ግዛቸው ሙሉነህ

የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ

“የተከፈተብን መጠነ ሰፊ ወረራ የሕልውና ጉዳይ በመኾኑ የክልሉ መንግሥት የትኛውንም ዐይነት አፍራሽ ግብ ያላቸውን አካላት እኩይ ሴራ አይታገስም” የአማራ ክልል መንግሥት

ኢዛ (ረቡዕ ሐምሌ ፯ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም. July 14, 2021)፦ የሕወሓት የሽብር ቡድን በተከፈተበት ይፋዊ ጦርነት ራሱን ከመከላከል ወጥቶ ወደ ማጥቃት ለመሸጋገር መወሰኑን የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስታወቀ።

በክልሉ ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት በኩል በወጣው መግለጫ፤ እስካሁን ድረስ ክልሉ ወራሪውን ኃይል ለመከላከል እና ለመመከት ብቻ ሲጥር እንደቆየ በማስታወስ፤ ከዚህ በኋላ ግን የክልሉ ልዩ ኃይልና አጠቃላይ የጸጥታ አካላት ወደ ማጥቃት እንዲሸጋገሩ ትእዛዝ ተሰጥቷል ብሏል።

የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ ዛሬ በሰጡት መግለጫ፤ የፌዴራል መንግሥት ያወጀውን የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔ ተከትሎ አሸባሪው ትሕነግ ከስሕተቱ ተምሮ ሕዝብን ከከፋ ስቃይ መታደግ ሲገባው፤ በአማራ ክልል ግዛቶች ላይ መጠነ ሰፊ ወረራ መክፈቱን ገልጸዋል።

የትሕነግ/ሕወሓት ቡድን በራያ አካባቢ አላማጣ፣ ኮረም እና ባላ፤ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ፃግብጅ፣ ዛታ እና አበርገሌ እንዲሁም በወልቃይት ጠገዴ እና ማይጠብሪ ዳግም ወረራ መክፈቱን ገልጸው፤ በወረራው ካህናትን፣ አዛውንቶችን፣ ሴቶችን እና ሕፃናትን ከፊት በማሰለፍ ነውረኝነቱን አሳይቷል ብለዋል።

የክልሉ ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ የትሕነግን ወረራ ስልታዊ በኾነ መንገድ ሲከላከል መቆየቱን ገልጸው፤ “ከዚህ በላይ ትእግሥት የከፋ ዋጋ ስለሚያስከፍል፤ ከዛሬ ጀምሮ ከመከላከል አልፈን ግልጽ ማጥቃት ጀምረናል” በማለት አስረድተዋል።
ትሕነግ ለአገር ብቻ ሳይኾን ለዓለም አቀፍ ስምምነቶችም ተገዥ አለመሆኑን ማረጋገጡን የገለጹት አቶ ግዛቸው፤ የክልሉ መንግሥት የአሸባሪውን አቅም በሚገባ እንደሚያውቀውና በአጭር ቀን ወደ መጣበት እንዲመለስ እንደሚደረግ ገልጸዋል።

ትሕነግ እስካለ ድረስ የአማራ ሕዝብ እና ሌሎች የኢትዮጵያ ብሐረሰቦች ለሕልውናቸው የሚያደርጉት ዘመቻ ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል፤ አስፈላጊው ዝግጅት ጎን ለጎን እንደሚቀጥል አስረድተዋል። የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ ሌሎቹም ክልሎች የሕልውና ዘመቻውን ጥሪ በአዎንታ ተቀብለው ድጋፍ እያደረጉ መኾኑን እና የፌዴራል መንግሥት ድጋፍም ይቀጥላል ሲሉ አቶ ግዛቸው ተናግረዋል።

የትሕነግ ቡድን ለዘመናት ከኢትዮጵያ በዘረፈው ገንዘብ በዓለም አቀፍ ተቋማት እና መገናኛ ብዙኀን ውስጥ የሚገኙ ተላላኪዎቹን ገዝቶ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ መጠነ ሰፊ ጫና እየፈጠረ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ ግዛቸው፤ ሕዝቡ ይህንን ተረድቶ በአንድነት መቆም እና ድጋፍ ማድረግ እንደሚጠበቅበት አሳስበዋል።

የአማራ ክልል መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ “የተከፈተብን መጠነ ሰፊ ወረራ የሕልውና ጉዳይ በመኾኑ የክልሉ መንግሥት የትኛውንም ዐይነት አፍራሽ ግብ ያላቸውን አካላት እኩይ ሴራ አይታገስም” ሲሉ የክልሉን መንግሥት አቋም አንጸባርቀዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ