የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ዜና ማርቆስ ጊዜያዊ የቀብር ሥነሥርዓት ተፈጸመ
ዋና ቀብራቸው ቴክሳስ በሚቋቋመው ታላቅ ገዳም ይደረጋል
Ethiopia Zare (ሰኞ የካቲት 15 ቀን 2002 ዓ.ም. February 22, 2010)፦ የሕይወት ዘመናቸውን በሙሉ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሰጥተው፤ በመማር በማስተማርና ከትንሽ እስከ ታላላቅ የአገልግሎት ክፍሎች በማገልገል ያሳለፉት አቡነ ዜና ማርቆስ በስደት ባቋቋሙት የሲያትል ቅ/ገብርኤል ቤተክርስቲያን የፍታት ሥነሥርዓታቸው ተካሂዶ በጊዜያዊ ማረፊያ ቦታ የቀብራቸው ሥነሥርዓት ተፈጸመ።
አቡነ ዜና ማርቆስ ከ18 ዓመታት በፊት በአስገዳጅ ሁኔታ ሀገራቸውንና የሚያገለግሉትን ህዝባቸውን ትተው ለመሰደድ ከበቁበት ጊዜ አንስቶ በኬንያና በአሜሪካ በስደት የሚገኙ የኃይማኖቱ ተከታዮችን በማሰባሰብ በማስተማርና አጥቢያ ቤተክርስቲያናቶችን በመሥራት በስደት ሲያገለግሉ ቆይተው የካቲት 6/2002 ዓ.ም. (ፌብሩዋሪ 13/2010 እ.ኤ.አ.) ሕይወታቸው ማለፉ ይታወሳል።
በቀብር ሥነሥርዓታቸው ከተለያዩ አህጉራት የተሰባሰቡ ሊቃውንት፣ ጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናትን ጨምሮ በስደት የሚገኙት ብጹዕ አቡነ መርቆሪዮስ በቀብር ሥነሥርዓቱ ላይ ተገኝተው አባታዊ ምክርና ትምህርት እንደሰጡ ለመረዳት ችለናል።
ይሄው ከሰኞ ጀምሮ ሲካሄድ የነበረው የሽኝት ሥነሥርዓት ላይ በሲያትል አካባቢ የሚገኙ ባሥልጣናት፣ የተለያዩ የእምነት አባቶች፣ ወጣቶችና የሰንበት ተማሪዎች እስከ ኀሙስ ዕለት ምስክርነቶች ሲያሰሙ ቆይተዋል።
የብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ዋና የቀብር ሥነሥርዓት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በአሜሪካን ሀገር ቴክሳስ ግዛት በምታስገነባው ታላቅ ገዳም እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ ገዳሙ ቦታው ተገዝቶ ሕጋዊ ሥርዓቶች እየተፈጸሙ መሆናቸውን ለምዕመናኑ በተበሰረ ሰዓት ለሁለት ደቂቃ ያላቆመ ጭብጨባና እልልታ ግቢውን ሞልቶት እንደነበር ታውቋል። ትላንት ቅዳሜ በተካሄደው የመጨረሻ ስንብት አዳራሹና ግቢው ሙሉ በሙሉ ሞልቶ መንገዶች ለመዘጋት ግድ ሆኖ የነበረ ሲሆን፣ አብዛኛው ምዕመናን የብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ በጎነት በተነሳ ቁጥር ኀዘናቸውን እንባ በመርጨት ይገልጹ ነበር። ጊዜያዊ የቀብር ሥነሥርዓቱ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ የካቲት 13 ቀን 2002 ዓ.ም. ሲታክ በሚባለው አካባቢ በሚገኘው የቀብር ቦታ ተፈጽሟል።
ኢትዮጵያ የሚገኘው ሲኖዶስ የገቡትን ቃል ኪዳን ዘንግተው፣ ቤተክርስቲያናቸውንና ሀገራቸውን ትተው የማይመለከታቸውን ተግባር መፈጸማቸውን ገልጾ፣ የመንፈሥ ልጆቻቸው ጠየቁኝ በማለት ውግዘቱን አንስቻለሁ፣ ወደ ሀገራቸው መጥተው መቀበር ይችላሉ ሲል መግለጫ ቢያወጣም፤ በውጭ የሚገኘውና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶን ቀኖና አናፈርስም በፓትሪያርክ ላይም ፓትሪያርክ አይሾምም በማለት ለሁለት አሥርተ ዓመታት ጸንቶ መቆየቱ የሚነገርለት በስደት የሚገኘው ሲኖዶስ የብጹዕ አቡነ ዜና ማርቆስ የቀብር ሥነሥርዓት ብዙ ምዕመናንን ባፈሩበትና ወጣቶችን፣ አዛውንቶችንና ህጻናትን አስተምረው ወደ ቤተክርስቲያኗ በሰበሰቡበት ቦታ እንዲሆን መወሰኑ ታውቋል።
- ተጨማሪ ፎቶግራፎች







