Happy Ethiopian Newy Year! መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልዎ!

ስለሺ ዘእንግልጣር This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

“የምንታገለው ለመንደር ወይስ ለሀገር? መታገል ያለብን ለሀገር አነድነት ነው፣ ሀገር ከሌለች መንደር አይኖርምና።”

አቶ ኦባንግ ሜቶ ‘የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የትብብር ንቅናቄ’ መስራች ከተናገሩት ተተርጉሞ የተወሰደ

አተኩሮ ላየው ቅንነቱን ለመረዳት ጊዜም አይፈጅም። በተኮላተፈና ጥርት ባለ አማርኛውም ሆነ አቀላጥፎ በሚናገረው እንግሊዝኛው በጨዋ ኢትዮጵያዊነት ከአፉ የሚወጡት ቃላት ልብ ውስጥ ጠልቀው ይገባሉ። ዘወትር በሄደበት ሁሉ የሚናገረው ኢትዮጵያዊነትን ነው። ሊነግረን የሚፈልገው ልዩነታችንን ወደጎን በመተው እርስ በርሳችን በመነጋገር ችግሮቻችንን እየፈታን አንድነታችንን ማጠንከር እንዳለብን ነው። በዘርና በመሳሰሉት ዛሬ ገዥው ፓርቲ የሚያራምደው የጎሣ ፖለቲካ ውስጥ ገብተን በመዳከር እርስ በርሳችን እንዳንጠላላና እንዳንቀያየም ይማጸነናል። “የነገዪቱ ኢትዮጵያ እጣ ያሰጋኛል፤ ዛሬ ካልተባበርን፣ ኢትዮጵያዊ ነን የምንል ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን መሔድ ካልቻልን፣ ነፃና ፍትሕ የሰፈነባት ዲሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ለማየት የምንጓጓበትን ጊዜ ያርቅብናል እንጂ አያቀርብልንም” ይለናል ኦባንግ።

 

ኦባንግ ሜቶን ዛሬ ከሰሜን አሜሪካ እስከ አውሮፓ፣ ከአፍሪካ እስከ አውስትራሊያ የማያውቀው ኢትዮጵያዊ አለ ለማለት ያስቸግረኛል። የሠላም ጥሪው፣ የፍቅር ጥሪው ከጫፍ እስከ ጫፍ አስተጋብቷል። የነገዪቱን ኢትዮጵያ ሁላችንም አንድ ሆነን ነው የምናቆማት። አድሎ የሌለባት የአንድ ዘር የበላይነት የማይታይባት፣ ሁሉም ሰብዓዊነቱ ተከብሮና እኩል ዜጋ ሆነን የምንኖርባትን ሀገር ለማቆየት ከፈለግን በአንዲት ኢትዮጵያ ጥላ ስር መሰባሰባችን ግድ ይላል።

 

ኦባንግ እንዲህ ይላል፣ “... ስንወለድ ከዚህ ጎሣ እንሁን ብለን ፈልገን አልተወለድንም፣ ወይንም ትግሬ ወይም አማራ ወይም ኦሮሞ ወይም ወላይታ ወይም አኙዋክ ለመሆን ምርጫ አልቀረበልንም። ስንወለድም ይህንን ቋንቋ እንናገር ብለን ፈልገን አላደረግንም፣ ወደዚህ ዓለም ስንመጣ እነዚህን ሁሉ ይዘን አልመጣንም። ...” አባባሉ ትክክል ነው። ከየትኛውም ጎሣ ልንወለድ ወይንም የተወለድንበትን ወይም ያደግንበትን ቋንቋ መናገራችን ኢትዮጵያዊነታችንን በምንም ዓይነት ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ አይችልም።

 

ኦባንግ በተለያዩ የሰሜን አሜሪካ፣ አሜሪካ እንዲሁም በአውሮፓ ሀገሮች በመዘዋወር የተለያዩ ስብሰባዎች ላይ ይህንኑ የኢትዮጵያዊነት፣ የአንድነትን፣ የመተባበርን እና የመከባበር መልዕክቱን በተገኘባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ከመናገር ወደኋላ ያለበት ጊዜ የለም። በነዚህ በተገኘባቸው ስብሰባዎቸ ላይም የታዘባቸውን ለትምህርት እንዲሆነን በምሳሌነት ይጠቅስልናል። ከታዘባቸውም ውስጥ በተለይ በጣም ያሳዘነውና ያስገረመው በተለያዩ ጊዜያት ተጋብዞ ንግግር ለማድረግ በኦጋዴንና በኦሮሞ ተወላጆች ባዘጋጁት ስብሰባ ላይ በተገኘበት ወቅት የስብሰባው ተካፋዮች በሙሉ በእጃቸው ባንዲራ ያውለበልቡ እንደነበርና ባንዲራዎቹ በሙሉ የክልሉ እንደሆኑ፤ ነገር ግን አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀዩን የኢትዮጵያዊነታችን መለያ የሆነው ባንዲራችንን ባለማየቱ ልቡ ክፉኛ እንዳዘነ ነው። ባንዲራ ማንንም አልጨቆነም፤ ባንዲራ ማንንም አልገደለም ይለናል። እኔም የኦባንግን ሃሳብ እጋራለሁ። መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት ብዙ ዓመታትና አሁንም ድረስ በገዥዎችና በአባሎቻቸው የተለያዩ ግፎች ማለትም የመገደል፣ የመታሰር፣ የመሰደድ እና የመሳሰሉት ሁሉ ሲደርስበት ቆይቷል። ነገር ግን አሁን በምንገኝበት ዓለም በተራቀቀበት ዘመን ያለፉትን እያነሱ መነካከስ እና መባላቱ ምን ጥቅም ሊያመጣ ይችላል? ይልቅስ ተነጋግረንና እርስ በርሳችን መተማመን ፈጥረን ሁላችንም በእኩልነት የምንኖርባትን አንዲት ኢትዮጵያን ለመፍጠር ብንሯሯጥ ምናልባት የኢትዮጵያን ትንሣዔ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብዬ አስባለሁ።

 

እዚህ ላይ ለእውነት ስለእውነት ብለን ለሀገራችን እና ለህዝባችን ጥሩ የተሻለ ጊዜ ለማምጣት የምንታገል፤ ከዚህ በፊትም በትግሉ የተፈተንንም ሆንን ለመፈተን እራሳችንን ያዘጋጀን፤ ለአንድ አፍታ ቁጭ ብለን ያለፉትን ጊዜያት ወደኋላ ዞር ብለን እናስብ። ምን ያህል ለእራሳችንም ሆነ ለምንታገልለት ህዝብ የሚያረኩ ተግባራትን ፈጽመናል? ትግሉንስ ምን ያህል ወደፊት እንዲራመድ አስተዋጽዖ አድርገናል? ይህን አድርጌያለሁ ብሎ የሚያስብ ኢትዮጵያዊ ካለ በጣም ጥሩ ነው። ለእኔ ግን መሥራት ከሚገባን 1 % (አንድ በመቶ) እንኳን ሠርተናል ለማለት ይቸግረኛል። በእውነቱ ችግራችን ምንድነው? በእኔ አመለካከት ችግራችን አለመነጋገር፣ አለመወያየት፣ የሌሎችን ሃሳብ መናቅና የእኔ ብቻ ነው ትክክል የማለት፣ የብዙኀኑን ድምፅ አለመቀበል፣ ብሎም አፈንግጦ መውጣትና ሌሎች ብዙ ጥሩ ሥራ ሊሠሩ የሚችሉትን ያልሆነ ስም በመስጠት በመተቸትና ስም በማጥፋት እንካ ሰላንቲያ ውስጥ በመግባት ብዙ ሥራ ሊሠራ የሚችልበትን ጊዜ በከንቱ ማጥፋት፤ ... ያውም እነዚህ በጣም ጥቂቶቹ ናቸው። እያንዳንዳችን ችግራችን ምን እንደሆነ ጠንቅቀን እናውቃለን፤ ነገር ግን እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ከራሳችን በመነሳት ምን ያህል ጥረት ለማድረግ ጀምረናል? እንዴት ባለ መንገድ ሁላችንም እየተነጋገርን እና እየተወያየን በመካከላችን ያሉትን ችግሮች እየፈታን በመተማመን ወደፊት የምንሄድበትን መንገድ መጥረግ እንችላለን?

 

በዚህ ላይ የራሴን አስተያየት ለመስጠትና መፍትሔ ይሆናል ብዬ የማቀርበው ሃሳብ እንደሚከተለው ነው፦

 

1. ራስን ማወቅ፦ በመጀመሪያ እራሳችንንና ዓላማችንን በደንብ እንወቅ። በምንሠራው ሥራ ላይ በቂ እውቀት አለኝ፣ ከኔ በላይ የሚያውቅ ማንም የለም፣ እኔ ያልኩት ብቻ መሆን አለበት ብሎ መነሳት በራሱ የመጀመሪያው ወደ ጥፋት የሚወስድ በመሆኑ ከዚህ አይነት አስተሳሰብ ራስን ማግለል። በራስ መተማመን በራሱ ምንም ጉዳት የለውም፤ ግን የበለጠ ውጤት የሚኖረው የሌሎቸን ሃሳብ እና ፍላጎት መቀበልና ማስተናገድ የሚችል ተፈጥሮ ሲኖር ብቻ ነው።

 

2. በውይይት እና በመነጋገር ማመን፦ መወያየት፣ መነጋገር እና የሌሎችን ሃሳብ መስማት፤ ከሰሙም በኋላ ይሄ ይጠቅማል ብሎ የሚጠቅመውን መያዝና ወደ ሥራ መተርጎም ወይም ደግሞ የተሰጠው ሃሳብ ለጊዜው ሊጠቅም የማይችል ከሆነ ወደፊት ሊጠቅም ይችላል ብሎ ማሰብና መያዝ፤ አሊያም ሃሳቡን ውድቅ ማድረግ፤ ግን ሃሳቡን ያቀረበውን ግለሰብ አክብሮት መስጠት። ግለሰቡም የታዳሚውን ውሳኔ ተቀብሎ አብሮ ለመጓዝ መስማማት።

 

3. መደማመጥ መቻል፦ ብዙውን ጊዜ በተለይ በስብሰባዎች ላይ ችግር የሚገጥመን አንዱ በሚናገርበት ጊዜ ሌሎቻችን ማዳመጥ አለመቻላችን ነው። ይህንንም ማረጋገጥ የምንችለው ተደጋጋሚ የሆኑ ሃሳቦች ወይንም ጥያቄዎች በተለያዩ ሰዎች ሲሰነዘሩ መታየት፤ አንዳንድ ሰዎችን ከዚህ በፊት በግል ባለን ቅሬታ ወይንም አመለካከት ወይንም ‘ይሄ ደግሞ ምን ያውቃል’ በሚል ንቀት በተሞላበት ሁኔታ የተነሳ ገና ሃሳባቸውን ሊሰጡ ሲነሱ ከመጀመራቸው በፊት መጨረሳቸውን የምንጓጓ ጥቂት አይደለንም። ስለዚህም የሚናገሩት ሃሳብ እንኳን ጥሩ እና ገንቢ ቢሆንም ለማዳመጥ ዕድል ስላልሰጠነው ጊዜን ከማባከን ውጪ የሚፈይደው ነገር ላይኖር ነው።

 

4. መተማመን መፍጠር፦ አብረን ለመጓዝ እንድንችል መተማመን በመካከላችን መፍጠር ያስፈልጋል። ይህም ሊፈጠር የሚችለው በደንብ መተዋወቅ ሲኖር፣ አሰተያየታችንን አጥብበን ሳይሆን ሰፋ አድርገን ብዙ ነገሮችን ማየት ስንችል፣ ብሎም እርስ በርሳችን በሃሳብም ሆነ በሌላው መደጋገፍ ስንችል፣ ሰዎችን በቅድሚያ ሰብዕናቸውን (ሰው መሆናቸውን) እንጂ ዘር ጎሣ ቋንቋና ቀለም የመሳሰሉት አንዱን ከፍ ሌላውን ዝቅ እንደማያደርግ ተገንዝበን ለአንድ ዓላማ አብረን እንቁም ያሉንን ወንድሞችና እህቶች በመያዝ ግንኙነታችንን እያሰፋን፣ ካለፈው እየተማርን፣ ዛሬን እየሠራንበትና መጪው ጊዜ ብሩህ እንደሚሆን በማመን መጓዝ መተማመንን ሊፈጥር ይችላል። ግን ከሁሉም በላይ ቅን ልቦና እንዲኖረን ግድ ይላል።

 

5. ይሉኝታንና ሐሜትን ማስወገድ፦ እኛ ኢትዮጵያውያንን እንደ በሸታ ከሚያጠቁን ነገሮች ውስጥ ይሉኝታና ሐሜት ዋናዎቹ ናቸው። ይሉኝታ የሚያስፈልግበት ቦታና ጊዜ ቢኖረውም በተለይ በግል ሕይወታችን አብዝተን ብንጠቀምበትም የማይጎዳን ሲሆን ነገር ግን ከፍተኛ ጥንቃቄን በሚጠይቁና ለህዝብ እና ለሀገር በሚደረጉ ሥራዎች ላይ የሚያመጣው ጉዳቱ እንዲህ ቀላል አይሆንም። አንድን ግለሰብ በጓደኝነትም ሆነ በዝምድና ወይንም በሌሎች ባሉን ቅርበቶች ምክንያት ግለሰቡ በሚሰነዝራቸው አስተያየቶች ወይንም ለህዝብ እና ለሀገር በሚሠራቸው ሥራዎች ላይ ስህተቶች እያየን በይሉኝታ ተይዘን በጭፍን ድጋፋችንን የምንቸር ከሆነ ልናደርስ የምንችለው ጉዳት ቀላል አይሆንም። ሐሜትም ሌላው ጎጂ የሆነ ፊት ለፊት ከሚመለከተው ጋር ከመነጋገር ይልቅ በጓሮ በር ግለሰቦች በማያውቁት መንገድ የሠሩበትን እንዳልሠሩ፣ የደከሙበትን እንዳልደከሙ አድርጎ ከሌሎች ጋር በመሆን የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄድ ለሀገርና ለወገን የምናደርገውን ትግል የሚያዳክም እንጂ የሚያጠናክር እንደማይሆን ግልፅ ነው። ለመሥራት ቆርጠው የተነሱትንም ሆነ የደጋፊዎቻቸውን ልብ እና ቅስም ሰባሪ ሆኖ ሁሉንም ከትግሉ መንደር የሚያርቅ ዕኩይ ሥራ ሊሆን ይችላል።

 

6. ድክመትንና ተጠያቂነትን መቀበል መቻል፦ በሀገራችን ከድሮም ጀምሮ እንደ ባህል ይዘነው እስካሁን ድረስ ልናሻሽላቸው ያልቻልናቸው ሁለት ነገሮች ውስጥ ድክመትን መቀበል እና ለሀገር እና ለወገን ለሚሠሩ ሥራዎች በተለይ በግለሰቦችም ሆነ በቡድን ለሚደርሰው ውድቀት ተጠያቂነትን የመቀበል ልምድ አለመኖር ናቸው። ይህ ደግሞ ባለፉት ጊዜያት ያየናቸው በተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ለተከሰቱት ችግሮች ተጠያቂ አለመኖሩ በህዝብና በደጋፊዎች ዘንድ ክፍፍልን ሊፈጥር በቅቷል። ነገር ግን ነገሮችን ከመሸፋፈን እና በውስጥ በአሠራርና በግለሰቦችም መካከል ቢሆን አሉ የሚባሉትን ችግሮች ተወያይተውበት ግልፅ በሆነ መንገድ ያሉትን ድክመቶች ግልፅ አድርጎ ማውጣትና ለችግሩ ተጠያቂ የሚሆኑትን በመረጃ በመደገፍ የማሳወቅ አሠራር ቢኖር ተጠያቂ የሚሆኑትን ቢቻል ተጠያቂነታቸውን አምነው ያለውን ስህተት አርመው ደጋፊዎቻቸውን ይቅርታ በመጠየቅ የሚሰጡትን አገልግሎት እንዲቀጥሉ የማድረግ አሠራር በመልመድ የቀድሞውን መጥፎ የአሠራር ልምድ መቀየር አስፈላጊ ነው። ቢቻል ለደረሱ ጉዳቶች ተጠያቂ መሆንም ሆነ በሥራ ላይ ድክመት ካለ ድክመትን አምኖ ለተተኪ ቦታውን መልቀቅ ሙሉ በሙሉ በራስ ፍቃደኝነት ቢሆን ይበልጥ ብልህ ያሰኛል በዛውም መጠን ለሀገር እና ለወገን ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ይሆናል።

 

በተለይ ለብዙ ዓመታት ቁልፍ ቦታዎችን በመያዝ ምንም ለውጥ ያልታየባቸው አንዳንድ የፖለቲካ መድረኮችን በብዛት እያየን ነው። እነዚህ መድረኮች አሠራራቸውን በአፋጣኝ መገምገምና በእውነት ትግላቸው ለዲሞክራሲ ከሆነ ዲሞክራሲያዊ አሠራርን ራሳቸው በውስጣቸው ማስፈንና ድክመት ያለባቸውን ቦታዎችና ግለሰቦች እየገመገሙና ሊሠሩ በሚችሉ እውቀቱና ጉልበቱ ባላቸው እየተተኩ ለውጥ ሊያመጣ የሚችል ሥራ እንዲሠራ ጥረት ማድረግ ያስፈልጋል።

 

እንግዲህ ከላይ የተዘረዘሩትን ለማሟላት አስፈላጊውን ጥረት ካደረግን በኋላ ከማንኛውም ዓላማችን አንድ ከሆነና የተለያዩ ጥቃቅን ሃሳቦች ቢያለያዩንም ነገር ግን ግባችን አንድ እና ያውም ሀገርን ማዳን ከሆነ በመካከላችን ዋናውና ትልቁን መተማመንን በመፍጠር መንገዳችንን እየጠረግን መሄድ ያስፈልገናል።

 

በአሁኑ ወቅትና ሰዓት ለእኛ ለኢትዮጵያውያን የሚያስፈልገን ምንድነው?

 

መወያየትና መነጋገር፦ ኢትዮጵያውያን በአሁኑ ወቀት የውይይት መድረክ በመፍጠር ባሉብን ችግሮች ላይ መወያየት እና ለችግሮቻችን መፍትሔ በመፈለግ አንዱ ሌላውን ጠልፎ ለመጣል ምክንያት እንዳይሆን መፍትሔዎችን መፈለግ ያሻል።

 

ለምሳሌ በዋሽንግተን ዲ.ሲ. ‘ውይይት ለሠላምና ለጋራ ዓላማ በኢትዮጵያ’ በሚል ስም ተጀምሮ በሚቀጥለው ጁን 28 ቀን 2009 ዓ.ም. ለሦስተኛ ጊዜ በኢትዮጵያውያን መካከል የሚደረገው ውይይት በትልቅ ምሳሌነት ሊወሰድ ይችላል። ሌሎችም ኢትዮጵያውያን ባሉባቸው ከተሞችም ሆነ ክልሎች የዚህን አይነት መድረክ በመፍጠር መነጋገሩ በመካከላችን በደንብ መተዋወቅና ብሎም መተማመን ስለሚፈጥር ይህ ትውውቅና መተማመን ደግሞ ጥሩና ዘለቄታ ያለው ሥራ ለመሥራት ትልቅ መንገድ ከፋች ይሆናል።

 

በእነዚህ ውይይቶች የጋራ ችግሮቻችንን፣ የስብሰባ ባህላችንን (ከሰዓት ማክበር ጀምሮ የሌላውን ሃሳብ እስከማክበር ድረስ)፣ ካለንበትና ከምንኖርበት ሀገር ስላለው ዲሞክራሲ መማርና ማዳበር ስለሚገባን ልምድ፣ ሀገራችንን በልማት ደረጃ እንዴት መርዳት እንደምንችል (ድሃውን ህዝብ አለንልህ ከአጠገብህ ነን ለማለት)፣ በመወያየትና በመማማር የራሳችንን እውቀት ከማዳበር አልፈን በመካከላችን ሠላም ፈጥረን በሀገራችን ላይ ለውጥ ለማምጣት ጥረታችንን መቀጠል ይኖርብናል። ይህ ውይይት ለግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በፓርቲዎች ደረጃም አስፈላጊነቱ ታምኖበት በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ ለማምጣት እንታገላለን የሚሉ ፓርቲዎችም ሆኑ ንቅናቄ ቡድኖች ለብቻ የሚመጣ ውጤት አለመኖሩን ተገንዝበው የውስጥ አሠራራቸውን ጠብቀው በሀገር ጉዳይ ግን የጋራ አቋም በመያዝ ለውይይቱ እራሳቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል።

 

ወጣቱን ትውልድ የሀገርና የወገን ፍቅር እንዲኖረው ማድረግና በትግሉ ውስጥ ተሳትፎ እንዲያደርግ ማድረግ

 

እወነት እንነጋገር ከተባለ ባሁኑ ወቅት አብዛኛው ወጣት ስለ ሀገር ጉዳይ “እንዴት ነው?” ተብሎ ሲጠየቅ፤ “እባካችሁ ተዉኝ! ፖለቲካ ማውራት አልወድም/አልፈልግም” የሚል መልስ ነው የሚያሰማው። ይህ ማለት ደግሞ ሁሉም ወጣት ነው ማለት አይደለም። ባሁኑ ወቅት ከፍተኛ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ወጣቶች የሉም ማለት አይደለም፤ አሉ። ግን ብዙኀኑ የፍርሃት ይሁን ወይንም ተስፋ የመቁረጥ ራሳቸውን ሲያገሉ ነው የሚታዩት። እርግጥ ነው እኛ ትላልቆቹ በመጀመሪያ ካለፈው ስህተታችን በመማር ልባችንን ከፈት፣ አዕምሯችንን ሰፋ አድርገን በመሰማማትና በመደማመጥ ደካማ ጎናችንን በማጠናከር ወጣቱን ወገናችንን ከኛ ጥሩ ነገር እያየና እየተሳበ ሀገሩንና ወገኑን የሚወድ ትውልድ የማድረግ ኃላፊነቱ የሁላችንም ነው። አለበለዚያ ግን እኛም በራሳችን እያዘንን ወጣቱ ትውልድም በእኛ እያዘነብን፣ ሀገራችንንም ምንም ለውጥ ሳይታይባት እንደውም ጭራሽ ድህነቷ እየባሰባት የልመናና የረሃብ ምሳሌ አድርገናት ለሚቀለው ትውልድ የምናስተላልፋት ከሆነ ትውልድም ይፈረድብናል።

 

እንግዲህ ከላይ የዘረዘርኳቸውን ችግሮቻችንና በመጠኑም ቢሆን መፍትሔ ሃሳቦች ይሆናሉ ያልኳቸውን በመነሻነት ሁላችንም በመገንዘብ አብረን በመሥራት ወደፊት የምንጓዝበትን መንገዶች ማጠናከር እና ውጤቱንም ለማየት የምንበቃበትን ጊዜ ላማሳጠር ሁላችንም የተቻለንን እንሞክር። በተናጠል ወይንም ግለሰቦችንም ሆነ ቡድኖችን በማምለክ ያሳለፍነው ጊዜ ውጤቱ ምን እንደሆነ አይተነዋልና፣ ወደፊትም ሥልጣን ይዞ ለህዝብ ተገዝቶ ህዝብን በሚፈለገው መንገድ የሚመራ መንግሥት ለማየትም ዋስትና አይኖረንም። ስለዚህ ሁላችንም በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምንኖር በአዲሲቷ ኢትዮጵያ ስር አንድ ሆነን ከተሰባሰብን ድምፃችን የጎላና በምንም ሆነ በምን ህዝብን አስተዳድራለሁ ብሎ ሥልጣን የሚይዝ መንግሥት ፈላጭ ቆራጭ የማይሆንበትን፣ አስተማማኝ የሆነ ህዝብ ድምፁን ሰጥቶ የራሱን መሪ የሚመርጥበትን ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በሀገራችን ለማስፈን አንድነታችን፣ መሰባሰባችን፣ መወያየታችን፣ መተዋወቃችን፣ ተዋውቀንም በመካከላችን መተማመን መፍጠር ከሁሉ በላይ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ። ለዚህም ነው በኦባንግ ሜቶ ‘የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የትብብር ንቅናቄ’ ጥላ ስር ሁላችንም በመሰባሰብ ከሁሉ ነገር ሰብዓዊነታችንን እና ከዛም ኢትዮጵያዊነታችንን አስቀድመን ለአንዲት ሀገር አንድነት ዕድገትና ሕልውና እንረባረብ የምለው።

 

ይህንን ሙሉ በሙሉ የራሴ የሆነውን ሃሳብ በመደገፍም ሆነ በመቃወም ወይንም ጠቃሚ ነው የምትሉትን በውስጡ ያላካተትኩትን ሃሳብ ለመሰንዘር የምትፈልጉ እንነጋገርበት፣ እንወያይበት፣ የናንተንም ለመስማት ዝግጁ ነኝ። ከላይ ከጠቀስኳቸው ውስጥ ስህተቶች ካሉም ለመታረም ዝግጁ ነኝ። ምናልባት የማከብረው ወንድሜን የአቶ ኦባንግ ሜቶን ሃሳብ አዛብቼ አቅርቤ ከሆነ የኔ የራሴ በትክክል አለመገንዘቤ (mis-understanding) ሆኖ እንዲታይልኝ በማክበር አሳስባለሁ። በዚሁም አጋጣሚ ወንድሜ ኦባንግን በመላው ዓለም በመዞር የታፈነውን የኢትዮጵያን ህዝብ ድምፅ ለዓለም ህዝብ እንዲያስተጋባ ያለዕረፍት ለሚያደርገው ትግል አድናቆቴን ልቸር እወዳለሁ። ልክ እንደሱም በምትችሉት ሁሉ አስፈላጊውን ትግል ለምታደርጉት ሁሉ ቀጥሉበት! በርቱ! እንበርታ! እላለሁ።

 

ከዚህም በላይ የበለጠ ለመረዳትና ግንዛቤ ለማግኘት www.solidaritymovement.org የሚለው ድረ ገጽ ውስጥ ገብቶ ማንበብ ይቻላል።

 

እንወያይበት! እንነጋገርበት!

ተባብረን የኢትዮጵያን ትንሣዔ እናፋጥን!

ከምስጋና ጋር፣ ቸር ይግጠመን! ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!


 

ስለሺ ዘእንግልጣር This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!