዬ፣ አቢአዲ የሚገኘው ጽ/ቤት ኃላፊያቸው እንዲያነጋግረኝ ጠየኳቸው። ስልኩን አጣርተው መልሰው እንደሚደውሉ በነገሩኝ መሰረት ወዲያው ደውለው አሳወቁኝ። በሰጡኝ ስልክ ደውዬ ወደ ህወሓት ቢሮ አመራሁ። እዛ ላገኘሁት የፓርቲው ም/ል ኃላፊ አቶ ዳንኤል ሐጎስ የደረሰብኝን በዝርዝር አሳወቅሁት፤ በስህተት ሊኾን እንደሚችል እና ካሁን በኋላ በነፃነት እንድንቀሳቀስ ችግር ከገጠመኝ እንድደውልለት ነግሮኝ ስልኩን ሰጠኝ።
እንዲህ በተንከራተትኩባት ተንቤን ያለ ምንም ሥራ እየመሸ መሄዱ እያበሳጨኝ መጣ። በቻልኩት መጠንም መንቀሳቀስ ጀመርኩ። ምርጫ ቦርድ፤ ከአቶ ስየ ጋር ተፎካካሪ ኾነው ወደሚቀርቡት አቶ ኪሮስ፣ በመጨረሻም ወደ አቶ ስየ አመራሁ። ወደ ኋላ የመመለስ ሃሳቤን ሰርዤም ብዙ ታሪክ ወዳላት ወደ ስየ ከተማ ... ዓዲሓ ... አቀናሁ።
ጽዮን ግርማ - ከተንቤን