ሮቤል አቀባበል ተደረገለት
Ethiopia Zare (ሐሙስ የካቲት 4 ቀን 2002 ዓ.ም. February 11, 2010)፦ በቫንኩቨርሩ የክረምት (ዊንተር) ኦሎምፒክ በበረዶ ላይ መንሸራተት (ስኪ) ውድድር ለመሳተፍ ዝግጅቱን ያጠናቀቀው ወጣት ሮቤል ተክለማርያም፤ ትላንት ከምሽቱ 8፡30 አካባቢ በቫንኩቨር አውሮፕላን ማረፊያ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት።
ሮቤል በክረምቱ የኦሎምፒክ ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ የሚሳተፍ ሲሆን፤ ዋና ዓላማው ኢትዮጵያዊያን ወጣቶችን በማነሳሳት ሀገሩ በክረምት ኦሎምፒክ ውድድሮች ላይ እንዲሳተፉ በር መክፈት መሆኑን "ቫንኩቨር ሰን" ለተባለ ጋዜጣ ገልጿል።

በ2010 እ.ኤ.አ. ኦሎምፒክ ለጥበቃና ደህንነት ብቻ የአንድ ቢሊየን ዶላር ወጭ የተመደበ ሲሆን፣ የከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ለወር ያህል የሚቆየውን የክረምት ኦሎምፒክና የዓለም አቀፍ አካል ጉዳተኞች ስፖርት ውድድር ምክንያት በማድረግ ተዘግተው እንደሚቆዩ ታውቋል።

የ2010 እ.ኤ.አ. ቫንኩቨር ዊንተር ኦሎምፒክ ነገ የካቲት 5 ቀን 2002 ዓ.ም. (ፌብሩዋሪ 12 ቀን 2010 እ.ኤ.አ.) በደማቅ ሁኔታ የሚከፈት ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ባንዲራ ለሁለተኛ በወጣት ሮቤል ምክንያት ይውለበለባል።

ለሮቤል መልካም ዕድልን እንመኛለን።



