አባቱን አክባሪ ትውልድ በሲያትል (አቤል አድማሱ)
አቤል አድማሱ
እ.ኤ.አ. February 13, 2010 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩን የሥነ መለኮትና የቅዳሴው ሊቅ የነበሩት ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳስን የመጨረሻ ስንብት አስመልክቶ በተለያዩ የዜና ማሰራጫዎችና የድረ ገፆች ላይ አይነተኛና ለምዕመናን አስደንጋጭ ዜና ሆኖ ሰንብቷል።
የብፁዕነታቸው እረፍት ያሳዘነው መላው የኢትዮጵያ ህዝበ ክርስቲያን ሆኖ ሳለ በተለይም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን ልብ በሀዘን አቃጥሎታል። ምነው እንደዚህ ሆድ ባሰህ አትበሉኝ እንጂ ሀዘኑ አንጀቴ ገብቶ አቃጥሎኛል። ምነው? ቢባል “ኢትዮጵያ ሰው ስታጣ! ቤተ ክርስቲያን ሰው ስታጣ! ምነው አልቃጠል” ወገኖቼ! ሰው ማለት እንደኔ ቆሞ ሲሔድ ሰው መስሎ የሚታየውን ማለቴ አይደለም። በሊቃውንት አባባል ሰው ማለት “ሰው በጠፋበት ዘመን ሰው ሆኖ የሚገኝ ሰው” ማለት ነው።
ታዲያ እኝህ ታላቅ አባት ሰው በጠፋበት ዘመን ሰው ሆነው የተገኙ፣ ትንሽ ትልቅ የማይሉ፣ ሰውን በሰውነቱ እንጂ በያዘው ማዕረግ (ዶክተር፣ ፕሮፌሠር፣ ደጃዝማች፣ ግራዝማች፣ ጀኔራል፣ ኮሎኔል፣ ... ወዘተ) ወይም ባለው ሀብትና ገንዘብ መጠን የግለሰቡን ከሰው የበለጠ ክብርን ከምንም የማይቆጥሩ አባት ነበሩ።
ብፁዕ አባታችን በአንፃሩ በክርስትና ሕይወቱ ቀጥ ብሎ ለመራመድ አስቦ እንዳይንገዳገድ ማጥበቂያ ክር እንዲሰጡት ለተጠጋቸው ምክራቸውና ጸሎታቸውን ለጠየቀ ማንም ግለሰብ (ትግሬ ነው፣ አማራ፣ ኦሮሞ ነው፣ ከምባታ፣ ጉራጌ ነው፣ ወላይታ፣ …) ሳይሉ የነገረ መለኮቱን ምስጢር አመሳጥረው በመተንተን ድነው የሚያድኑ፣ ተምረው የሚያስተምሩ፣ ወደር የማይገኝላቸው የክርስትና ኣባት ነበሩ። “ያላወቁ አለቁ” ይላል ያገሬ ሰው። ብፁዕነታቸው በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ቅድስናቸውንና የተሰጣቸውን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ የተረዳላቸው ግን በጣም ጥቂቱ ህዝብ ነበር። ያ ጥቂት ህዝብም በጸሎታቸውና በቡራኬአቸው ተጠቅሞባቸዋል።
ይህችን አጭር ጽሑፍ ለማቅረብ ያነሳሳኝ ነገር ቢኖር የብፁዕነታቸው የሕይወት ታሪክና መንፈሳዊ ተጋድሎ ገድል ለመጻፍ አይደለም። የብፁዕ አባታችን የሕይወት ታሪክና መንፈሳዊ ተጋድሎ ለዛ ባለው ብዕር ሊያቀርቡልን የሚችሉ ብቃቱ ያላቸው ሌሎች ታላላቆች ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ስላሉ ይህን ሥራ ለእነርሱ እተወዋለሁ።
እኔ ግን ዛሬ ለመጻፍ የፈለኩት ስለ ሲያትል ቅዱስ ገብርኤል ካህናትና ምዕመናንን መልካም ሥራን ነው።
ወገኖቼ!
እነዚህ ከትልቁ ባሕር (ኢትዮጵያ) በጥቂቱ የተቀዱ ወገኖች፣ የተፈጠሩበትን ሀገርና ምድር የሚያስከብሩ፣ ልባቸውንና ወሰናቸውን የሚያውቁ ወገኖቻችን የብፁዕነታቸውን መንፈሳዊ ጣዕም ተረድተው የሚሰጥዋቸውን አባታዊ ትዕዛዝ አክብረው ቤተ ክርስቲያኗን ያለምንም የባንክ እዳ አንፀው፣ በሰው ሀገር የወለዷቸውን ልጆቻቸውን የትውልድ ቋንቋቸውን አስተምረው ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን በስደት ላለው ለመላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ መኩሪያ ሆነው አግኝቻቸዋለሁ።
የነዚህ ወገኖች ታሪካዊና መንፈሳዊ ሥራ ለብዙ ጊዜ በብፁዕ አባታችን በኩል በጆሮዬ ስሰማ ኖሬአለሁ። በአባታችን በሞት መለየት ምክንያት በሥፍራው ተገኝቼ በዓይኔ ያየሁትን ለመመሥከር እገደዳለሁ።
የብፁዕነታቸው ዜና እረፍት ከተሰማበት ቀን ጀምሮ ከየክፍለ ዓለማቱ ወደ ሲያትል መጉረፍ የጀመረው ምዕመናን ብዛት ቁጥር በቀላሉ የሚቆጠር አልነበረም። ይህንን ሁሉ ከየአቅጣጫው የመጣውን ካህናትና ህዝበ ክርስቲያን ማስተናገድ ደግሞ ራሱን የቻለ ምን ያህል ከባድ ኃላፊነት እንደሆነ መገመት አያዳግትም። ለካህናቱና ለምዕመናኑ ቁርስ ምሳና እራት ማዘጋጀት፣ ከግብር በኋላ ማፅዳት፣ እንደገና ለሚቀጥለው ቀን የሚሆን ምግብ ሲያዘጋጁ ማደር፣ ... ወዘተ፤ በሌላ የሥራ ክፍል ደግሞ በብፁዕነታቸው የአሸኛኘት ሥነ ሥርዓት በተቀላጠፈ መልክ ለማዘጋጀት ከቀብር አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶችና ከልዩ ልዩ የመንግሥትና የግል ድርጅቶች አካሎች ጋር ግንኙነት በማድረግ ፕሮግራም በማውጣት ልዩ ልዩ በራሪ ወረቀቶችን ፎቶግራፎችን በማዘጋጀት፤ በሌላው የሥራ ድርሻ ደግሞ ከተለያዩ ክፍለ ዓለማት የመጡትን እንግዶች ማረፊያ ቦታ በማዘጋጀትና የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ማቀናጀት፣ … ኧረ ስንቱ ድንኳን መትከል፣ ወንበር መደርደር፣ ይህ ነው የማይባል ከፍተኛ የሥራ ድርሻ ሲወጡ ከርመዋል።
ወገኖቼ!
እኔን ያስደነቀኝና እነዚህን ወገኖቻችንን በታሪክ ፊት እንዳይረሱ ያስፈልጋል ለማለት ያስደፈረኝ፤ ይህን ሁሉ ሥራ ሲሠሩ የእርስ በርስ መጨቃጨቅ ወይም በኃይለ ቃል መነጋገር አላየሁባቸውም። ሁሉም በበጎ ፈቃደኝነት የተመደቡበትን የሥራ ድርሻ በፀጥታና በትሕትና ሲሠሩ ነው የተመለከትኩት።
ማርን የሚያህል ለሰው ልጅ የሚጠቅመውን ጣፋጭ ምግብ የምታመርተው ንብና ሠራዊቷ እያንዳንዳቸው የተመደቡበትን የሥራ ድርሻ በብቃት ለመወጣት በሕብረት ስለሚጓዙና ስለሚሠሩ ጣፋጭ ምርት ለሰው ልጆች ሊያቀርቡ ችለዋል።
እነዚህም የሲያትል ቅዱስ ገብርኤል ካህናትና ምዕመናን ከልብ የሚወዷቸውን አባታቸውን ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስን የመሰለ ታላቅ መንፈሳዊ የዘመኑ ሐዋርያ በሚያስደንቅ ግርማ በመሸኘት እንኳን እኛ ኢትዮጵያውያን የሀገሩን ተወላጆች አሜሪካውያኑንም ያስደነቀ ሥራ ሲሠሩ ታይተዋል።
“አባቱን አክባሪ ትውልድ” ማለት ይህ ነው። የተወደዳችሁ ወገኖቻችን እግዚአብሔር በሁሉም ነገር ይባርካችሁ ዘንድ የሁላችንም ምኞት ነው።
ወገኖቼ!
ታዲያ እነዚህ ወገኖቻችን ባደረጉት መልካም ሥራ እኛ ፍጡሮች እንደዚህ የተደሰትን፣ የዓለሙ ጌታ ፈጣሪማ እንዴት ይደሰት? ከነዚህ የተባረኩ ሰዎች የምንማረው ብዙ ትምህርት አለ። መደማመጥ፣ መከባበር፣ ወገናዊ ፍቅር ማሳደር፣ ለኃይማኖትና ለታሪክ መልካም ሥራ ሠርቶ መገኘት፣ ... እና የመሳሰሉት ናቸው።
እኛ ኢትዮጵያውያን ወንድማችን ወይም እህታችን ከአጠገባችን በሞት ድንገት ሲለዩን ለጊዜው እንደነግጣለን። ወዲያው ከዛሬ ጀምሮ ጥሩ ሰው ሆነን የእግዚአብሔርን መንገድ ለመከተል ሕጉን ለማክበርና ለመኖር ቃል እንገባለን። ቃል መግባት ብቻ አይደለም የአቋም መግለጫ እናወጣለን። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ውለን አድረን ያወጣነውን የአቋም መግለጫ ቀለሙ ሳይደርቅ ወደ ቀድሞው ክፉ ሥራችን እንመለሳለን።
ውድ ወገኖቼ!
ይህ አስከፊ ባሕሪያችን ግን ከእኛ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ ይኖርበታል።
ብፁዕ አባታችን በሕይወታቸው በነበሩበት ጊዜ በየቦታው እየዞሩ ያስተማሩን ነገር ቢኖር ሰው ሆነን ለቁም ነገር እንድንበቃ ነው። ያለበለዚያ አንዱንም ጠቃሚ ነገር ሳንይዝ አጓጉል ወድቀን እንቀራለን።
የተከበራችሁ ወገኖቼ!
ብፁዕ አቡነ ዜና ማርቆስ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን ዕድገትና መስፋፋት በሀገርም ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር ያደረጉት አስተዋፅዖ በሚዛን የሚለካ አይደለም።
እኚህ ታላቅ መንፈሳዊ አባት ተወልደው ባደጉበት፣ ያለምንም ረዳት ወጥተው ወርደው፣ ተምረው ባስተማሩበት፣ ለአንዲት ኦርቶዶክሳዊ ተዋኅዶ ኃይማኖታቸው መስፋፋት የቤተ ክርስቲያን ዕድገት ሌት ተቀን በደከሙበት ሀገራቸው ላይ በሠላም ለመኖር በገጠማቸው ሰው ሰራሽ ችግርና በደረሰባቸው ከአቅም በላይ የሆነ ውጣ ውረድ ምክንያት ከሀገራቸው ተሰደው በመውጣት ወደ ሰሜን አሜሪካ ከመጡበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው ድረስ በዓላማቸው ፀንተው የቆሙ፤ ስደተኛውን የኢትዮጵያን ህዝብ ያፅናኑ፤ ከስቴት ስቴት አድካሚ ጉዞ በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ አብያተ ክርስቲያናት እንዲስፋፉና ራሳቸውን እንዲችሉ ጥረት ያደረጉ ታላቅ የፍቅርና የትህትና መምህር ነበሩ።
ብፁዕ አባታችን መኖሪያቸውና መንበረ ጵጵስናቸው ሲያትል ቅዱስ ገብርኤል ይሁን እንጂ፤ በጠቅላላ በአሜሪካን ግዛቶች፣ በካናዳ፣ በአውስትራሊያ፣ በአፍሪካ፣ በአውሮፓ በመዞር አባታዊ ግዴታቸውን የተወጡ የዘመናችን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ ሐዋርያ ነበሩ።
ውድ ወገኖቼ!
ለዛሬ ጹሑፌን ከማጠናቀቄ በፊት ለእግዚአብሔር በሚቀርብ በንፁህ ጸሎተ ኃይል ይተማመኑ የነበሩት ብፁዕ አባታችን በጸሎት ኃይል ያደረጉትንና እኔ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በግል የማውቀውን ታሪክ ላካፍላችሁ እወዳለሁ።
በሀገራችን በኢትዮጵያ በደርግ ዘመነ መንግሥት ብፁዕ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕራብ ኢትዮጵያ የወለጋ ክፍለ ሀገር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ሆነው አገልግለዋል። በዚህ የአገልግሎት ዘመናቸው ከአውራጃ ወደ አውራጃ፣ ከወረዳ ወደ ወረዳ እየተንከራተቱ አዳዲስ አብያተ ክርስቲያናትን በማሳነፅ፣ የፈረሱትን በማስጠገን፣ የሌሎች እምነቶች ተከታይ የነበሩትን ወንጌልን በመስበክ እንዲጠመቁና የመንፈስ ቅዱስ ሀብተ ፀጋ እንዲያገኙ በማድረግ፣ ምዕመናን እንዲበዙ፣ የስብከተ ወንጌሉን ክፍል በማዋቀር ያደረጉት መንፈሳዊ ተጋድሎ በቀላሉ የሚገመት አልነበረም።
ብፁዕነታቸው መንፈሳዊ ተጋድሏቸው የክርስቲያን ጠላት ከሆነው ዲያብሎስ ጋር ብቻ አልነበረም፤ የኦርቶዶክስ ኃይማኖት እንዳይስፋፋ ልዩ ልዩ ሰው ሰራሽ ተንኮል ከሚፈጥሩ ግለሰቦችና የመንግሥት ባለሥልጣን ከነበሩ የፖለቲካ ካድሬዎች ጋር ጭምር ነበር።
ታዲያ በአንድ ወቅት የተለመደውን የሀገረስብከት ሥራቸውን ለማከናወን ወደ ምዕራብ ተጉዘው በጊምቢ አውራጃ እናንጎ በተባለ ወረዳ ውስጥ የፈረሰ ቤተ ክርስቲያን በሚያሳድሱበት ጊዜ ይህችን ልዩ አጋጣሚ ሲጠብቅ የኖረና በብፁዕነታቸው ሥራ የማይደሰት አንድ የፖለቲካ ካድሬ ያልተጠበቀና ድንገተኛ ማዕቀብ ያደርግባቸዋል። ለክፉ ሥራ እንዲያመቸው ሹፌራቸውን በቀጥታ ትዕዛዝ ጠርቶ ወደ ሌላ አውራጃ ለፖለቲካ ሥራ የሚሔዱ ካድሬዎችን ይዞ እንዲሔድ ካደረገ በኋላ፤ ብፁዕነታቸውን ካሉበት ከተማ እንዳይወጡ በማስደረግ ያለአስፈላጊ የሆነ ዘለፋና ሞራላቸውን የሚነካ ድርጊት ፈፅሞባቸዋል። ይህ ካድሬ ለዚህ አድራጎቱ የሰጠው ምክንያት አባታችንን ለኢትዮጵያ አብዮት ፀር ከሆኑ የድሮ የመሬት ከበርቴዎችና ባላባቶች ጋር የጠበቀ ግንኙነት አላቸው የሚል ነበር።
ይህን ታሪክ ለእኔ ያስተላለፉት ወላጅ አባቴ በዚያን ጊዜ በቦታው ተገኝተው የዓይን ምሥክር የነበሩ ሲሆን፤ ይህ በጭካኔውና በሰው ልጅ ገዳይነቱ የታወቀው ካድሬ የአባታችንን ሕይወት ለማጥፋት ወደኋላ የሚል እንዳልነበረ ሁሉም የተረዳውና ተስፋ ቆርጦ የተቀመጠበት ወቅት ነበር።
ብፁዕ አባታችን ይህ ሁኔታ እንደተፈጠረ በቤተ ክርስቲያን አጠገብ የነበረ መቃብር ቤት በመግባት ዘግተው ምግብ ከመብላት ራሳቸውን ገትተው ጸሎት ጀመሩ። አንዳንድ ግለሰቦች በድብቅ ሁኔታውን ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ጽሕፈት ቤት አዲስ አበባ ጉዳዩን እናመልክትልዎ ሲሏቸው ፈቃደኛ ካለመሆናቸውም በላይ “እኔ የማመልከው አምላክ ይህንን ካድሬም ሆነ ዓለሙን የፈጠረ ጌታ ነው፣ ታዲያ የእኔ ጸሎት ይህንን አንድ ደካማ ፍጡር ከዚህ መጥፎ ሥራው መለወጥ ካልቻለ የእኔ ድካም ሁሉ ከንቱ ነው ማለት ነው” በማለት በጸሎታቸውና በሱባዔአቸው ፀንተው ምህላቸውን ቀጠሉ። ከሁለት ሰባት በኋላ ልክ በአስራ አምስተኛው ቀን ይህ ሀገሩን ያንቀጠቀጠው የፖለቲካ ካድሬ እየበረረ አባታችን ወደ አሉበት መቃብር ቤት በመምጣት በሩን እንዲከፍቱ ይጠይቃቸዋል። በቦታው የነበሩ የዓይን ምሥክሮች፤ “ይህ ሰው አባታችንን ወዲያው የሚገላቸው መስሎን ነበር” ነው ያሉት። ነገር ግን የተፈጠረው ሁኔታ ከሁሉም ሰው ግምት የተለየ ነበር።
ግለሰቡ በአባታችን እግር ላይ ወድቆ “አባቴ ይማሩኝ፣ ለእርስዎ የማይገባዎትን ማጉላላትና በደል በመፈፀሜ ምክንያት በመንፈሴ ሌትም ቀንም ሠላም አጥቻለሁ። ይቅር ይበሉኝ!” በማለት በእንባ ይታጠባል። አባታችንም በተለመደው የረጋ ትህትና የተሞላው ጠባያቸው ይህን ሰው “አይዞህ የክርስቲያኖች ጠላት የሆነው ዲያብሎስ ሊጠቀምብህ ያደረገው ስለሆነ አልቀየምህም። እግዚአብሔር ይቅር ይበልህ፣ እግዚአብሔር ይፍታህ፣ ወደፊትም የዚህ ዓይነት ክፉ ሥራ አትሥራ።” በማለት መልሰውለታል። ቀጥሎም ይህ ሰው ወደ ሌላ ሥራ የላከውን ሹፌራቸውን እስኪመጣ ድረስ ሳይጠብቅ ለአባታችን ሌላ ሾፌርና አጃቢ አዘጋጅቶ ወደ መንበረ ጵጵስናቸው፣ ነቀምቴ ከተማ በክብር እንዲመለሱ አድርጓቸዋል። በእውነቱ ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ጸሎት ምላሹ ፈጣን ነው።
የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በአንድ ወቅት አባታችንን አግኝቶ በዚያን ጊዜ ስለነበረው ሁኔታ ስጠይቃቸው እርሳቸው ግን ዝርዝር ውስጥ ሳይገቡ በጠቃላይ “ሁኔታው ሲፈጠር ወደ ፈጣሪዬ ጸለይኩ፤ ያቀረብኩትም ጸሎት በጌታዬ መንበረ ፀባዎቱ ፊት ቀርቦ ወዲያውኑ የአፈጻጸም መልስ ተሰጠኝ” በማለት ለዛ ባለው አነጋገር መልሰውልኛል።
ውድ ወገኖቼ!
ልብ ብላችሁና አስተውላችሁ ከሆነ ብፁዕነታቸው ሲያስተምሩ በሰው ልጅ ላይ የሚደርሰውን ግፍና ጭቆና የማይሹ ሁልጊዜ ሠላምን የሚሰብኩ የትህትና አባት ነበሩ። በተጨማሪም ለሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንና ለሕግ እንድንታዘዝ ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን እንድናውቅና እንድናስከብር። በልዩ ልዩ እንግዳ ትምህርትና ተራ አሉባልታ እንዳንፈታ በያዝነው ዓላማ እንድንፀና በጸሎት እንድንተጋ እርስ በርሳችን እንድንከባበር፣ እንድንዋደድና እንድንስማማ ይህንንና የመሳሰሉትን ምክርና መንፈሣዊ ትምህርት ሲሰጡን ቆይተው በሥጋ ከኛ ተለይተዋል ሆኖም በመንፈስ ዘወትር ከእኛ ጋር ናቸው።
በዓለም ዙሪያ ያሉትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋኅዶ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸውን ሁሉ እንግዚአብሔር ያጥናን።
በጸሎተ ፍትሀቱ ወቅት በብፁዕ አቡነ ሉቃስ በሲያትል ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን የበላይ ጠባቂ ሲነገር እንደሰማነው፤ የብፁዕ አባታችን አቡነ ዜና ማርቆስ አፅም ያርፍበታል ተብሎ የታሰበውና በቅርቡ ይገነባል የተባለው በሂውስተን ቴክሳስ የሚገኘውን ገዳም ለሁላችንም ስደተኛ ኢትዮጵያውያን መታሰቢያና የታሪክ ወመዘክር ሊሆን ስለሚችል በጉልበት፣ በእውቀት፣ እንድንረዳ አስፈላጊ ነው ብዬ በግሌ አምንበታለሁ። እርግጠኛ ነኝ ሁላችሁም በዚህ የተቀደሰ ተግባር እንደምትሳተፉ ጥርጥር የለኝም።
የብፁዕ አባታችን ቡራኬ ይድረሰን!
አቤል አድማሱ