አጥጋቢ ዝናብ ካልኖረ በኢትዮጵያ ያለው ችግር እንደሚባባስ ተገለጸ

Ethiopia Zare (ሰኞ ሰኔ 1 ቀን 2001 ዓ.ም. June 8, 2009)፦ የመብራት ስርጭት እጥረት በመላ ሀገሪቱ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ መምጣቱንና ብዙ ቦታዎች በሁለት ቀን አንድ ቀን ብቻ እየደረሳቸው ከመምጣቱም በላይ ከመብራት ጋር የተያያዙ ዕቃዎችን የኤሌክትሪክ ውጤቶች ዋጋ በእጥፍ እየጨመረ መሆኑን ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና አስረዳ።

 

ታላላቅ ፋብሪካዎች ሥራቸውን እንዲያቆሙ ወይንም የምርት ውጤቶቻቸውን በውድ ዋጋ እንዲሸጡ የተገደዱበት ይሄው የመብራት እጦት በውሃ ክፍፍሉም ላይ ከፍተኛ ችግር እያስከተለ ከመሆኑም አልፎ በተለይ በጅማ፣ በደሴና ጎንደር፣ እንዲሁም በባህርዳር አካባቢ የውሃ አገልግሎት በየሣምንቱ እንደሚለቀቅላቸው ለማወቅ ችለናል።

 

በተያያዘም ቀጣዩ ሣምንት የሚገባው ሰኔ ወር አጥጋቢ የዝናብ መጠን የሚኖረው ካልሆነ በኢትዮጵያ ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች ተባብሰው እንደሚቀጥሉ ባለሙያዎች ያስታወቁ ሲሆን፣ ባለፉት ሁለት ወራት በአብዛኛው ሰሜናዊ፣ ምሥራቃዊ ሰሜንና ምዕራባዊ ሰሜን ግዛቶች ዝናብ ባለመጣሉ የተከዜና የዓባይ ወንዞች እንዲሁም የእነዚሁ ወንዞች ገባር የሆኑ ዥረቶች የውሃ አቅም በእጅጉ ቀንሷል።

 

የጣና ሐይቅ የውሃ መጠንም በአሳሳቢ ሁኔታ በመውረድ ላይ ነው። አብዛኛው ህዝቧ ገበሬና የገበሬውን ዓመታዊ ምርት ጠባቂ በሆነችው ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ስጦታ የሆነው ዝናብ መምጣትና መቅረት የዜጐቿን ሕልውና የሚወስን መሆኑ የማይታበል ሐቅ ስለሆነ፤ ከበልግ ወራት መባቻ ጀምሮ በአብዛኛው የሀገሪቱ ግዛት የተስተዋለው የአየር ድርቀትና ኃይለኛ ንፋስ የገጠሩን ህዝብ አሳስቦታል።

 

በምዕራብና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የአየሩ ሁኔታ ለመጪው ዓመት የሀገሪቱ ሰብል ምርት ማማር አስደሳች ምልክት የሚሰጥ አይደለም። በዚሁ የዝናብ እጥረት ችግረኛ በነበረው የኃይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ መሠረታዊ ስህተት ምክንያት በመላው ኢትዮጵያ የኤሌትሪክ ስርጭት ቀውስ አጋጥሟል። የግልገል ጊቤ አንድ ግድብ ውሃ ከመቶ 75 እጅ በላይ በትነትና በስርገት እንዲሁም በአቅራቢያው ዝናብ ባለመጣሉ ቀንሷል። በተከዜም ተመሳሳይ ችግር ተስተውሏል። የጊቤ ቁጥር ሁለት እና ሦስት ፕሮጀክቶችም በቅርቡ የሚሰጡ መሆናቸው አልተረጋገጠም። የፊንጫ እና የቆቃ ኃይል ማመንጫዎችም ከሀገሪቱ ከፍተኛ የአቅርቦት ፍላጐት አኳያ ሲታዩ እንደሌሉ የሚቆጠሩ ናቸው። ስለሆነም ከእርሻው ክፍለ ኢኮኖሚም ሆነ ከሌላው ዘርፍ ተዛማጅ ችግር ጋር ተዳምሮ በኢትዮጵያ ማኅበራዊ ቀውስ መባባሱ የማይቀር ነው የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት።

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ