ክርስቲያን

አብዛኛውን ጊዜ አምባገነን መሪዎች እንዴት እንደሚያስቡ ማወቅ ካባድ ነገር ነው። ባህሪያቸውን ለመተንበይ በጣም አስቸጋሪ ነው። ግን ይህንን ከባድ ነገር ለመሞከር ተነሳሁ። ብርቱካን መቼ እንደምትፈታ ለማወቅ ከመጓጓቴ ብዛት የማይደፈረውን ለመድፈር አሰብኩ። እናም ጠቅላይ ሚኒስትሩ የብርቱካንን መፈታት መቼ እንደሚፈቅዱ ለማወቅ ሞከርኩ። ከምርጫ በፊት ወይስ ከምርጫው በኋላ?

 

ይህንን ለማወቅ ተያያዥ የሆኑ ነገሮችን ማንሳት አለብን። በተለይም ከመጪው ምርጫ ጋር የተያያዙ ጉዳዮችን።

 

1. ወያኔ (ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ) ሥልጣን ለመልቀቅ ፈቃደኛ ነውን? ይህንን የሚያሳይ አንድም ምልክት የለም። ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የማሳደድ ተግባራቸውን እንደገፉበት ነው፣ ሀገሪቱን ኢኮኖሚ የመቆጣጠር ህልማቸውን አሁንም ቢሆን ገደብ አላስቀመጡለትም፤ እንዲያውም ከዚህ በፊት ያልተቆጣጠሩትን የንግድ ዘርፍ (የቡናን ንግድ) በቁጥጥር ስር ለማዋል በእንቅስቃሴ ላይ ናቸው፣ የአምባገነን መሪዎች መገለጫ የሆኑ ልዩ ምልክቶችንም ማሳየት ቀጥለዋል (ለምሳሌ ያክል በቅርብ ጊዜ ውስጥ ከወጣቶች ጋር ባደረጉት ስብሰባ ላይ “ቆራጡ መሪያችን” መንግሥቱ ኃይለማርያም ያስደርጉት እንደነበረው ወጣቶቹ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ ያለበትን ካኔተራ እንዲለብሱ መደረጉ)።

 

2. ወያኔ ምርጫውን ዲሞክራሲያዊ ለማስመሰል መጣሩ የማይቀር ይመስለኛል። ቢያንስ እንደ አሜሪካና እንግሊዝ የመሳሰሉትን ዕርዳታ ሰጪ መንግሥታትን ለማስደሰት። ግን ያለፈው አይነት ስህተት ላለመፈፀም ይጥራል። እናም የህዝብን ቀልብ ሊስቡ የሚችሉ በተቃዋሚው ጎራ የተሰለፉ ግለሰቦችን በበጎ ዓይን አይመለከታቸውም። ህዝብ ለመብቱ እንዲነሳሳ ስለሚያደርጉ።

 

አሁን በተቃዋሚው ጎራ ካሉት የፖለቲካ ሰዎች መካከል የህዝብን ቀልብ መያዝ የሚችል ማን አለ? አብዛኛዋቹ በእኔ እይታ የህዝብን አመኔታ አጥተዋል። የተወሰኑት ተጠልተዋል። የተወሰኑት በጥርጣሬ ዓይን የሚታዩ ናቸው። ጎላ ብለው ከሚታዩት መካከል የተወሰኑትን በጥልቀት ለመመልከት እንሞክር።

 

ልደቱ አያሌው

ራሱን በራሱ የገደለ ፖለቲከኛ። በአጭር ጊዜ ውስጥ የህዝብ ፍቅርን ማትረፍ የቻለ ግን አመኔታውን ይዞ መቆየት ያልቻለ ግለሰብ ነው። እንዲያውም በከሃዲነት የሚታማ። የከሃዲነቱን ወሬ እውነት ነው ብየ ባላምንም፤ ተወዳጅ የፖላቲካ ሰው የመሆኑን ተስፋውን በገዛ ራሱ ያጨለመ ስለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። በምርጫ 97 ከቀሪዎቹ የቅንጅት አመራሮች ጋር የነበረውን አለመስማማት ሊፈታ የሞከረበት መንገድ የፖለቲካ ብስለቱን እንድጠራጠረው አድርጎኛል። ይባስ ብሎ ወያኔ ተቃዋሚዎቹን ከሚሰድባቸው በላይ እሱ ለመስደብ በመሞከሩ ራሱን ጎድቶታል። በርግጥ ነው አብዛኛዎቹ የተቃዋሚ መሪዎች ሌሎች የተቃዋሚ መሪዎችን የመሳደብ ሱስ ያለባቸው ይመስላሉ። በዚህ ጉዳይ ዶ/ር ብርሃኑ (መኢአድን “ጀሌዎች” ማለቱ)፣ ኢንጂንየር ኃይሉ ሻውል (ዶ/ር ብርሃኑን “ለምኖን ነው ቅንጅት ውስጥ የገባው” ማለታቸው) ሁሉ ተጠያቂ ናቸው። አካሄድን ከመተቸት ይልቅ ስብዕናን መተቸት ይቀላቸዋል።

 

በነገራችን ላይ የአሁኑ የዶ/ር ብርሃኑ አቋም የበፊቱ የኃይሉ ሻውል አቋም ነበር (ከወያኔ ጋር መደራደር ለውጥ አያመጣም ብሎ ማመን)፤ እንዲሁም የአሁኑ የኃይሉ ሻውል አቋም የቀድሞ የብርሃኑ አቋም ነበር (ከወያኔ ጋር በመደራደር ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ ማመን)። ለውጥን ለማምጣት የአካሄድ ልዩነት መኖሩ የሚጠበቅ ነገር ነው። እናም ልዩነትን መቀበል ተገቢ ይመስለኛል። የአካሄድ ልዩነትን መተቸት ተገቢም ሊሆን ይችላል (አስፈላጊ ባይመስለኝም፣ ዓላማቸው እስከተመሳሰለ ድረስ)። ከዚያ አልፎ ግን መሰዳደቡ ሰዎቹ ምን ነካቸው፣ ትልቅ ሰዎች አይደሉምን የሚያስብል ነው።

 

ኃይሉ ሻውል

ኃይሉ ሻውል የልደቱን ያህል የህዝብ ፍቅር ነበራቸው ብዬ ባላምንም በ97ቱ ምርጫ ላይ ትልቅ ሚና መጫወታቸው የሚካድ አይደለም። ግን ምን ዋጋ አለው እሳቸውም ልክ እንደ ልደቱ የራሳቸውን ተስፋ በራሳቸው አጨልመውታል። ከምርጫው በኋላ በተለይም ከእስር ከተፈቱ በኋላ ከቀሪዎቹ የቅንጅት አመራሮች ጋር የነበራቸውን ችግር መፍታት ባለመቻላቸው የህዝብ አመኔታን አጥተዋል። በአሁኑ ሰዓትም ቢሆን ለተቃዋሚ ፖለቲከኞች ያላቸው አመለካከት ጥሩ አለመሆኑን በተለያየ ጊዜ በሰጧቸው ቃለምልልሶች በማመልከታቸው ተስፋቸውን ያጨልመዋል።

 

መረራ ጉዲና እና በየነ ጴጥሮስ

የሁለቱ ግለሰቦች የፖለቲካ ታሪክ በጣም ተመሳሳይ ነው። ሁለቱም በብሔር የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሪ መሆናቸው፣ ሁለቱም ፓርላማ ውስጥ የመክረማቸው እንዲሁም ሁለቱም የአብዛኛውን ህዝብ ቀልብ መያዝ አለመቻላቸው ያመሳስላቸዋል። ወያኔም ቢሆን በሁለቱ ሰዎች የፖለቲካ ሕይወት ከከሰረው ይልቅ ያተረፈው የሚበልጥ ይመስለኛል። እናም የህዝብንም ቀልብ ያለመሳባቸውን ያክል የወያኔን የጥፋት ቀልብ አልሳቡም። ለሚመጣውም ምርጫ ቢሆን የወያኔን የጥፋት ዘመቻ ቀልብ የሚስቡ አይመስለኝም።

 

ገብሩ አስራት፣ ነጋሶ ጊዳዳ፣ ስየ አብርሃ

ሁሉም የጋራ መገለጫቸው ከወያኔ ጋር አብረው መሥራታቸው ነው። በዚህም ምክንያት የህዝብን አመኔታ ለማግኘት ይቸገራሉ። ማግኘትም የሚችሉ አይመስለኝም። ቢያንስ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ወቅት ላጠፉት ጥፋት ከልብ የሚደርስ ይቅርታ ባለመጠየቃቸው ከህዝብ ልብ ውስጥ ለመግባት በጣም ይቸገራሉ። የገብሩ አስራት “ዓረና ትግራይ” አይደለም የመላውን የኢትዮጵያን ህዝብ ቀልብ መግዛት የትግራይንም ህዝብ ቀልብ መግዛት የቻለ/የሚችል አይመስለኝም። ግለሰቦቹም ቢሆን ጠንካራ የፖለቲካ ሰዎች አይመስሉኝም።

 

ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የዋህ ናቸው፣ ገብሩ አስራት የሥራ ሰው እንጂ ፖለቲከኛ አይደለም፣ ስየ የጦር ሰው እንጂ ፖለቲከኛ አይደለም።

 

ኢንጂንየር ግዛቸው እና ዶ/ር ኃይሉ አርኣያ

ሁለቱ ደግሞ በ97ቱ ምርጫ ወቅት እንኳን የህዝብ ልብ ውስጥ ብዙም የገቡ አልነበሩም። ሁለቱም ቢሆኑ በልደቱ፣ በኃይሉ ሻውል እና በብርሃኑ ጥላ ተሸፍነው ነበር። ከዚያም በኋላ ቢሆን አንድነትን እየመሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት፣ እንኳን የህዝብ ልብ ውስጥ ሊገቡ የህዝብን ቀልብ መሳብ አልቻሉም።

 

ዶ/ር ብርሃኑ

ዶ/ር ብርሃኑ በሚቀጥለው ምርጫ ላይ ምንም አይነት ተፅዕኖ ማሳደር የሚችሉ አይመስለኝም። ከምርጫው ሂደት ወጥተው ሌላኛውን አማራጭ የተከተሉ በመሆኑ። የመረጡት መንገድ ያዋጣል አያዋጣም የሚለውን በሂደት የምናየው ይሆናል። ይህኛውን አማራጭ መከተላቸው ደግሞ የወያኔ ህልም የነበረ ይመስለኛል። ዶ/ር ብርሃኑ ከሀገር በመውጣታቸው ወያኔ እረፍት አግኝቷል። ምክንያቱም የህዝብን ቀልብ ሊይዙ የሚችሉ ግለሰብ ስለነበሩ። የህዝብ አመኔታን እስካሁን ድረስ ከያዙ በተቃዋሚው ጎራ ካሉ ግለሰቦች አንዱ ናቸው። በሠላማዊ ትግሉ በቀጥሉና ሀገር ቤት ቢሆኑ ኑሮ የሚቀጥለውን የወያኔን የምርጫ ድራማ ሊያበላሹ የሚችሉ ግለሰብ ነበሩ።

 

ብርቱካን ሚደቅሳ

ህዝብ እንደወደዳት፣ ለህዝብ እንደታመነች፣ ለወያኔ ድራማ የቀን ቅዠት እንደሆነች የቆየች እስከ አሁንም ድረስ በህዝብ ልብ ውስጥ ያለች የፖለቲካ ሰው ነች። የመታሰሯ ነገር ወያኔ ሊተውነው ከተዘጋጀው የምርጫ ድራማ ጋር የተገናኘ ይመስለኛል። በተቃዋሚ ጎራ ከተሰለፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ወያኔን የሚያሰጋው አንድነት ፓርቲ ነው (ከስሙ ጀምሮ ወያኔ ሊወደው አይችልም - ወያኔ እና አንድነት የሚለው ቃል ተቃራኒዎች ናቸው። አንድነት የሚለው ቃል ወያኔን ያስደነግጠዋል። የሥልጣን ዘመኑን ሊያሳጥርበት ስለሚችል)።

 

አንድነት ጠንካራ ፓርቲ መሆን እንዲችል የህዝብን ቀልብ መግዛት የሚችል ጠንካራ የሆነ መሪ ያስፈልገዋል። እናም አንድነት በስሩ ካቀፋቸው ግለሰቦች መካከል ህዝብን በስሯ ማሰለፍ የምትችል ብቸኛዋ ግለሰብ ብርቱካን ነበረች። ከ97ቱ ምርጫ በኋላ ስምና ዝናዋ እየገነነ መጣ፣ የህዝብ ፍቅር እየበዛላት ሄደች። የዚያኑ ያህል ደግሞ በወያኔዎች ተጠላች። የብርቱካን መኖር ብቻ የአሁኑን የምርጫ ድራማቸውን ሊያበላሽ እንደሚችል ገባቸው። ብርቱካንን በማሰር አንድነትንና ህዝብን ማሰር እንደሚችሉ አወቁ፤ እናም ሰበብ ተፈልጎላት እስር ቤት ወረደች። አንድነትም ህዝብም አብሮ ታሰረ። ቀሪዎቹ የአንድነት መሪዎች ወያኔ እንደገመተው የህዝብን ቀልብ መያዝ አልቻሉም።

 

እናም የብርቱካን መታሰር ከመጪው የምርጫ ድራማ ጋር የመያያዙን ያክል የመፈታቷም ነገር ከምርጫው ጋር የተያያዘ ነው። እናም ብርቱካን መቼ ትፈታለች? መጪው የምርጫ ድራማ እንደተጠናቀቀ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ