የመብራት መቋረጥ ችግር መፍትሔ አልተበጀለትም
Ethiopia Zare (ቅዳሜ ግንቦት 8 ቀን 2001 ዓ.ም. May 16, 2009)፦ በአዲስ አበባ ከተማ በአንዳንድ አካባቢዎች በሣምንት ከሦስትና ከአራት ቀናት በላይ የመብራት መቋረጥና ካናካቴውም የመጥፋት ችግር እያጋጠመ መሆኑንና ችግሩ ካለፈው ሣምንት ረቡዕ ሚያዝያ 21 ቀን 2001 ዓ.ም. ወዲህ ባለው ጊዜ ተባብሶ መቀጠሉ ተገለጸ።
ይህ በመሆኑም በከተማይቱ ከኤሌትሪክ ጋር የተገናኘ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት ከዚህ ቀደም ያገኙት የነበረውን ትርፍ ለማጣት ከመገደዳቸውም በላይ የሠራተኞቻቸውን ደምወዝ ለመክፈል የማያስችል ደረጃ ላይ እየደረሱ መሆኑን ምንጮቹ ገልፀዋል። በአንፃሩም ለመንግሥት ወርሃዊ ኪራይና የግብር ገቢ በአግባቡ በሚከፍሉበት ሁኔታ ይህ ችግር እልባት እንዲያገኝ በመብራት ኃይል በኩል ችግሩን ለመፍታት ይሄ ነው የሚባል ጥረት አለመደረጉ እያሳሰባቸው መሆኑን አንዳንድ ተጠቃሚዎች ገልጸዋል።
ስለኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫዎች አቅም መጎልበትና ስለስርጭቱ አስተማማኝነት በመንግሥት በኩል እጅግ ብዙ እየተባለ ቢሆንም፤ ብዙዎቹ የአዲስ አበባ ከተማ ክፍለ ከተሞች ግን መብራት በፈረቃ ማግኘት ከጀመሩና የምሽቱን ጊዜ በአማካይ እስከ 4፡30 ሰዓት በጭለማ መዋጥ ከመጀመራቸውም በላይ መብራት ከፈረቃ ውጭ የሚቋረጥባቸው ቦታዎች እንዳሉም ለማወቅ ችለናል። ተመሳሳይ ችግር በጋምቤላ፣ በባሕርዳር፣ በጎንደርና በሐረር መኖሩን መረጃዎች ያመለክታሉ።