የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የቅርብ ዘመድ ከአቶ ነጋ ቦንገር ቤት ተይዘው ታስረዋል

Ethiopia Zare (አርብ ሚያዝያ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. May 1, 2009)፦ ባለፈው ሣምንት የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎትና የፌደራል ፖሊስ የጋራ ፀረ-ሽብር ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ ከግንቦት 7 ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪ ናቸው ብሎ ካሰራቸው 35 ሰዎች ውስጥ፤ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ መስራችና የምክር ቤት አባል አቶ መላኩ ተፈራ፣ በኢህአዴግ የትጥቅ ትግል ዘመን ስመጥር የጦር መሪ ብርጋዴር ጄኔራል ተረፈ ማሞ፣ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ አባት የ80 ዓመቱ አቶ ጽጌ ኃብተማርያም እና የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የቅርብ ዘመድ አቶ ጌቱ ወርቁ ይገኙበታል።

 

ከታሳሪዎቹ መካከል የሚገኙት በቀድሞ የቅንጅት አባልነታቸው እስር ቤት የነበሩት አቶ መላኩ ተፈራ ባለፈው አርብ ፒያሳ አራዳ አካባቢ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ተወስደው መታሰራቸውና ፍርድ ቤት ቀርበው እንደነበር ታውቋል።

 

በሌላ በኩል የግንቦት 7 ንቅናቄ መስራች የሆኑት የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አባት የ80 ዓመቱ አቶ ጽጌ ኃብተማርያም ከንቅናቄው ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን፣ በኢህአዴግ የትጥቅ ትግል ዘመን ስመጥር የጦር መሪ የነበሩ የኅዳሴው ዋዜማ በሚለው ዶክመንተሪ ፊልም ከሌፍተናንት ጄኔራል አበባው ታደሰ ጋር በመሆን ስለ ብሔረ አማራ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዲን) የትግል ትውስታ በአስረጂነት የቀረቡ፣ በ1997 ዓ.ም. በመጨረሻ ከሽሬ ግንባር ምክትል አዛዥነታቸው ተዛውረው አዲስ አበባ ተመድበው የሠሩት የወታደራዊ ንዑስ ቡድን መሪ ናቸው የተባሉት ብርጋዴር ጄኔራል ተረፈ ማሞም በቁጥጥር ስር ውለዋል።

 

ሳሪስ አካባቢ ከሚገኘው የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ አባት የአቶ ነጋ ቦንገር መኖሪያ ቤት ባለፈው አርብ ማምሻውን በሠላም አለማደሩን ነበር ምንጮች የጠቆሙት። ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ሲሆን ፖሊሶች ወደ አቶ ነጋ ቦንገር ቤት በመሄድ አቶ ጌቱ ወርቁን እንደሚፈልጉ ተናገሩ፤ የተባለው ግለሰብ የሚኖረው በአቶ ነጋ ቦንገር ቤት ሳይሆን ቤታቸው ፊት ለፊት ባለው የራሳቸው ቤት ከልጃቸው ዳንኤል ነጋ ጋር በአንድ ፎቅ ላይ መሆኑ ተነግሯቸው ወደዚያው አምርተዋል።

 

አቶ ጌቱ ባለትዳርና የልጆች አባት ሲሆን፣ እስከማግስቱ ከቀኑ አስር ሰዓት ድረስ ከፍተኛ ፍተሻ ተደርጎ ወደ እስር ሊወሰድ መቻሉ ታውቋል። እስከዛን ሰዓት ድረስም ከአቶ ነጋ ቦንገር ቤት አንድም ሰው እንዳይገባና እንዳይወጣ ተከልክሎ ነበር።

 

በሌላ በኩል ከግንቦት ሰባት ጋር በተያያዘ ሌሎች ወደ አምስት የሚጠጉ ሰዎች መታሰራቸውንና በጠቅላላ ከተያዙት ውስጥ ሁለት ተጨማሪ ጄኔራሎችና ሰባት የሚሆኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት እንደሚገኙበት ታውቋል።

 

የመጀመሪያዎቹ 35 ሰዎች ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት ፖሊስ 14 ቀን የምርመራ ግዜ ይሰጠኝ ብሎ በማመልከቱ ጊዜ ቀጠሮ የተሰጠው ሲሆን፣ ምንጮች እንደጠቆሙት የተያዙት ሰዎች በሁለት ተከፍለው ተራ ሠራተኞች በዋናው ፍርድ ቤት እንዲዳኙና ጄኔራሎችና የመከላከያ ሠራዊት አባላት ደግሞ በጦር ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ሊታይ ይችላል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ