መኢአድና መድረክ በጣት ምልክት ተወዛገቡ
Ethiopia Zare (አርብ ታህሳስ 9 ቀን 2002 ዓ.ም. December 18, 2009)፦ ግንቦት 2002 ዓ.ም. እንደሚካሄድ በሚጠበቀው ምርጫ ለመለያ የሚሆን ምልክታቸውን ካስገቡት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ስምንት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያቀፈው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ እና በኢ/ር ኃይሉ ሻውል የሚመራው መኢአድ (የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት) በአውራ ጣት ምልክት ይገባናል ጥያቄ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል።
መድረክ የአውራ ጣት ምልክቴን ለምርጫ ቦርድ ያስገባሁት ድርጅቱ የመመስረቻ ሰነዱን በሚያስገባበት ወቅት ነው ሲል፤ መኢአድ በበኩሉ አውራ ጣትን እንደ ምርጫ ምልክት አድርገን ለምርጫ ቦርድና ለህዝብ ይፋ ያደረግነው እኛ ነን ብሏል።
የሁለቱን ድርጅቶች ውዝግብ በሚመለከት ምርጫ ቦርድ እስካሁን ምንም አይነት ምላሽ ያልሰጠ ሲሆን፤ በቅርቡ ውሳኔ በመስጠት ውጥረቱን ያረግበዋል ተብሎ ይጠበቃል።



