ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ቦምብ መጠመዱን አቶ ኦባንግ ገለጹ
Ethiopia Zare (ሐሙስ መስከረም 21 ቀን 2002 ዓ.ም. October 1, 2009)፦ ባለፈው ዓርብ መስከረም 15 ቀን 2002 ዓ.ም. በስዊድንና አካባቢው ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር ህዝባዊ ውይይት ያደረጉት “ለአዲሲቱ ኢትዮጵያ የጋራ እንቅስቃሴ” የተሰኘው ድርጅት መሪ የሆኑት አቶ ኦባንግ ሜቶ፤ “ኢትዮጵያ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት ሳይሆን፤ የዘር መለያ የሰፈነበት ቦምብ ተጠምዷል” ሲሉ ገለጹ።
አቶ ኦባንግ በዚሁ ህዝባዊ ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ስላለሰው እና በአጠቃላይ ስለሰብዓዊ መብት መረገጥ፤ እያንዳንዱ ሰው ከራሱ በመነሳት ለሰው ልጅ እኩልነትና መብት መከበር አስተዋጽዖ ማድረግ እንዳለበት ገልጸዋል። ይህንንም ለማድረግ የአስተሳሰብ ለውጥ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

በዚሁ በስዊድን ቆይታቸው አቶ ኦባንግ፤ ከስዊድን የሶሻል ዲሞክራት ፓርት የዓለም አቀፍ ግንኙነት ምክትል ፀሐፊ የሆኑትን ማርቲን ሳንድግሬን በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ አነጋግረዋል። ስዊድን በአሁኑ ሰዓት የአውሮፓ ሕብረት ሊቀመንበር እንደመሆንዋ መጠን የኢትዮጵያ ህዝብ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት እያደረገ ያለውን ትግል እንድትረዳ ጠይቀዋል።
ከዚህም ሌላ በረሃቡና በፖለቲካ እስረኞች ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥተው ከማርቲን ሳንድግሬን ጋር የተወያዩ ተወያይተዋል።
ቅዳሜ መስከረም 16 ቀን 2002 ዓ.ም. ደግሞ የኢትዮጵያን ሰንደቅዓላማ ሉዓላዊነት በተመለከተ በተዘጋጀው ሠላማዊ ሰልፍ ላይ አቶ ኦባንግ ሜቶ ተገኝተው ለሰልፈኞቹ ንግግር አድርገዋል።