PM Abiy Ahmed

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ

ወይዘሪት ብርቱካን ሚደቅሳን አመስግነዋል

ኢዛ (ረቡዕ ሰኔ ፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. June 10, 2020)፦ ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. በተካሔደው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስብሰባ ላይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምክር ቤቱ አባላት ከተነሱላቸው ጥያቄዎች መካከል ስድስተኛውን አገር አቀፍ እና ክልላዊ ምርጫን የተመለከተው ይገኝበታል። የምርጫው መራዘምን ተከትሎ በተለይ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ መንግሥት አይኖርም፤ ብጥብጥ ይነሳል በማለት ጭምር እየገለጸ ነው። እንደ ትግራይ ያሉ ክልሎች ደግሞ ምርጫ ካልተካሔደ በክልል ደረጃ ምርጫ እናደርጋለን በማለት እየገለጹ ስላሉት ጉዳይም የቀረበ ጥያቄ ነበር።

በምርጫውና ከዚሁ ጋር ተያይዞ ለቀረቡት ጥያቄዎች ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርጫው እንዲካሔድ ብልጽግና ከፍተኛ ፍላጎት እንደነበረው በማስረዳት፤ “በዚህም ምክንያት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ባልተለመደ መንገድ ጫን ብዬ ጠይቄና አነጋግሬያቸው ነበር” ብለዋል። ወይዘሪት ብርቱካን ግን ለማንም ጫና እና ቁጣ ሸብረክ የሚሉ ሴት ስላልኾኑ፤ ሥራቸውን ባመኑበት መንገድ ስለመሥራታቸውም በማውሳት ምላሻቸውን ቀጥለው የወይዘሪት ብርቱካን እርምጃ ትክክል ነበር የሚል እምነታቸውን አንጸባርቀዋል። “ዛሬ ላይ ስንመለከተው እርሳቸው ትክክል ነበሩ፤ ምስጋና ይገባቸዋል” በማለትም አወድሰዋቸዋል።

“ምርጫው ቢካሔድ ፍላጎታችን ነው፤ ብልጽግና ምርጫ የሚያስፈራው ፓርቲ እንዳልኾነ ለሁሉም ግልጽ ነው፤ ምርጫን በተመለከተ ለጥቂት የወራት ጊዜ ብለን ብዙ ዓመት ዋጋ የሚያስከፍል አካሔድ መከተል የለብንም” በማለት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል። አምስት ቢሊዮን ችግኝ መትከል ከቻልን፤ ምርጫ ለምን አናካሒድም የሚል ውኃ የማያነሳ ክርክር እንደሚሰማ ያስረዱት ዶ/ር ዐቢይ፤ ምርጫ ማካሔድ የማይቻለው ምርጫውን እንዲያስፈጽም ሥልጣን የተሰጠው አካል ምርጫውን ለማካሔድ የዝግጅትና መሰል ሥራዎችን ለማከናወን አልቻልኩም ስላለ ነውም በማለት ያለውን ሁኔታ አስረድተዋል።

ችግኝ መትከል የተቻለው ደግሞ፤ ጉዳዩ የሚመለከተው አካል አስቀድሞ የቅድመ ችግኝ ተከላ ሥራን ስላከናወነና እችላለሁ በማለቱ መኾኑንም በሚመለከት ከምርጫው ጋር በተየያዘ ካነሱት ምላሽ የሚጠቀስ ነው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ