Ethiopian Airlines Bombardier Q400 / የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦምባርዲየር ኪው 400 አውሮፕላንEthiopia Zare (እሁድ መጋቢት 12 ቀን 2002 ዓ.ም. March 21, 2010)፦ በ192 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለመግዛት ካዘዛቸው ስምንት ቦምባርዲየር ኪው 400 አውሮፕላኖች ውስጥ የመጀመሪያው አንድ አውሮፕላን ዛሬ መጋቢት 12 ቀን 2002 ዓ.ም. አዲስ አበባ ገባ። አውሮፕላኑ ዘመናዊ፣ ባለሁለት ሞተርና 78 መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን፣ ስምንቱም አውሮፕላኖች ለሀገር ውስጥ በረራ የሚውሉ ናቸው። 

 

ባለሁለት ሞተር የሆነው ይኸው ኪው 400 የተሰኘው አውሮፕላን የአንዱ ዋጋ 24 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ሲሆን እጅግ ዘመናዊ መሆኑ ተነግሮለታል። በበረራ ላይ እያለ ችግር ቢገጥመው በአንዱ ሞተር ብቻ በመጠቀም መሬት ላይ ማሳረፍ እንደሚቻል ለማወቅ ተችሏል።

 

አየር መንገዱ በተለይም በሀገር ውስጥ በረራው በመዘግየት፣ በበረራ መሰረዝ እና በመስተንግዶ ከፍተኛ ቅሬታና ትችት ይቀርብበት የነበረ ሲሆን፣ እነዚህ ስምንት ቦምባርዲየር ኪው 400 አውሮፕላኖቹን ተጠቃልለው ሀገር ውስጥ ሲገቡ የሀገር ውስጥ በረራው ይሻሻላል ተብሎ ይታመናል።

 

ዛሬ የገባው አውሮፕላን በሚቀጥለው ሣምንት ሥራውን የሚጀምር ሲሆን፣ ቀሪዎቹ 7 አውሮፕላኖች ደግሞ እስከሚቀጥለው ዓመት (2003 ዓ.ም.) ጥቅምት ወር ድረስ ተጠናቅቀው እንደሚገቡ ለማወቅ ተችሏል።

 

አውሮፕላኖቹ የታዘዙትና የተገዙት ከካናዳው ቦምባርዲየር ኩባንያ ሲሆን፣ የመግዣው ገንዘብ ደግሞ በብድር የተገኘው ከካናዳ መንግሥት መሆኑን የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ግርማ ዋቄ ገልፀዋል። አክለውም አየር መንገዱ ብድሩን በአስር ዓመታት ውስጥ ከፍሎ እንደሚጨርስ እምነታቸው መሆኑን ሳይገልፁ አላለፉም።

 

50 መቀመጫዎች ያሏቸውንና ላለፉት 15 ዓመታት በሀገር ውስጥ በረራ አየር መንገዱ ይጠቀምባቸው የነበሩትን “ፎከር” የተሰኙትን አውሮፕላኖች አዲሶቹ ቦምባርዲየር ኪው 400 አውሮፕላኖች እንደሚተኳቸው ታውቋል። አየር መንገዱ ቦይንግ 737 የተሰኘውን አውሮፕላንም በሀገር ውስጥ በረራ እንደሚጠቀም ይታወቃል።

 

አየር መንገዱ ባለፉት ስድስት ወራት 215 ሺህ መንገደኞችን በማጓጓዝ ወደ 59 ሚሊዮን የሚጠጋ የኢትዮጵያ ብር ማግኘቱን ያሳወቀ ሲሆን፤ በያዝነው የ2002 ዓ.ም. ማብቂያ ድረስ 500 ሺህ መንገደኞችን በማመላለስ 100 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር ለማስገባት አቅዷል።

 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአፍሪካም ሆነ ከዓለም ምርጥ ከሚባሉት አየር መንገዶች ውስጥ አንዱ መሆኑ ይታወቃል።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ