Ethiopia Zare (እሁድ መጋቢት 28 ቀን 2000 ዓ.ም. April 6,2008) የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን የኤሌክትሪክ ኃይል በፈረቃ ማከፋፈል መጀመሩን በይፋ አስታወቀ። ባጋጠመው የኃይል እጥረት ምክንያት የፈረቃ ፕሮግራሙ ለሚቀጥሉት ሦስት ወራት ይቀጥላል። በአዲስ አበባ የውሃ አገልግሎት እንዳይቋረጥ ለውሃ ፓምፖች ኃይል ማመንጫ በተመረጡ አራት ቦታዎች ላይ የዲዝል ጄነሬተር ተከላ እየተካሄደ ነው። 

 

ኮርፖሬሽኑ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ እንደተገለፀው በአዲስ አበባ በከተማ ውስጥ የኃይል እጥረት በመከሰቱ የፈረቃ ፕሮግራሙን ለመጀመር እንደተገደደና የተፈጠረውን የኃይል እጥረት ለመቋቋም አስፈላጊ ቦታዎች ላይ በተተከሉ የዲዝል ጄነሬተር ጣቢያዎች አማካኝነት ችግሩን ለመቋቋም ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ለዲዝል ጀኔሬተሮቹ ከ100 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ እየተደረገ ነው። 

 

በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት የኮርፕሬሽኑ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ምሕረት ደበበ እንደገለጹት አሁን የተከሠተው የኃይል እጥረት 80 ሜጋ ዋት ሲሆን እጥረቱ ሊከሠት የቻለው የኃይል ፍላጐት እድገቱ ካለፈው ዓመት በ12 በመቶ ከፍ በማለቱ የአቅርቦት ክፍተት ሊፈጠር ችሏል። በተጨማሪም የበልግ ዝናብ መጣል በነበረበት ጊዜ ባለመጣሉ እንዲሁም ይጠናቀቃሉ ተብለው የተገመቱ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ከተወሰነው ጊዜ ወደፊት መግፋታቸው የአቅርቦት እጥረቱ እንዲፈጠር አድርጓል። 

 

እንደ አቶ ምህረት ገለፃ የፈረቃ ፕሮግራሙ አጭርና በየትኛውም ሀገር ሊፈጠር የሚችል በመሆኑ ደንበኞች ችግሩን እንዲገነዘቡ አሳስበዋል። በዚህም የአጠቃቀም ባሕልን መለወጥና አማራጭ ኃይሎችን በመጠቀም ችግሩን መፍታት እንደሚችል አሳስበዋል። 

 

ያጋጠመውን የኃይል እጥረት ለዘለቄታው ለመፍታት በአጭርና በመካከለኛ ጊዜ ግንባታቸውን የሚያጠናቀቁ ፕሮጀክቶችን ለማድረስ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ተገልጿል። ከነዚህም ውስጥ በሐምሌ ወር ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀውና 300 ሜጋዋት የሚያመርተው የተከዜ ፕሮጀክት ይጠቀሳል። 

 

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ኮርፖሬሽን ከመላ ሀገሪቱ የኃይል ፍላጐት ውስጥ እስካሁን ማሟላት የቻለው 22 በመቶ ብቻ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት መጨረሻ 30 በመቶ ለማድረስ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል። 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ