Ato Siye Abrha አቶ ስየ አብርሃጽዮን ግርማ - ከትግራይ

በመኪና ከአቢአዲ የአንድ ሰዓት፤ በእግር ደግሞ ለሦስት ሰዓት የሚያስጉዘውን፣ ዳገታማ፣ ቁልቁለታማ፣ ጠመዝማዛ እና ድንጋያማ መንገድ አቆራርጠን ዳገት ላይ ከሚገኝ አንድ ቤት ደረስን - ቅዳሜ ግንቦት 14 ቀን 2002 ዓ.ም.። የቤቱ ብረት በር ተከፈተልን እና ወደ ውስጥ ዘለቅን። በድንጋይ የተሠራው ቤት ሰፊ ሳሎን አለው። አነስ አነስ ያሉ አራት መኝታ ክፍሎችንም ይዟል። የቤት ዕቃዎቹ አርጅተዋል፤ ሰፊው ግቢ አካባቢው ላይ በስፋት በሚገኘው ቀይ ድንጋይ ታጥሯል።

 

አንገታቸው ላይ የጠመጠሙትን ሽርጥ (ኩሽክ) ፈተው ጥግ ተቀመጡ። አብረዋቸው ከመጡት ወጣቶቹ ጋርም መጫወት ጀመሩ። ገና ከመቀመጣቸው አንዲት ልጅ እግር ሴት የጣት ውሃ አቀረበችላቸው። በዳንቴል የተሸፈነ ነገርም በሰፌድ ይዛ ብቅ አለች። ከሰፌዱ ላይ ወፈር ብሎ ጠቆር የሚለውን እንጀራ እያነሳች ሙሉ ሙሉውን ዝርግ ሳህኖቹ ላይ አነጠፈች። ላዩ ላይም ቀይ ድፍን ምስር አፈሰሰችበት። አንዱን ሳህን ለሰውየው አቀረበችላቸው።

 

Ato Siye's mother houseበጆግ ያመጣችውን ነጭ የትግራይ ጠላ አፉ ላይ ሰፋ ባለው ጥቁር ዋንጫ እየሞላች ሰጠች። ሰውየው እንጀራ በምስር ወጣቸውን በጠላ እያወራረዱ ዝም ብለው ይመገባሉ። ከኔ አጠገብ የተቀመጠ ወጣት፤ ”ታጋዮች በብዛት ይመገቡት የነበረው ይህንን ነበር፤ ድፍን ምስሩን ”ብርሽን” ይሉታል” አለኝ። ሰውየውን ቀና ብየ አየኋቸው። አሁንም በፀጥታ አቀርቅረው ይመገባሉ። ምናልባት ምግቡ የትግል ጊዜያቸውን አስታውሷቸው ይሆናል ብዬ አሰብኩ።

 

እኚህ ሰው በ1967 ዓ.ም. በመስከረም ወር ሥልጣን ላይ የወጣው ደርግ፤ ተማሪዎች ወደ እድገት በኅብረት ዘመቻ እንዲሄዱ ያቀረበውን ሃሳብ ተቃወሙ። በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይከታተሉት የነበረውን የሕክምና ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደዚህች የትውልድ መንደራቸው ”ዓዲሓ” ቀበሌ መጡ - ከ34 ዓመታት በፊት።

 

ትምህርታቸውን አቋርጠው ወደዚች መንደር የመጡት ያለምክንያት አልነበረም። በዩኒቨርስቲ ውስጥ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች ሲያደርጉ የነበሩ ጓደኞቻቸው ”መልዕክት እስኪደርስህ ጠብቅ” ብለዋቸው ስለነበር ነው። ብዙም ሳይቆይ አንድ መልዕክት ደረሳቸው፤ ወደ ኤርትራ እንዲሄዱ። ኤርትራ እንደደረሱ ተኩስ ተከፈተ። ለአንድ ዓላማ የተሰለፉት ወጣቶች መሄጃ ስላልነበራቸው ግራ ተጋቡ።

 

Ato Siye Abrha አቶ ስየ አብርሃበኋላ ግን እሳቸው የሄዱበት ቡድን እና የካቲት 11 ጉዞ የጀመረው ቡድን አንድ ላይ ተቀላቀለ። ኤርትራ በረሃ ውስጥ ሳህል በተባለው የሻዕቢያው ማሠልጠኛ ገብተው ለሦስት ወራት ሠለጠኑ። ከበረሃው ሲመለሱ 20 የመከራ ቀናትን በመንገድ አሳለፉ። ፀሐዩ፣ ዝናቡ፣ ረሃቡ፣ ... ዓላማቸውን ደግፈው ተቀላቅለዋቸው የነበሩ ጥቂት ገበሬዎች አቅቷቸው እዛው ቀሩ። እነሱ ግን ሥልጠናውን አጠናቀው ተመለሱ። እኚህ ሰው የትጥቅ ትግሉን በዚህ መንገድ ጀምረው 17 የትግል ዓመታትን በበረሃ አሳለፉ - አቶ ስየ አብርሃ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስቴር ሚኒስትር።

 

በትግሉ ውስጥ አምስት ዓመታትን እንዳሳለፉ አንድ አሳዛኝ መርዶ ተነገራቸው። ቅድመ አያቶቻቸው የቆረቆሩት የትውልድ መንደራቸው፤ የልጅነት ጊዜያቸውን ያሳለፉበት የወላጆቻቸው ቤት ችግር ገጠመው። ደርግ በሐውዜን አድርጐት ከነበረው ዘመቻ ሲመለስ ወደ ወላጆቻቸው ቤት ጐራ ብሎ ነበር። የባላባት ወላጆቻቸውን መኖሪያ ቤት የደርግ ሠራዊት ሙሉ ለሙሉ አቃጥሎ ወደ ሜዳነት ቀየረው። እናት እና አባታቸው አቢአዲ ተወስደው ታሰሩ። ወላጅ እናታቸው ወ/ሮ አልጋነሽ በላይ ተፈተው ተመልሰው በመምጣት እዛው አካባቢ በሚገኝ ቤት ልጆቻቸውን ሰብስበው ተቀመጡ። አባታቸው ግራዝማች አብርሃ ሐጐስ ግን በወጡበት አልተመለሱም፤ ወደ መቀሌ ተወሰዱ። ከታሰሩ ከአንድ ወር በኋላም አንድ ለሊት ከሌሎች እስረኞች ጋር ወደ ሚረሸኑበት ቦታ ጉዞ ጀመሩ። ጥቂት እንደተጓዙ ግራዝማች አብርሃ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ከፖሊስ ጋር ትግል ጀመሩ። መኪናውን አጅቦ ሲከታተል የነበረ ሌላ መኪና እሳቸው ወዳሉበት መኪና የጥይት ሩምታው ለቀቀበት።

 

ከዚህ ጥይት ሕይወቱ የተረፈው አንድ ወሬ ነጋሪ ብቻ ሲሆን፤ ፖሊሶቹን ጨምሮ በመኪና ውስጥ የነበሩት በሙሉ ሕይወታቸው አለፈ። አቶ ገ/ሥላሴ የተባለው ወንድማቸውም በደርግ ተገደለ። ፍሰሃ፣ ወልደሥላሴ እና አስመላሽ ትጥቅ ትግሉን ተቀላቀሉ። አሰፋ የተባለው ወንድማቸው ወደ እስር ቤት ገባ። ትዕምኒት የተባለች አንድ እህታቸው ከምትማርበት ሚሲዮን ትምህርት ቤት ዩጐዝላቪያ የትምህርት ዕድል አግኝታ ወደ አውሮፓ ሄደች። ምህረትአብ ብቻ ከእናቱ ጋር ቀረ። ቤተሰቡ ተበታተነ።

 

”ሁሌም በየዓመቱ ጥር ሰባት የሥላሴ በዓል ይከበራል፤ በዚህ ዕለት ተሰባስበን እየመጣን እናታችንን አይተን ተመልሰን ወደ ትግሉ እንሄዳለን። ትግሉን ከጨረስን በኋላ ደርግ አቃጥሎ ባዶውን ባስቀረው መሬት ላይ ለእናታችን ገንዘብ አዋጥተን ቤት ለመሥራት ተስማማን። ይህንኑ ለአካባቢው ገበሬዎች አማከርን፤ በሃሳባችን ያልተስማማ አልነበረም። ሁሉም የቻለውን ቃል ገባ እና ይህ ቤት ለናታችን ተሠራ። እንግዲህ ይህን ቤት ነው ስየ ለእናቱ ቤተመንግሥት ሠራ የተባለው። ስለዚህ ቤት አሠራር እነ መለስም ጠንቅቀው ያውቃሉ። እኔ ላይ የሐሰት ፕሮፖጋንዳን ለመክፈት ብቻ ነው ስለዚህ ቤት ብዙ የተባለው” አሉኝ።

 

”እናታችንን ወደዚህ ቤት ካሻገርን ብዙም ሳንቆይ የኤርትራ ጦርነት መጣ። ልዩነቱ ተፈጠረ ቤተሰቡ ተሰብስቦ ታሰረ። ወ/ሥላሴ ከእስር ሲፈታ ወደ መከላከያ ተመለስ አሉት፤ የታሰረበትን ምክንያት እንዲያብራሩለት ጠየቃቸው፤ ሊገልፁለት ስላልቻሉ መከላከያን ለቆ ወደ እናቱ ቤት ተመለሰ። ትዳር መስርቶ ልጆች ወልዶ በዚህ ቤት ይኖራል፤ እኛም ስንመጣ ማረፊያችን ሆኖናል። የቡና እና የብርቱካን ሰፊ የእርሻ መሬት አለው። ግብርናውን አጥብቆ እስከያዘም ድረስ አይራብም” በማለት አቶ ስየ በትውልድ መንደራቸው ተቀምጠው ስለ ታሪካቸው ይተርኩልኝ ገቡ።

 

አቶ ስየ ለአራተኛው ሀገራዊ ምርጫ በቆላ ተንቤን ለመወዳደር ወደተወለዱበት ዓዲሓ ቀበሌ ከከተሙ ቀናት አስቆጥረዋል። በተከራዩት ላንድ ክሩዘር መኪና ቀኑን ሲቀሰቅሱ ውለው ማምሻውን ወደ ማደሪያቸው፣ ወደ እናታቸው ቤት ይመጣሉ።

 

”ወደዚህ እንደመጣሁ ስብሰባ እንዳላደርግ የሚከለክል ዝግጅት ተደርጐ ነበር። ስብሰባ መጥራት ደግሞ በጣም አስቸጋሪ ነው። ከአንድ ቀበሌ ህዝብ ጋር ቁጭ ብሎ ለመወያየት ገበሬው ተሰባስቦ እስኪመጣ ጊዜ ይወስዳል። በዚህ ላይ በቅስቀሳ ተጠርቶ እንዳይመጣ ጫና ይደረግበታል። እኔ የነበረኝ ጊዜ አጭር በመኾኑ፤ ስቱዲዮ ያዘጋጀሁትን በሙዚቃ የታጀበ ንግግር በስፒከር እለቅላቸዋለሁ፤ ህዝቡ ከያለበት መጥቶ ያዳምጠዋል። ንግግሩ ሲያልቅ ደግሞ ራሴ ቆሜ ተጨማሪ ንግግር አደርጋለሁ።” ይላሉ - አቶ ስየ።

 

አቶ ስየ በዚች ትውልድ መንደራቸው ለመወዳደር በሚያደርጉት የምርጫ ቅስቀሳ ብቻቸውን አልነበሩም። ወንድማቸው አቶ ፍሰሃ አብሯቸው ነበር። ለታዛቢዎቹ በየሰዓቱ ይደውላል፣ ያሰማራል፣ መረጃ ይቀበላል፣ ችግር ሲፈጠር ለመፍታት ይሞክራል፣ በየምርጫ ጣቢያው እየተዘዋወረ ሁኔታውን ይከታተላል። ከአቅሙ በላይ ሲሆን አቶ ስየ ስር ቁጭ ይልና ያዋያቸዋል። አንዳንዴም ታዛቢዎችን ሰብስቦ ይወያያል። አቶ ወልደሥላሴ የተባለው ወንድማቸውም ከሥራቸው አይወጣም። የሚኖረው በዛች መንደር ስለሆነ ነገሮችን በቅርበት ይከታተላል። ሁለቱም ወንድሞቻቸው አንድም ሰዓት ሳያባክኑ አግዘዋቸዋል።

 

የወንድማቸው ወልደሥላሴ ባለቤት ልጅ እግር ናት። የሦስት ልጆች እናት አትመስልም። የመቀሌ ልጅ ነበረች። እንደነገረችኝ ጤና ጣቢያ ውስጥ በሕክምና ሞያ ሥራ አግኝታ ስትመጣ የሚከራይ ቤት መፈለግ ዋና ተግባሯ ነበር። ነገር ግን የተገኘላት ቤት መግባት አልፈለገችም፤ ስለ እነ አቶ ስየ ብዙ ይወራ ነበር፤ ሱቅ አላቸው ሱቃቸው ውስጥ ዕቃ የሚሸጥበት ዋጋ ከተማ ከሚሸጠው ዋጋ በግማሽ የቀነሰ ነው፣ እነሱ ለብቻ መብራት አላቸው፣ ቤታቸው ቤተመንግሥት ነው የሚመስለው፣ የቤት ኪራይ ቅናሽ ነው የሚሉና የመሳሰሉ በርካታ ነገሮችን ሰምታ ነበር፤ ”እኔም ወደዚህ ስመጣ እባካችሁ ከነስየ ቤት ፈልጉልኝ ብዬ ወጥሬ ያዝኳቸው፤ ፍለጋዬ ከቤት ኪራይ አለፈና ተድሬ ገባሁ። የተባለው አንድም እውነት አልነበረም። ቤቱ እንደምታይው ነው፤ ምኑ ቤተመንግሥት እንደሚመስል አላውቅም፣ ወንድማማቾቹ ካላቸው ኅብረት፣ ከደረሰባቸው ግፍ እና ከተንከራተቱት አንፃር ለእናታቸው ቤት መሥራት ሲያንሳቸው ነው። ደሞ ቤቱ የተለየ ነገር የለውም ድንጋይ ነው። ድንጋዩ ደግሞ እዚህ አካባቢ የሞላ ነው። በጣም የሚገርመው ቤቱ መብራት እንኳን የገባለት በ1999 ዓ.ም. መጨረሻ ላይ ነው። ውሃ እስካሁን ከጉድጓድ በአህያ እያስቀዳን ነው የምንጠጣው ይህን ደግሞ ራስሽ አይተሸዋል” ስትል የትግራይ ቡና እያጠጣች አጫወተችኝ። ያየሁትን እንድመሰክር በምስክርነት ቆጠረችኝ።

 

የስየ የምርጫ ቅስቀሳ

በግንቦት ወር መጀመሪያ ከአሜሪካ በተመለሱ በሁለተኛው ቀን ወደ ትውልድ መንደራቸው ያቀኑት አቶ ስየ፣ በዘፈን የታጀበ ንግግር አዘጋጅተው፤ መኪና ተከራይተው በትልቅ ስፒከር በየመንገዱ እየዞሩ ቀኑን ሙሉ ሲቀሰቅሱ ይውሉ እንደነበር ይናገራሉ።

 

የቅስቀሳ መልዕክቱ፣ በመሬት ፖሊሲ ላይ ስላላቸው አቋም፣ በክልል ስላለው የብድር አሰጣጥ፣ ስለ ፍትሕ ሥርዓቱ እና ስለ ትምህርት ፖሊሲው አቋማቸውን የሚያስረዳ ነበር። ”መንደር ውስጥ እገባና፣ መኪናየን አቁሜ ከፍ ባለው ድምፅ ማጉያ ንግግሬን እከፍትላቸዋለሁ። በመንገድ የሚሄደው፣ ቤቱ ያለው፣ የሚያርሰው ሁሉም ተሰብስቦ ያዳምጣል። በተለይ ስለ ብድር እና ፍትሕ ሥርዓቱ ስናገር ሰዉ ተነቅሎ ይወጣል። ቴፑ ሲያልቅ እኔም እዛ እንዳለሁ እንዲያውቁ ወጥቼ እናገራለሁ።” በማለት ሲያደርጉት ስለነበረው ቅስቀሳ አጫወቱኝ።

 

በምርጫ ለመወዳደር ከመወሰናቸው በፊት ጥር ወር ላይ ወደ አካባቢው መጥተው፣ ያለውን ሁኔታ ቃኝተው፣ ተዘዋውረው ነዋሪውን ባነጋገሩበት ወቅት ያገኙት ምላሽ ጥሩ በመኾኑ ወደ ምርጫው ለመግባት እንደወሰኑ የሚናገሩት አቶ ስየ፤ ከአሜሪካ መልስ ወደ ትውልድ መንደራቸው ሲያቀኑ ግን ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ ተደርጐ እንደጠበቃቸው ይገልፃሉ።

 

የኃይሌ ገሪማ ”ጤዛ” የተሰኘው ፊልም በእያንዳንዱ ቀበሌ እንዲታይ ከተደረገ በኋላ ”ስየ ከደርጐች ጋር ተባብሮ በዘመኑ የነበረውን ጭፍጨፋ ሊመልስብህ ነው፣ መሬት ይሸጥ ይለወጥ የሚለው የወላጆቹን መሬት ሊሸጥ ነው፣ መሬትህን ሊያሸጥብህ ነው” የሚል እና በርካታ በውሸት ላይ የተመሰረተ ቅስቀሳ እንደተደረገባቸው ይናገራሉ።

 

ህወሓት በትግራይ በዓረና ላይ ካደረገው ቅስቀሳ በተለየ በአቶ ስየ ላይ ያደረገው ሚዛኑን እንደሚደፋ የሚናገሩ አሉ። ለምን ይሆን? ስል የትግራይ ክልል የመንግሥት እና ህዝብ ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጐበዛይ ወ/አረጋይን ጠየኳቸው። ”የፖለቲካ ሥራ ሲሠራ ህዝቡን ለማሳመን ዋጋ የሚያወጣ ንግግር ተመርጦ ነው ተግባር ላይ የሚውለው፤ ማንም የማያውቀውን ተመራጭ ስም ጠርቶ ስለሱ እየተጠቀሰ ቅስቀሳ ቢደረግ ሰውየውን ማንም ሊያውቀው ስለማይችል ቅስቀሳው ዋጋ እንደሚያጣ ይጠቅሳሉ። ፓርቲውን የሚመሩትን ሰዎች፤ እነ ስየ፣ ነጋሶ፣ ግዛቸው፣ ... እየተባለ ቢቀሰቀስ ግን ሁሉም ሰው ያውቃቸዋል። ከመሪዎቹም በምክትልነት የሚታወቁት እንደ ገብሩ አስራት ያሉ ትልልቅ ሰዎች በመኾናቸው እነሱ የሚናገሩት እና የሚያደርጉት ነገር የፓርቲው መገለጫ ነው። ስለዚህ ፓርቲው እሳቸው ላይ ማነጣጠሩ ትክክለኛ እርምጃ ነው ይላሉ” - አቶ ጐበዛይ።

 

እነሱም የማስተባበል እና ራሳቸውን የመከላከል መብት እንዳላቸው ይገልጻሉ። አቶ ስየ አንድ ምርጫ ክልል አካባቢ ተወዳዳሪ ስለሆኑ በክልሉ ያለው ቅስቀሳ ከፓርቲ አልፎ በግለሰብ ደረጃ የሚታይበት ሁኔታ እንደሚኖርም አቶ ጎበዛይ ተናግረዋል።

 

ሌላ ተጨማሪ ምክንያት የሚያስቀምጡት አቶ ጎበዛይ ”አቶ ስየ ብዙ ስህተት ደጋግመው ስለሚናገሩ ደግሞ ለህወሓት ምርጫ ቅስቀሳ በጣም ጠቃሚ ይሆናሉ። ፓርቲ ወክለው በኅብረተሰቡ ተቀባይነት እና የፖለቲካ ብስለት የሌለው ሃሳብ ደጋግመው ሰንዝረዋል፤ ስለዚህ እነዚህን ንግግሮች ሌላ ተቃዋሚ ፓርቲ ለፕሮፖጋንዳ ቢጠቀምበት ምንም ስህተት የለበትም” ብለዋል።

 

አቶ ስየን ከዓመታት በኋላ በእነዚህ ቦታዎቹ ተዘዋውረው ሲቀሰቅሱ ምን እንደሚሰማቸው ጠየኳቸው፤ ”ለኔ ሁለተኛ ምዕራፍ ነው። በትጥቅ ትግሉ ጊዜ አሁን በምንቀሳቀስባቸው ደን እና ተራሮች በእግሬ ወጥቼ ወርጄያለሁ። ያኔ በ20ዎቹ መጨረሻ በ30ዎቹ መጀመሪያ ላይ የነበረ የወጣትነት ጊዜዬ ነው። ጠመንጃ ተሸክሜ ሽጉጥ ታጥቄ ነበር የምንቀሳቀሰው። ስለዚህ ገጠሮቹን በደንብ አውቃቸዋለሁ። አሁን ወደዚህ አካባቢ ስመለስ እያንዳንዱ ኮረብታ የራሱ ታሪክ አለው። የውጊያ እና የመቃብር ቦታ ነው። በሕይወት ከሌሉትም ካሉትም ጓደኞቼ ጋር ጨዋታ እና ሳቅ የነበረበት ቦታ ነው። እያንዳንዱ መንገድ የራሱ ታሪክ አለው። ትዝታን ይቀሰቅሳል። ቤዝ አካባቢያችን እና ቤታችን የነበሩ አካባቢዎች ናቸው፣ የተሸከመን፣ የቀለበን ያስጠለለን፣ መጠለያችንን ሠርቶ የሰጠን ገበሬ ያለበት አካባቢ ነው። የመሬት ውስጥ ቤት ሠርተን የኖርንባቸው አካባቢዎች አሉ፣ ቤቱን የሠሩልን ገበሬዎች አሉ፣ ቁስለኞቻችንን ተሸክመው በረሃ አቋርጠው ሆስፒታል ያደረሱልን ገበሬዎች አሉ። ውጊያ ያካሄድንባቸው አካባቢዎች አሉ። ጥይቱን ተሸክመው ያጓጓዙልን ገበሬዎች አሉ፤ እነዚህን አካባቢዎች ከዓመታት በኋላ እየዞርኩ ስቀሰቅስባቸው፤ በትዝታ የኋላውን እቃኛለሁ።” ይላሉ አቶ ስየ።

 

”አሁን ደግሞ ስዘዋወርበት ይሄ ሁሉ ትግል እና ችግር ታልፎ የህዝቡ ሕይወት አለመቀየሩ፣ ገጠሩ ምንም ያልተለወጠ መሆኑ ይታያል። ውሃ ገብ በኾኑ የተወሰኑ መንደሮች ላይ ትንሽ የቆርቆሮ ቤት አያለሁ። በአብዛኛው ግን የህዝቡ ኑሮ፣ ድህነቱ፣ ፊት ለፊት ይታያል። ይህ ሁሉ ተከፍሎ ህዝቡ ከዲሞክራሲ፣ ከመልካም አስተዳደር፣ ከነፃነት፣ ከልማት እና ከኢኮኖሚያዊ እድገት ተጠቃሚ አለመኾኑን ሳይ ደግሞ አዝናለሁ። እቆጫለሁ። ይሄ ደግሞ ጉልበት ይሰጠኛል። በዚህ በፀሐይ፣ በዚህ በመንገድ፣ በዚህ ዕድሜዬ፤ ሰውየው አብዷል ወይ? ምን ለማግኘት ነው? ፓርላማ ገብቶ ገንዘብ ለመውሰድ? የሚል ይኖራል። ግን አይደለም። መቀየር እንዳለበት ይበልጥ እየተሰማኝ እና ጥንካሬ እየሰጠኝ ይሄዳል፤ ስለዚህ እንደ ዱሮ እንጀራ በልቼ፣ የተገኘውን ጠጥቼ በረሃ ውዬ ማታ እገባለሁ።” አሉኝ።

 

ድንጋያማ፣ ዳገት እና ቁልለት በበዛባት የአቶ ስየ መንደር ተዘዋወርኩ። ድካም ሲሰማኝ ወደ አንዲት ሻይ ቤት ጎራ አልኩ። አቶ ስየ ቀደም ሲል ከመንደሩ ሰው ጋር አድርገውት ስለነበረው የቅስቀሳ ውይይት ሰማሁ። በአስተርጓሚዬ አማካኝነት ተጨማሪ ጠየኩ።

 

እሁድ ግንቦት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. አቶ ስየ 57ኛ ዓመት የልደት በዓላቸውን በተወለዱበት ዓዲሓ ቀበሌ ያከበሩባት ዕለት እንደነበር አወጉኝ። የአካባቢውን ሰው ማነጋገር እንደሚፈልጉ በመግለጽ በየቤቱ በጠዋቱ ነበር መልዕክት የላኩት። ወደ 300 የሚጠጉ የአካባቢ ነዋሪዎች ወደ አመሻሹ አካባቢ በየድንጋዩ ላይ ተቀምጠው ጠበቋቸው። የዕለቱ የአቶ ስየ ንግግር የአካባቢውን ነዋሪ ስሜት የቀሰቀሰ እንደነበረ እማኞቻችን ገለፁልኝ። የሚያስታውሱትን እንዲነግሩኝ ጠየኳቸው። ያብራሩልኝ ገቡ። ”እሱ ቆሞ እኛ ተቀምጠን ነበር የምንወያየው። በመካከላችን የነበሩትን አንድ አባት … አቶ ገረቻ … ብሎ ጠራቸው። ቀና ብለው አዩት፤ … አቶ ገረቻ ድሮ በዚህ በኩል የትግል ጓደኞቼን ይዤ ሳልፍ፤ … ወዲ ግራዝማች 20 ሰው ይዘህ መንግሥት ልትገለብጥ ነው? ብለው ስቀው ያለፉብኝን ያስታውሳሉ? ያ ሁሉ አልፎ ከትግል አጋሮቼ ጋር ሆኜ አልደፈር ያለውን ደርግ መታነው።

 

”... ”ከዛ በኋላ መከላከያ ሠራዊቱን አደራጅተን ደሞዝ እንዲከፈለው አድርገን ጥሩ አድርገን ገነባነው፤ መጨረሻ ላይ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት መጣ፤ ሁላችንም የነበርንበትን ሥራ ትተን ሻዕቢያን ድምጥማጡን እንደምናጠፋ፣ አሰብንም እንደምንይዝ በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ወስነን ወደ ጦርነት ገባን። ውጊያውን ጀመርን ከዛ የተፈጠረውን ታውቃላችሁ። ... እኔ እና መለስ ከትግል ጀምሮ እስከዛች ቀን ድረስ እንዴት እንዋደድ እንደነበር ታውቃላችሁ፤ መለስ ብዬ ጠርቼው አላውቅም ”መሊ” ነበር የምለው፤ ስየ ብሎኝ አያውቅም ”ስዩማይ” ነበር የሚለኝ። በኤርትራ ጉዳይ ግን ተጣላን። እናም ከሁሉም ቀድመው መጀመሪያ ወንድሞቼን አሰሩብኝ። እንደምታውቁት ወልደሥላሴን ከሻዕቢያ ጋር ሲዋጋ ከነበረበት አንስተው አሰሩብኝ። የወንድሜን ልጆች አሰሩብኝ። የዚህን ጊዜ ለጓደኛየ፤ ”ፀብህ ከኔ ጋር ነው እነሱ ምን አድርገውህ ነው ያሰርክብኝ?” ብዬ መልዕክት ላኩበት ቀጥሎ እኔም ታሰርኩ፤ አንዲት ብርቱካን የምትባል ዳኛ ጉዳዩን አይታ ለቀቀችን። ከፍርድ ቤቱ ስወጣ መልሰው አሰሩኝ። ከዛ በኋላ እንደምታውቁት ስድስት ዓመት ታሰርኩ። አርባ ስካንያ፣ ሰማንያ ስካንያ አለው እየተባለ ተወራብኝ፣ በዓዲሓ ቤተመንግሥት የኾነ ቤት ሠርቷል ብለው አስወሩብኝ፤ ቤቱ ከእናንተ የተደበቀ አይደለም የምታዩት ነው። አሁን ደግሞ ስየ መሬታችሁን ሊቀማችሁ ነው ተባላችሁ፤ እኔ ነኝ የእናንተን መሬት የምቀማ፣ እኔ የአያቶቼን መሬት ቆሜ ለደሀ ሴቶች ለእናንተ አላከፍፈልኩም?” ሲል ጠየቀን። ...” ሲሉ ተረኩልኝ። በአቶ ስየ ንግግር የተነኩ እንባቸውን አውጥተው አለቀሱ፤ አንዳንዶችም ከንፈራቸውን መጠጡላቸው። ውይይቱ በዚሁ መንፈሥ እንደቀጠለ እማኞቹ ነገሩን።

 

ጥቂት ጥያቄና አስተያየቶችን ተቀበሉ። አንዲት እናት ተነሱና፤ ”አንተ ስየ እኛ የማናቅህ ኾነህ ነው የምትነግረን፤ ምን ይባላል መሰለህ አሉ በትግረኛ ”ሳርን ውሃ ያበቅላታል መልሳ ግን ውሃውን አላሳልፍ ትለዋለች” አሉት፤ ከዛም አንዲት ቃል ሳይናገሩ መልሰው ተቀመጡ። በማለት አቶ ስየ በመንደራቸው አድርገውት ከነበረው ውይይት ስለ አንዱ አጫወቱኝ።

 

ምርጫው አልቆ ጊዜያዊ የምርጫ ውጤት መለጠፍ ከጀመረ በኋላ አንድ ሌላ ጋዜጠኛ ጨምሬ ወደ አካባቢው ተመለስኩ፤ ልምዴን ላጋራው ወደ ሌላ ሻይ ቤት ጐራ አልን። አንድ ወጣት አንገቱን ደፍቶ ወረቀት ላይ ይጽፋል። ሸምገል ያሉት አዛውንት አንባሻ እየገመጡ ሻይ ይጠጣሉ። ጋዜጠኛው ትግርኛ ተናጋሪ ነበር፤ በቋንቋቸው አጫወታቸው፤ ”የሚበጀንን መርጠናል”፤ አሉ ማንን እንደመረጡ ከመናገር ተቆጥበው፤ ከአዛውንቱ ጋር ያደረግነውን ሰፋ ያለ ጨዋታ ሲያዳምጥ የቆየው ወጣት ”ማንም ያሸንፍ ማንም እንኳን ይሄ ምርጫ አለፈልን” አለን። አነጋገሩ ምርጫ ተመልሶ እንዲመጣበት የሚፈልግ አይመስልም። ምክንያቱን ለማወቅ በመጓጓት ለምን እንደሆነ አከታትለን ለጠየቅነው ጥያቄ መልስ ሳይሰጠን የአቶ ስየን መንደር ለቀን ወጣን።


ጽዮን ግርማ - ከትግራይ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ