ፍርድ ቤቱ የአቶ ጌቱ ወርቁን የቪዲዮ ማስረጃ አልቀበልም አለ

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ነሐሴ 19 ቀን 2001 ዓ.ም. August 25, 2009)፦ ከግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጋር በተያያዘ ከተከሰሱት ግለሰቦች ውስጥ የንቅናቄው መስራች የሆኑት የአቶ አንዳርጋቸው አባት፣ አቶ ጽጌ ኃብተማርያምን ጨምሮ ሦስት ተከሳሾች ዛሬ የመከላከያ ምስክሮቻቸውንና የሰነድ ማስረጃዎቻቸውን ለፍርድ ቤቱ አቀረቡ።

 

ዛሬ ማክሰኞ ነሐሴ 19 ቀን 2001 ዓ.ም. የዋለው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 2ኛ ወንጀል ችሎት ከግንቦት 7 ንቅናቄ ጋር በተያያዘ ከተከሰሱት 46 ግለሰቦች ውስጥ የ32ቱን ተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎቻቸውን መስማት መጀመሩን ከአዲስ አበባ የደረሰን ሪፖርት አስረዳ።

 

“በእነጄኔራል ተፈራ ማሞ” በሚል ከተከሰሱት ውስጥ በዛሬው ዕለት የመከላከያ ምስክሮቻቸውንና የሰነድ ማስረጃዎቻቸውን ያቀረቡት የ80 ዓመቱ አዛውንት አቶ ጽጌ ኃብተማርያም፣ አቶ ጌቱ ወልዴ እና አቶ ጌቱ ወርቁ ናቸው።

 

በተመሠረተባቸው አምስት ክሶች መከላከያቸውን ካቀረቡት ሁለቱ ተከሳሾች ውስጥ አቶ ጽጌ ኃብተማርያም የሰነድ መከላከያቸውን በጽሑፍ አቅርበው ለፍርድ ቤቱ በንባብ ያሰሙ ሲሆን፤ አቶ ጌቱ ወርቁ ደግሞ የሰውና ቪዲዮ መከላከያዎችን አቀርበዋል። የአቶ ጌቱን ሦስት የሰው የመከላከያ ምስክሮችን ፍርድ ቤቱ የተቀበላቸው ሲሆን፤ የቪዲዮ የመከላከያ ማስረጃዎቻቸውን ግን ፍርድ ቤቱ ሳይቀበላቸው ቀርቷል።

 

አቶ ጌቱ ወልዴ የተባሉት ተከሳሽ ዓቃቤ ሕግ ቀድሞ የመሰረተባቸውን ክስና ያቀረበውን ማስረጃ ፍርድ ቤቱ ተመልክቶ፤ ባለፈው ሐምሌ 30 ቀን በዋለው ችሎት ፍርድ ቤቱ አምኜበታሉ ባለውና ቀለል ያለ ቅጣት ሊያስቀጣቸው በሚችል ወንጀል እንዲከላከሉ መወሰኑን መዘገባችን አይዘነጋም። አቶ ጌቱ ወልዴ በበኩላቸው አራት የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን በመከላከያነት አቀርበዋል።

 

በነገው ዕለትም ፍርድ ቤቱ የቀሪዎቹን ተከሳሾች የመከላከያ ምስክሮችና የሰነድ ማስረጃዎች ለመስማት እንደሚሰየም ታውቋል።

 

ዓቃቤ ሕግ የመሰረታቸው አምስቱ ክሶች “በኅቡዕ በመሰባሰብና ከግንቦት 7 ሕገ ወጥ ቡድን ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ላይ አደጋ ለመጣል፣ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ለመግደል፣ ተቋማትን ለማውደም፣ በመከላከያ ኃይል ላይ ጉዳት ለማድረስ፣ …” የሚሉ መሆናቸው ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ