“ባይጫኑን! ባይገፉን! ጥሩ ነው፤ ከተጫኑን ግን ሁሉን ነገር ይፋ እናወጣዋለን!” አቶ ስየ አብርሃ

Ethiopia Zare (ረቡዕ መጋቢት 1 ቀን 2002 ዓ.ም. March 10, 2010)፦ አቶ ስየ አብርሃ እና ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አሁንም በመከላከያ ሚኒስትርነትና በፕሬዝዳንትነት ሲያገለግሉት የነበረውን የህወሓት/ኢህአዲግ አገዛዝ ከመንቀፋቸውም በላይ አቶ ስየ አብርሃ ከፍተኛ ትኩረት ለሳበው የቢቢሲ ዘገባ ምላሽ ሰጥተዋል።

 

የካቲት 28 ቀን 2002 ዓ.ም. አቶ ስየ አብርሃ “ደርግ መውደቁ ጥሩ ቢሆንም ብዙ የተበላሹ ነገሮች አሉ። ስለዚህም ዝም ብዬ አልቀመጥም” ያሉ ሲሆን፤ “ከኢሳይያስ አፈወርቂ ጫና ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መገላገል ስንችል ያ ሊሆን ባለመቻሉ ከህወሓት የተለየን መሆኑ አሁንም ግንዛቤ ማግኘት አለበት” በማለት ከእነ አቶ መለስ እሳቸውና ሌሎች የህወሓት አባላት ከታገሉለት ድርጅት የተነጠሉበትን ምክንያት ለአዲስ አበባ እና ለመላው ኢትዮጵያ ህዝብ በድጋሚ ገልጸዋል።

 

“ሠላማዊ እንጂ የትጥቅ ትግል ሙሉ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በኢትዮጵያ ሊያሰፍን እንደማይችል በመገንዘቤ አንድነት ፓርቲን ተቀላቅያለሁ” የሚሉት ስየ አብርሃ፤ “የዮሐንስ እና የአሉላ የትውልድ ሥፍራ እና የህወሓት የማይደፈር አካባቢ በሆነው በትግራይ ተምቤን ተወዳድሬ በምርጫ እንደማሸንፍ አልጠራጠርም” በማለት ጠንካራ የሆነ አቋማቸውን ግልጽ አድርገዋል።

 

ሰሞኑን ቢቢሲ ባሰራጨው የህወሓት የትጥቅ ትግልንና የ1977ቱን ረሃብ ሁኔታ የሚዳስስ ዝግጅት ላይ የሚያውቁትን ይናገሩ ዘንድ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ስዬ “መረጃ ኃይል ነው፣ መረጃ ሀገር ሊያፈርስ የሚችል ነገር ነው” የሚለውን ቃል በማስቀደም በመቶዎች የሚቆጠር ሚሊዮን ብር ህወሓት በ1977 ዓ.ም. ከረድኤት ድርጅቶች ያገኘ መሆኑን አምነዋል። ይሁን እንጂ አቶ ስዬ አብርሃ “ህወሓት ያገኘውን ገንዘብ 95 እጅ ከመቶ ለጦር መሣሪያ ግዢ አወሎታል” የሚባለው ሐሰት ነው ካሉ በኋላ፤ ገንዘቡ የዋለው በረሃብ የተጠቃውን ከማይጨው ባሻገር ያለውን የትግራይ ህዝብ ለመታደግ፣ ለመልሶ ማቋቋም፣ ኤፈርትን ለመመሥረት፣ የተሰዉ ታጋዮችን ቤተሰቦች ለመደጎም፣ ለመሶበ ሲሚንቶ፣ ለአዲግራት መድኃኒት፣ ለአልመዳ ጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ መቋቋሚያ በእርሾነት ነው። ከደርግ የማረክነው የጦር መሣሪያ በቂ ቢሆንም፣ ታንከና አየር መቃወሚያ የትየለሌ መሆኑ ባይከድም … በእርዳታ ከተገኘው ገንዘብ ለተሸከርካሪዎች ነዳጅና ለጦር መሣሪያዎቹ አገልግሎት ለሚውሉ ግብዓቶች ወጪ መደረጉን ማስተባበል እንደማይቻል ሳይጠቁሙ አላለፉም።

 

“የኢትዮጵያ አንድነት ጥያቄ በጥያቄነት መቅረብ የለበትም፣ ኢህአዲግ ስለ ብሔር ብሔረሰቦች የሚያወራው ነገር ተቀባይነት የሌለው ነው፣ ብሔራዊ መግባባት በሚፈጠርበት ሁኔታ ሕገ-መንግሥቱ መሻሻል አለበት፣ ኢትዮጵያ የባሕር በር መብቷ ሊጠበቅላት ይገባል። ይህም ጠንካራና ሀገር ወዳድ መሪ በሚኖርበት ጊዜ ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ነው፣ የኤርትራም ዘለቄታዊ ዕድል ከኢትዮጵያ ጋር የተያያዘ ነው …” በማለት ድምፃቸውን ያሰሙት ስየ አብርሃ፤ “ባይጫኑን! ባይገፉን! ጥሩ ነው፤ ከተጫኑን ግን ሁሉን ነገር ይፋ እናወጣዋለን!” በማለት የህወሓትን ሰዎች ለማስጠንቀቅ ሞክረዋል። ስላለፈው ጊዜ ስህተት ሁሉ የኢትዮጵያን ህዝብ ቆሞ ይቅርታ መጠየቅ ለእሳቸው ክብር መሆኑንም በግልጽ አስታውቀው፤ “ይቅርታ ለመጠየቅ ግን የይቅርታ ሥርዓት መኖር አለበት። ይቅርታ ሰጪና ተቀባይ ሊኖሩ ይገባቸዋል፤ አሁን ከ40 ዓመታት በላይ የሆነውን የጦርነት አዙሪት ልናቆመው ይገባል። አዙሪቱን ካላቆምነው ለልጅ ልጆቻችን ጦሱ ይተርፋል። ስለዚህ ለብሔራዊ መግባባትና ዕርቅ እንሥራ!” የሚለውን ጥሪአቸውንም አስተላልፈዋል።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ የበኩላቸውን መሰል መልዕክት ያስተላለፉት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ፤ በአዲስ አበባ ከተማ ወረዳ 18 የፌደራል ፓርላማ ዕጩ ተወዳዳሪ መሆናቸውን በማሳወቅ፤ ህዝቡ ለሠላማዊ ትግል ስምረትና በምርጫው ኢህአዲግን ተሸናፊ ለማድረግ እርስ በርሱ በጩኸት በመጠራራት በአንድነት የመቆሙን እውነት ያረጋግጥ ብለዋል።

 

ዜጎች ከአስመሳይ ተመራጮች ራሱን እንዲጠብቅ ያስገነዘቡትም በ1992 ዓ.ም. የኦህዲድ ኢህአዲግ ካድሬዎች ህዝቡን ለማደናገር የሠሩትን ሥራ ሲያጋልጡም “የመቶ አለቃ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስና አቶ በድሩ አደም በ1992 ዓ.ም. በጅማና በወሊሶ ዕጩ ተወዳዳሪ ሆነው በመቅረብ አሸናፊ ሆነዋል የተባሉት በቅድመ የኦህዲድ ካድሬዎች ጥቆማና ህዝቡን የማወናበድ ሤራ መሆኑን አውቃለሁ” ብለዋል ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ