የወ/ት ብርቱካን የአራት ዓመት ልጅ በቃሊቲ እስር ቤት ተንሰቅስቃ አለቀሰች
ወ/ት ብርቱካንን መጠየቅ አይቻልም፤ እናትና ልጃቸው ብቻ ተፈቀደላቸው
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ታህሳስ 25 ቀን 2001 ዓ.ም. January 03, 2009)፦ ቅዳሜ ዕለት ወ/ት ብርቱካንን ቃሊቲ ወሕኒ ቤት ለመጠየቅ የሄዱ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ለረዥም ሰዓታት እንዲጠብቁ ከተደረገ በኋላ ገብተው እንዳይጠይቋቸው ተከለከሉ። የወ/ት ብርቱካን ወላጅ እናትና የአራት ዓመት ሕፃን ልጃቸው ብቻ ለ40 ደቂቃ አገኟቸው። ሕፃንዋ ልጃቸው ከቃሊቲ እስር ቤት ስትወጣ ተንሰቅስቃ አለቀሰች።
ወ/ት ብርቱካንን ለመጠየቅ ቅዳሜ ከጠዋት ጀምሮ በቃሊቲ ወሕኒ ቤት ወረፋ ሲጠብቁ የነበሩ በርካታ ደጋፊዎቻቸው፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ አባላት፣ ጓደኞቻቸው፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸውና ቤተሰቦቻቸው፤ በር ላይ በነበሩ ጠባቂዎች “ወ/ት ብርቱካንን መጠየቅ የሚቻለው ከቀኑ 6 ሰዓት እስከ 7 ሰዓት ድረስ ነው” ተብለው ለረዥም ሰዓታት ለመግባት ከአካባቢው ብዙም ሳይርቁ ሲጠባበቁ ይቆያሉ። በመጨረሻም ሰዓቱ ከደረሰና ከስድስት ሰዓት ጀምሮ እስከ ሰባት ሰዓት ድረስ በሩ ላይ እንዲጠብቁ ከተደረጉ በኋላ ከቀኑ ሰባት ሰዓት ላይ ወ/ት ብርቱካንን በዕለቱ መጠየቅ እንደማይቻል ይነገራቸውና ወደየቤታቸው እንዲሄዱ ይነገራቸዋል።
ምንም እንኳን በወሕኒ ቤቱ ጠባቂዎች ወ/ት ብርቱካንን መጠየቅ እንደማይቻል የተነገራቸው ቢሆንም አንዳንድ የቅርብ ዘመዶች መላ በመፍጠር ሌላ ሰው ጠያቂ በመምሰል ወደ ውስጥ ዘልቀው ይገባሉ። እናም ታሳሪዎችና ጠያቂዎች በሚገናኙበት ቦታ ላይ ሲደርሱ፤ በሥፍራው ለሚገኙ የወሕኒ ቤቱ ፖሊሶች ወ/ት ብርቱካንን ለመጠየቅ እንደመጡ ይገልፃሉ።
በዚህን ጊዜ ፖሊሶቹ ወ/ት ብርቱካን መጠየቅ እንደማይቻል ቢገልጹም፤ የወ/ት ብርቱካን እናት መኖራቸውንና እሳቸው እንዲጠይቋቸው እንዲፈቀድላቸው አንዱን ፖሊስ ይጠየቃሉ። ፖሊሱም ወደ ውስጥ ገብቶ ለጥቂት ደቂቃ ከቆየ በኋላ በመጨረሻም ተመልሶ በመውጣት የወ/ት ብርቱካን ወላጅ እናት ብቻ እንዲገቡ ይፈቀድላቸዋል። እናትየውም የወ/ት ብርቱካን ልጅ የሆነች የአራት ዓመትዋ ሕፃን ሐሌ አብራቸው ገብታ እናትዋን እንድትጠይቅ ይማፀናሉ። እናም ፈቃድ አግኝተው ሁለቱ ብቻ ወ/ት ብርቱካንን ለ40 ደቂቃ ጠይቀው እንደወጡ በሥፍራው የነበሩ የዓይን እማኞች ለኢትዮጵያ ዛሬ ገልፀዋል።
እነኝሁ የዓይን እማኞች ሕፃን ሐሌ ሚደቅሳ እናትዋን ከማግኘቷ በፊት ደስታ በተቀላቀለበት ገጽታና አንደበት “ቡቴን አስፈታታለሁ፤ አብራኝ እቤት ትሄዳለች” ስትል እንደነበረና፤ ነገር ግን ወላጅ እናትዋ የሆኑትን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ከአያትዋ ጋር ጠይቃ ስትወጣ በፊትዋ ላይ የነበረው የደስታ ገጽታ ጠፍቶ በዝምታ ተውጣ ነበር። በመጨረሻም ከወሕኒ ቤቱ ደጃፍ ላይ ስትደርስ “ዋይ” በማለት ልክ እንደ ትልቅ ሰው ተንሰቅስቃ ለረዥም ጊዜ ያለቀሰች ሲሆን፣ “ምን ሆነሻል?” በማለት ቢጠይቋትም ምንም አይነት ምላሽ ሳትመልስ ስታለቅስ እንደነበር ከዓይን ምስክሮቹ ቃል ለመረዳት ችለናል። የሕፃን ሐሌን ለቅሶ የተመለከቱና ማንነቷን ያወቁ በአካባቢው የነበሩ በርካታ ሰዎችም ልባቸው በኀዘን የተነካ ሲሆን፣ አንዳንዶቹም ማልቀሳቸውን የዓይን ምስክሮቹ ለኢትዮጵያ ዛሬ አስረድተዋል።
ሕፃን ሐሌ ሚደቅሳ ወላጅ እናትዋ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ከምርጫ 97 ጋር በተያያዘ በቅንጅት አመራርነታቸው ተከስሰውና ታስረው በነበረበት ወቅት ቃሊቲ እስር ቤት እየሄደች እናትዋን ለሁለት ዓመታት ትጠይቅ እንደነበር ይታወቃል።
ወ/ት ብርቱካን ከታሰሩበት ካለፈው ቅዳሜ ዕለት እናታቸው ይዘውላቸው የመጡትን የምግብ ሣህን ጨምሮ ከሰኞ ጀምሮ የገቡላቸውን የምግብ ሣህኖች ምንም ምግብ ሳይበሉ እንዳለ የመለሷቸው መሆኑን ለማወቅ ችለናል። ቅዳሜ ዕለት ከገባላቸው ውስጥ የብርቱካን ጭማቂውን ብቻ ያስቀሩ ሲሆን፣ ይህንንም ያደረጉ በረሃብ አድማ ወቅት ትንሽ ፈሳሽ መውሰድ ስለሚቻል እንደሆነ ታውቋል። ወ/ት ብርቱካን ከታሰሩበት ዕለት አንስቶ እስከዛሬ ድረስ በረሃብ አድማ ላይ ይገኛሉ።
ከዚህም ሌላ ወ/ት ብርቱካን ለመኝታ ተብሎ የታሰሩ ዕለት ከእናታቸው የተላከላቸውን ፍራሽ ተመላሽ ማድረጋቸውንና የሚተኙትም መሬት ላይ እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።
የኢትዮጵያ ዛሬ ምንጮች፤ ምንም እንኳን ወ/ት ብርቱካን በረሃብ አድማ ላይ የሚገኙ ቢሆኑም ከነአካልና መንፈስ ጥንካሬያቸው እንደሆኑና ጤንነታቸውም በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።