አቶ ስዬ አብርሃ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ ላይ አቶ መለስን ተቹ
Ethiopia Zare (ማክሰኞ ግንቦት 26 ቀን 2000 ዓ.ም. June 3, 2008)፦ የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር አቶ ስዬ አብርሃ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ጉዳይ ላይ ያላቸውን አስተያየት ሰጡ። የድንበር ማካለሉን አስመልክቶ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሰጠውን መግለጫ፣ በተለይም ጠ/ሚ/ር መለስ ዜናዊ ለፓርላማው ግንቦት 13 ቀን 2000 ዓ.ም. የሰጡትን ማብራሪያ አቶ ስዬ አብርሃ ተችተዋል።
አቶ ስዬ በዚህ በጽሑፍ ባቀረቡት ትችታቸው/አስተያየታቸው ካካተቷቸው ንዑስ ርዕሶች ውስጥ “ግጭት ለመፍጠር ሆን ተብሎ የሚደረግ አደገኛ አሻጥር”፣ “ከዘመነ ሉላዊነት (ግሎባላይዜሽን) ጋር መሄድ ያቃተው የኢህአዴግ የብዙኀን መገናኛ ፖሊሲ እና የገባበት አጣብቂኝ”፣ “መንግሥት ከሰጠው ማብራሪያ እስከ አሁን ለማወቅ የቻልነው ምንድን ነው?”፣ “ኢህአዴግ በድንበሩ ጉዳይ ፓርላማውን ሳይቀር አለማሳወቁ ከምን የተነሳ ሊኾን ይችላል?”፣ “የሱዳን መንግሥት አርቆ አስተዋይነት” የሚሉትን አካትተዋል።
አቶ ስዬ እሳቸው በሥልጣን ላይ በነበሩበት ጊዜ ስለ አካባቢው የሚያውቁትን በዚህ ጽሑፋቸው ሲያስረዱ እንደሚከተለው አስፍረውታል።
“… ሱዳኖች በድንበር አካባቢ የጀመሩትን ጉዳይ አላቆሙም። ይባስ ብለው በእርሻ ሥራ መቋቋም የጀመሩትን ኢትዮጵያውያን ገበሬዎችን መተናኮል እና መጋፋት ጀመሩ። ይህ ኹኔታ እየባሰበት በመሄዱ ውሱን የመከላከያ ኃይል በዚሁ አካባቢ በማስፈር ቀስ በቀስ ይህንኑ ማጠናከር ጀመርን። ሠራዊቱ ይህን በአራሾች ላይ የሚደርሰውን በደል እና በዓይናችን ፊት የሚደርሰውን ውድመት መቃወም ጀመረ። …
“… አንድ ቀን በዚህ አካባቢ የተመደበው የመከላከያ ሠራዊታችን አዛዥ የጽሑፍ መልዕክቱን አስይዞ አቻው ወደ ኾነው የሱዳን ጦር አዛዥ አንድ መልዕክተኛ ጓድ ይልካል። የተላከው ጓድ የተደረገለት አቀባበል የወዳጅ አገር ሠራዊት አቀባበል አልነበረም። ኑ ብለው ተቀብለው ትጥቃቸውን አስፈትተው አረዷቸው። ይህ ድፍረት እና ጭካኔ እንደተፈፀመ ሠራዊታችን አይምሬ የአፀፋ እርምጃ ወስዶ በአካባቢው የነበረው ጦር እንደወጣ ቀረ። እኔ በኃላፊነት እስከነበርኩበት ጊዜ ድረስ ሱዳኖቹ ወደዚህ አካባቢ ተተኪ ሠራዊት አልላኩም። …”
አቶ ስዬ በዚህ ጽሑፋቸው ማሳረጊያ ላይ የሚከተለውን አስፍረዋል። “የአቶ መለስ መንግሥት ከኤርትራ እና ኢትዮጵያ ድንበር ክርክር ጋር በተያያዘ በአንዳንድ የጾረና እና የአካባቢዋ ቦታዎች ላይ ለኤርትራ ምስክርነት መስጠቱ እና የሄጉ ኮሚሽን በዚሁ ተመስርቶ እነዚህ አካባቢዎችን ለኤርትራ እንዲሰጡ መወሰኑን ከኮሚሽኑ ሪፖርት ለመገንዘብ ችለናል። አሁንም በአንድ በኩል “ድንበር አልተካለልንም” እየተባለ በሌላ በኩል ደግሞ “ሠራዊታችን በወሰደው ማጥቃት ምክንያት የእኛ አራሾች ገብተውበት ሲጠቀሙበት የቆየ የእኛ ያልኾነ መሬት ነው” ብሎ አስቀድሞ በኢትዮጵያ ላይ እየመሰከረ ነው። አቶ መለስ ስለሱዳኖች አርቆ አስተዋይነት ከመናገሩ በፊት ስለገዛ ራሱ አስተውሎት ቆም ብሎ ቢጠይቅ ይሻል ነበር።” ሲሉ አቶ ስዬ ተችተዋል።
አቶ ስዬ አብርሃ “የኢትዮ-ሱዳን ድንበር ማካለል እና መንግሥት የሰጠው መግለጫ” በሚል ርዕስ አስተያየታቸውን በጽሑፍ ያቀረቡት ሀገር ቤት በሚታተመው “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ቅጽ 1፣ ቁጥር 32፣ ቅዳሜ ግንቦት 23 ቀን 2000 ዓ.ም. ዕትም ላይ ነው። ሙሉውን ጽሑፍ በፒ.ዲ.ኤፍ. ለማንበብ ከፈለጉ እዚህ ላይ ይጫኑ!