የብርቱካንን ምስል በቲሸርት ማሠራት ያስቀጣል
ቲሸርት የለበሱ ወጣቶች ለአንድ ቀን ታሰሩ
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ታህሳስ 24 ቀን 2002 ዓ.ም. January 2, 2010)፦ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ፕሬዝደንት ወ/ት ብርቱካን ሚዳቅሳን ምስል በቲሸርትም ሆነ በሌላ መንገድ ይዞ መንቀሳቀስ እንደሚያስቀጣ ተገለጸ።
ሰሞኑን የብርቱካን ምስል ያለበትን ቲሸርት ለብሰው ለአንድ ቀን ያህል የታሠሩትን ሰባት ሰዎች አስመልክቶ ይፋዊ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም። የፖሊስ ምንጮች እንደገለጹት የብርቱካን ፖለቲከኝነት ከሌሎቹ ፖለቲከኞች በላይ መንግሥትን የሚያሰጋ እንደሆነ ገልጸው፤ በተለይ ከዚህ በኋላ እስከ ምርጫው መዳረሻ የብርቱካንን ምስል መልበስ ይቅርታ ሊያሰጥ እንደማይችልና በቅርቡ ታስረው እንደተለቀቁት ወጣቶች በእስር ብቻ እንደማያበቃ ጠቁመዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ወ/ት ብርቱካን የታሰረችበት አንደኛ ዓመት ታህሳስ 20 ቀን የተባረሩት የአንድነት አባላትና አባራሪዎቹ የአንድነት አባላት ለየብቻ አክብረዋል። “መርኅ ይከበር!” በሚል ያፈነገጡት የፓርቲ አባላት ለተወሰነ ጊዜ በፓርቲው ጽ/ቤት የተደረገውን ዝግጅት ተሳትፈው የነበረ ሲሆን፤ ኢንጂንየር ግዛቸው ንግግር በሚያደርጉበት ወቅት ግቢውን ለቀው በመውጣት ለብቻቸው ጧፍ በመለኮስ ከግቢው ውጭ አክብረዋል።
የወ/ት ብርቱካን እናት ለጠቅላይ ሚንስትሩ ልጄ እንድትፈታ እግርዎ ሥር ተደፍቼ ይቅርታ እለምንዎታለሁ በማለት ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወቃል።