ዶ/ር ብርሃኑንና አቶ አንዳርጋቸውን ጨምሮ አምስት ሰዎች ሞት ተፈረደባቸው
33ቱ ተከሳሾች የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት፣ ሁለቱ የ10 ዓመት ጽኑ እስራት ተፈረደባቸው
የአምስቱ ንብረት እንዲወረስ ተወሰነ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ታህሳስ 13 ቀን 2002 ዓ.ም. December 22, 2009)፦ ከግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጋር በተያያዘ “ሕገመንግሥቱንና ሕገመንግሥታዊ ሥርዓቱን በኃይልና በትጥቅ አመጽ ለመጣል ሲንቀሳቀሱ ተደርሶባቸዋል” በሚል በፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ከተከሰሱትና በአምስቱም ክሶች ጥፋተኛ ከተባሉት 40 ግለሰቦች ውስጥ የግንቦት ሰባት መሥራቾችና አመራሮች ውስጥ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ አቶ መስፍን አማን እና አቶ ሙሉነህ እዩኤል፤ እንዲሁም በእስር ቤት የሚገኙት አቶ መላኩ ተፈራ በዛሬው ዕለት የሞት ቅጣት ተፈረደባቸው። የሞት ቅጣቱን የወሰነው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ነው።
ከዚህም ሌላ ፍርድ ቤቱ 33ቱን ተከሳሾች የዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት የፈረደባቸው ሲሆን፣ ሁለቱን ተከሳሾች ደግሞ በ10 ዓመት እስራት እንዲቀጡ ሲል ወስኗል።
ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን ጨምሮ በአምስቱ ተከሳሾች ላይ የሞት ቅጣት የፈረደበትን ምክንያት ፍርድ ቤቱ ሲገልጽ፤ ተከሳሾቹ ከዚህ በፊት በሌላ ተመሳሳይ ወንጀል ተከስሰው ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተው የእስር ቅጣት ተወስኖባቸው በምህረት ከተለቀቁ በኋላ፤ በድጋሚ ተደራራቢ ወንጀል በመፈፀማቸው ቅጣቱን ለማቅለል የሚያስችል ሕጋዊ ምክንያት ባለመኖሩ ነው ብሏል።
በተከሰሱበት በአምስቱም ክሶች ጥፋተኛ የተባሉትና በዛሬው ዕለት የዕድሜ ልክ እስራት ከተፈረደባቸው 33ቱ ውስጥ 24ቱ ክሳቸውን ሲከታተሉ የቆዩት በእስር ሆነው ሲሆን፣ ዘጠኙ ደግሞ ጉዳያቸው በሌሉበት ነበር ሲታይ የቆየው። ክሳቸውን በእስር ሆነው ሲከታተሉ የነበሩትና በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ የተወሰነባቸው ስም ዝርዝር እንደሚከተለው ይገኛል።
ጄነራል ተፈራ ማሞ፣ አቶ አሳምነው ፅጌ፣ ሌ/ኮ ደምሰው አንተነህ፣ ሻለቃ መኮንን ወርቁ፣ አቶ አበረ አሰፋ፣ ሌ/ኮ ዓለሙ ጌትነት፣ ሌ/ኮ ሠለሞን አሻግሬ፣ ሌ/ኮ ጌታቸው ብርሌ፣ ሻምበል ተመስገን ባይለየኝ፣ ሌ/ኮ ፋንታሁን ሙሃባ፣ ሻለቃ መሰከረ ካሣ፣ ሻምበል ምስጋናው ተሰማ፣ አቶ ክፍሌ ስንሻው፣ የሽዋስ መንገሻ፣ መንግሥቱ አበበ፣ ወይዘሮ እማዋይሽ ዓለሙ፣ አቶ ጎሽይራድ ፀጋው፣ ሳጅን አመራር ባያብል፣ ምክትል ሳጅን ጎበና በላይ፣ ረዳት ሳጅን ይበልጣል ብርሃኑ፣ ምክትል ሳጅን የሺዋስ ምትኩ፣ አቶ ውድነህ ተመስገን፣ አቶ ጌቱ ወርቁ (የዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ዘመድ)፣ እና ፅጌ ኃብተማርያም (ከ80 ዓመት በላይ የዕድሜ ባለፀጋ የሆኑትና የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ወላጅ አባት) ናቸው።
ጉዳያቸው በሌሉበት የታየውና በዕድሜ ልክ ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ የወሰነባቸው ዘጠኙ ተከሳሾች ሌተና ኮሎኔል አለሁበል አማረ፣ አቶ ያረጋል ይማም፣ አቶ ዳንኤል (ዳን)፣ አቶ አወቀ አፈወርቅ፣ አቶ ኤፍሬም ማንዴቦ፣ አቶ ዳንኤል አሰፋ፣ አቶ ቸኮል ጌታሁን፣ አቶ ፋሲል የኔዓለም እና ጋዜጠኛ ደረጀ ሀብተወልድ ናቸው።
በአስር ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጡ ፍርድ ቤቱ የወሰነባቸው ሁለቱ ተከሳሾች አቶ አዱኛ ዓለማየሁ እና አቶ አደፍርስ አሳምነው ናቸው። የሁለቱን ተከሳሾች ቅጣት አስመልክቶ ፍርድ ቤቱ በሰጠው ማብራሪያ፤ ተከሳሾቹ ወንጀሉን መፈፀማቸውን ዘግይተውም ቢሆን ስላመኑና ስለተፀፀቱ ቅጣቱን እንዳቀለለላቸው ገልጿል።
ከዚህም ሌላ በሌሉበት የቅጣት ውሳኔ የተላለፈባቸውን ተከሳሾች ፖሊስ አድኖ በመያዝ ቅጣቱን እንዲያስፈጽም ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በኢትዮጵያ ሕግ መሠረት የሞት ቅጣት ተፈፃሚ የሚሆነው የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር (ፕሬዝዳንት) የሆኑት የመቶ አለቃ ግርማ ወልደጊዮርጊስ በፊርማቸው ሲያፀድቁት መሆኑ ይታወቃል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዓቃቤ ሕግ ንብረታቸው ይወረስልኝ ሲል ጥያቄ ካቀረበባቸው ከስምንቱ ተከሳሾች ውስጥ የአምስቱ እንዲወረስባቸው ፍርድ ቤቱ ወስኗል። የግል ንብረቶቻቸው የቤተሰቦቻቸውንና የሦስተኛ ወገንን መብት በማይነካ መልኩ እንዲወረስባቸው የተወሰነባቸው ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ፣ ኮሎኔል አለሁበል አማረ፣ አቶ ጌቱ ወርቁ እና አቶ ያረጋል ይማም ናቸው።



