ቫንኩቨር ሮቤልን ለመቀበል በዝግጅት ላይ ነች
በሲያትል ኮንሰርቱን የሚያቀርበው ቴዲ አፍሮ ሮቤልን ይቀበላል ተብሎ ይጠበቃል
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ጥር 29 ቀን 2002 ዓ.ም. February 6, 2010)፦ ለመጀመሪያ ጊዜ ኢትዮጵያን በመወከል ለፈረንጆቹ የክረምት የበረዶ ላይ የስፖርት ውድድር ተሳታፊ የሆነው ሮቤል ተክለማሪያምን ለመቀበል ዝግጅቱ መጠናቀቁን በቨንኮቨር የሚገኘው ግብር ሀይል ለኢትዮጵያ ዛሬ ገለጸ።
ሮቤልን ለመቀበል በሲያትል የሙዚቃ ኮንሰርቱን ዛሬ ቅዳሜ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ የሚገኘው እውቁ ድምጻዊ ቴዎድሮስ ካሳሁን የኦሎምፒክ ውድድር በሚካሄድባት ቫንኩቨር ከተማ ተገኝቶ ሮቤልን እንዲቀበለውና እንዲያበረታታው የቫንኩቨር ነዋሪዎች ቴዲን ጠይቀው መልስ እየተጠባበቁ መሆኑን ለማወቅ ችለናል።
ቴዲ አፍሮ ወደካናዳ የመግቢያ ፈቃድ (ቪዛ) ለማግኘት ሰኞ ወደ ካውንስለሩ ቢሮ የሚቀርብ መሆኑን የገለጹልን ምንጮች ከቪዛ ፈቃዱ በኋላ የዝነኛው አቀንቃኝ ቴዎድሮስ ካሳሁን ውሳኔ እንደሚጠበቅ ለማረጋገጥ ችለናል።
የኢትዮጵያ ስኪ ፌደሬሽን ሮቤልን በሚመለከት ያወጣውን መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።
ሮቤል ተክለማሪያም:- በቫንኩቨር የበጋ ኦሊምፒክ፡ ብቸኛው የኢትዮጵያ ተወዳዳሪ
የዛሬ አራት ዓመት፡ ኢትዮጵያዊው የአገር አቋራጭ የበረዶ ላይ ስፖርት ተወዳዳሪ፡ ሮቤል ተክለማሪያም፡ ኢትዮጵያን ለመጀመሪያ ግዜ፡ በቱሪን የበጋ ኦሊምፒክ ይዞ በመቅረብ፡ ታሪክ ሰርቶ ነበር። ያንኑ ፈለግ በመከተል፡ በዘንድሮው የቫንኩቨር የበጋ ኦሊምፒክም፡ ኢትዮጵያን ባለድል የማድረግ ሕልሙን ይዞ እየተጓዘ ነው።
ሪችመንድ፡ ቨርጂኒያ፡ ጥር፡ 2010 ዓ.ም። ይሄ የያዝነው ዓመት፡ ለኢትዮጵያ ሁለት አበይት የኦሊምፒክ ታሪካዊ ክስተቶች የሚታሰቡበት ነው። በሮም ኦሊምፒክ በባዶ እግሩ በመሮጥ ወርቅ ያስገኘውና የዓለምን ክብረወሰን የሰበረው አበበ ቢቂላ ሀምሳኛ ዓመት የድል በዓል የሚዘከርበትና፡ ሮቤል ተክለማሪያም እንደገና ኢትዮጵያን ወክሎ በቫንኩቨር፡ ካናዳ በያዝነው የፈረንጆች ወር የሚደረገውን የበጋ ኦሊምፒክ የሚሳተፍበት ዓመት ነው።
የአበበ ቢቂላ ታሪካዊ ድል፡ የዛሬዎቹን የረጅም ርቀት ሩጫ ተወዳዳሪዎችን የቀሰቀሰ ብቻ ሳይሆን፡ ለኢትዮጵያ እንግዳ የሆነውን፡ የበረዶ ላይ ስፖርት ውድድር ፈር ቀዳጅና ለሌሎችም ወጣቶች አርአያ የሆነውን ሮቤል ተክለማሪያምን ያነሳሳና እድሜ ልክ የሚታወስ ድል ነው። ሮቤል ተክለማሪያም ዘወትርም በአፅንኦት እንደሚገልጸው፡ በበጋ ኦሊምፒክ የመሳተፍ ሕልሙ የሚጫረው ለአገር አቋራጭ የበረዶ ላይ ውድድር ባለው ልዩ ስሜት ብቻ ሳይሆን፡ የዚህን ስፖርት ፍቅር በሌሎች ወጣት ኢትዮጵያዊያን ላይ ለመለኮስ ካለው ጽኑእ እምነት የተነሳ ነው።
ሮበል፡ “ይሄ ለኢትዮጵያ መንገድ ከፋች ነው፡ በበረዶ ላይ ሸርተቴ ወደ ኦሊምፒክ መግባት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ካለ፡ አሁን መንገዱ ተከፍቷል። ኢትዮጵያዊያን ጽናትን በሚሹ ስፖርቶች ጎበዝ ናቸው። ኢትዮጵያዊያን ህጻናት በ8 እና 9 አመታቸው የበረዶ ላይ አገር አቋራጭ ውድድር መለማመድ ቢጀምሩ፡ ሜዳሎችን የማያመጡበት ምክንያት አይታየኝም” ሲል ተናግሯልረ።
ወጣት ኢትዮጵያዊያንን ደረጃውን ወደጠበቀ አለም አቀፍ የበረዶ ላይ ስፖርቶች ለመሳብና ለመኮትኮት የተሰናዳው የኢትዮጵያ ስኪ ማህበር ከተቋቋመ ግዜ ጀምሮ፡ የሮቤልና ማህበሩ ምኞት፡ በኦሊምፒክ ተሳትፎው አማካኝነት ስፖርቱንና ይህን አዲስ ማህበር በኢትዮጵያዊያን ዘንድ ማስተዋወቅ ነው። የኢትዮጵያ ስኪ ማህበር ሊጎለብትና አላማውን ከግብ ሊያደርስ የሚችለው፡ በግለሰቦች፡ ንግድ ድርጅቶችና ሌሎች ማህበራት እርዳታ ነው። የኢትዮጵያ ስኪ ማህበር (ESA) የኢትዮጵያዊያንን የድል ባህል ወደ በጋ ኦሊምፒክም በዘላቂነት ለማስፋት ይጥራል። ስፖንሰር የማድረግ እድሎችና የበጎ አድራጎት ችሮታ ለማድረግ፡ ድረ-ገጹን www.ensf.org ይጎብኙ።
የኢትዮጵያ ሰኪንግ ማህበር (ESA) ብቸኛውን ኢትዮጵያዊ ተወዳዳሪ፡ ሮቤል ተክለማሪያምን በ2006 ወደ ቶሪኖ፡ ጣሊያን ለመላክ በሚል ዓላማ እንደ በጎ አድራጎት ድርጅት በ 2005 ተቋቋመ። ሮቤል፡ በማናቸውም አይነት የበጋ ኦሊምፒክ ለመወዳደር የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነበር። ነውም። ያንን ዓላማ ከግብ በማድረስ፡ በአሁኑ ሰዓት ሮቤልን በዚህ ወር በሚጀመረው የቫንኩቨር የበጋ ኦሊምፒክ ለማሳተፍ ገንዘብ እያሰባሰበና ድርጅቱንም እያስተዋወቀ ነው። ሮቤል በአውሮፓ በልምምድ ላይ የቆየ ሲሆን፡ ሰሞኑን ወደ ቫንኩቨር ይገባል ተብሎ እየተጠበቀ ነው።
ለተጨማሪ መረጃ፡ ዮሴፍ ተክለማሪያምን በ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ወይም በ 917 655 2183 ደውለው ይጠይቁ።



