ስድስተኛው ዙር የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ቀጥሏል
Ethiopia Zare (ዓርብ ሚያዝያ 1 ቀን 2002 ዓ.ም. April 9, 2010)፦ መኢአድ፣ መኢብል፣ መድረክ፣ ኢዴፓ፣ ቅንጅት እና ገዥው ፓርቲ ኢህአዲግ የተሳተፉበት ስድስተኛው ዙር የፓርቲዎች ክርክር ተካሄደ።
”የውጭ ጉዳይ ግንኙነት ላለፉት 19 ዓመታት” በሚል ርዕስ በተካሄደው ክርክር ኢህአዲግ በአቶ አርካበ ዕቁባይ እና በአቶ ሬድዋን ሁሴን፤ መኢአድ በአቶ ያዕቆብ ልኬ፤ ኢዴፓ በአቶ ልደቱ አያሌው፤ መኢብን (የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ) በአቶ መስፍን ሽፈራው፣ ቅንጅት በአቶ ለገሰ ቢራቱ እንዲሁም መድረክ በአቶ ስየ አብርሃ ተወክለው በመወያያ ርዕሱ ዙሪያ ያላቸውን ዋና ዋና ሃሳቦች አቅርበዋል።
በቀድሞው መከላከያ ሚኒስትር በአቶ ስየ አብርሃ የተወከለው መድረክ ሉዓላዊነት ጋር የተያያዙ ጉዳዮች ላይ እና በጎረቤት ሱዳን ድንበር ለባዕዳን እየተሰጠ ያለውን መሬት በሚመለከት ከመግለጻቸውም በላይ፤ በወደብ አጠቃቀም ዙሪያ በተለይ በኢህአዲግ እምቢተኝነት ከጅቡቲ ጋር ተደርጎ የነበረውን ጠቃሚ የወደብ ስምምነት ድርጅታቸው ቢመረጥ ከእንደገና በማንሳት ዘላቂ መፍትሔ እንደሚያደርግለት በአጽንዖት ገልጸው፤ ኢትዮጽያ ሕጋዊ የባህር በር እንደሚያስፈልጋት ተናገግረዋል።
የመኢአዱ (የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት) ተከራካሪ አቶ ያዕቆብ፤ ኢትዮጵያ ሉዓላዊነቷን የሚያስጠብቅ መሪ እንዳላገኘችና አሁን ያለውም አንድ ግለሰብ እንደፈለገ የሚያሽከረክራት ሀገር መሆኗን አስረድተዋል። ባለፉት የንጉሡ እና የወታደራዊው መንግሥታት ባሳለፉት የአገዛዝ ዘመን እያንዳንዳቸው አራትና አምስት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሲያፈሩ አሁን አለው የኢህአዲግ መንግሥት ላለፉት 19 ዓመታት አንድ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዲኖራት ማድረጉ፤ ‘ሀገሪቱ ምንም ሰው የላትምን?’ የሚል ጥያቄ እንደሚያስነሳ ገልጸዋል።
የኢዴፓው አቶ ልደቱ አያሌው ሉዓላዊነቷ የተጠበቀች ሀገር እንድትሆን ያስፈልጋሉ ያሏቸውን ስምንት ነጥቦች አስቀምጠዋል። ኢትዮጵያ አሁን ባለችበት ሁኔታ ዝቅ ብላ የተቀመጠች ሀገር መሆኗን ገልጸው፤ ድርጅታቸው ለሥልጣን ቢበቃ ብሔራዊ መግባባትን እንደሚያመጣ፣ ሀገራዊ ጥቅም የሚያስቀድም፣ በህዝብ የሚወደድ መንግሥት እንዲኖር እንደሚያደርግ፣ የሀገሪቱ ዲፕሎማቶች በሙያ ብቃታቸው እንደሚሾሙ፣ ማናቸውም በውጭ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የጣምራ ዜግነት እንዲኖራቸው በማድረግ በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ሙሉ ተሳታፊ እንዲሆኑ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
የመኢብን (የመላው ኢትዮጵያ ብሔራዊ ንቅናቄ) ፓርቲን መከራከሪያ አቀረቡት አቶ መስፍን ሽፈራው፤ አገዛዙ በውጭ ጉዳይ ላይ ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮች ላይ ጥሩ እየሠራ መሆኑን ገልጸው፤ መቃወም ብቻ መፍትሔ እንዳልሆነ አስረድተዋል።
የቅንጅት ተወካይ አቶ ለገሰ ቢራቱ በበኩላቸው በውጭ ጉዳዮች ዙሪያ ጠቃሚ ናቸው ያላቸውን ሃሳቦች አቅርበዋል።
በሉዓላዊነት ትርጓሜ ንግግራቸውን የጀመሩት የኢህአዲጉ አቶ አርካበ ዕቁባይ፤ ተቃዋሚዎችንና ፓርቲያቸውን በማነጻጸር ኢህአዲግ ለሉዓላዊነት ቅድሚያ በመስጠት ከውጭ መንግሥታት ጋር በመሥራት ላይ መሆኑንና ተቃዋሚዎች ግን ለውጭ ኃይላት ተንበርካኪ ሆነዋል ሲሉ ተደምጠዋል። ሌላው የኢህአዲግ ተወካይ አቶ ሬድዋን ሁሴንም ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ በአፍሪካ ሀገራት ጉዳዮች ላይ በመሪነት የምትመረጠው ኢህአዲግ ባሳየው ብቃት ነው ብለዋል።



