መኢአድ በአራተኛው ዙር የፓርቲዎች ክርክር ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳተፈ
Ethiopia Zare (ዓርብ መጋቢት 10 ቀን 2002 ዓ.ም. March 19, 2010)፦ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሲካሄድበት የቆየው የፓርቲዎች ክርክር አራተኛው ክፍል ዛሬ ዓርብ መጋቢት 10 የተጀመረ ሲሆን፤ በቀደሙት ሦስት የተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ በክርክሩ ያልተሳተፈው የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ለመጀመሪያ ጊዜ ተሳታፊ ሆኗል።
“የጤና ጉዳዮች በኢትዮጵያ” በሚለው ርዕስ ላይ የተካሄደው አራተኛው ዙር ክርክር ላይ መኢአድን ጨምሮ ስድስት ፓርቲዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
በዚሁ ክርክር ከኢዴፓ አቶ ሙሼ ሰሙ፣ ከመድረክ ፕሮፌሠር በየነ ጵጥሮስ፣ ከመኢአድ አቶ አበባው መሀሪ፣ ከቅንጅት አቶ አየለ ጫሚሶ፣ ከገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ ደግሞ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድኀኖም በመወከል የውይይት ሃሳቦችን ያቀረቡ መሆኑ ታውቋል።
ፕ/ር በየነ የሀገሪቱ የጤና ችግር ዋና ምክንያት የጤና ፖሊሲ ያለመሻሻል መሆኑን ጠቅሰው በሽግግር መንግሥቱ አካል ሆኜ በነበርኩበት ሰዓት በተረቀቀ ፖሊሲ እስካሁን ድረስ መቀጠሉና በፖሊሲው ምንም አይነት መሻሻል ባለመደረጉ የጤና ችግሩ እንዲባባስ አድርጓል ብለዋል። በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ ምንም አይነት ተጨማሪ ሆስፒታሎችን መክፈት ያለመቻሉና በኃይለሥላሴ ጊዜ የተከፈቱ ሆስፒታሎችም ከመፈራረስ ውጭ ትኩረት ተሰጥቶት ኅብረተሰቡን ሊጠቅም አለመቻሉን አብራርተዋል።
የኢዴፓው አቶ ሙሼ ሰሙ በጤና ችግር መባባስ የተነሳ ዜጎች አላስፈላጊ ወደሆነ የጥንቆላ ሕክምና እንዲያመሩ እየገፋፋ መሆኑንና በሙያው የሠለጠኑ ባለሙያዎችም ሀገር ጥለው እንዲወጡ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል።
የመኢአድ ተወካይ አቶ አበባው መሀሪ ድርጅታቸው ባለፉት ክርክሮች ያልተሳተፈው ለፓርቲዎች የተሰጠው ሰዓት ያልተመጣጠነ በመሆኑና አከራካሪዎች ልምድ ያላቸው እንዲሆኑ ያቀረበው ትያቄ ምላሽ ያለማግኘቱን በማብራራት ቢጀምሩም፤ ክርክሩ በጤና ጉዳይ በመሆኑ በቀጥታ ወደ ክርክሩ ርዕስ እንዲገቡ በአከራካሪዎች ተጠይቀዋል።
በርዕሱ ጉዳይም መኢአድና ሌሎቹም ፓርቲዎች አንገብጋቢ ያሏቸውን የባለሙያ ፍልሰት፣ የደመወዝ አለመመጣጠን፣ ህዝቡን የማንቃት ችግሮች፣ ... በማንሳት የአገዛዙን ድክመቶች አስቀምጠዋል።
የገዥው ፓርቲ ተወካይ ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሀኖምም የቀረቡት ትችቶች የጤና ችግርን መንግሥታቸው ከወሰደው እርምጃ ጋር ሲወዳደር ጥቂት መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ተቃዋሚዎች ድክመትን ብቻ ማንሳት የለባቸውም ብለዋል። በማጠቃለያቸውም በዓለማቀፍ ደረጃ በጤና ጉዳይ ላይ ከፍተኛ ነጥብ ማስመዝገባቸውን አብራርተዋል።



